“የዘላለም ሕይወት ተስፋ የሚሰጠውን ሞት ለማስታወስ የተዘጋጀውን በዓል ማክበር
1 ሚያዝያ 6 ቀን 1993 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የዋነኛውን የሕይወት ማስገኛ ሞት እናከብራለን። (ሥራ 3:15 አዓት) በእርግጥም ለኢየሱስ ሕይወትና ሞት መታሰቢያ የሚሆን በዓል ማክበራችን በጣም ተገቢ ነው። ለዘላለም የመኖር ተስፋችን ራሱ በፈሰሰው የኢየሱስ ደም ላይ የተመሠረተ ነው።
2 የመታሰቢያው በዓል በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ላይ የክርስቶስ መሞት ያለውን አስፈላጊነት ያጎላል። ይህ ዓላማ የአዳምን ዝርያዎች ለመቤዠት የሚያስፈልገውን ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ መሥዋዕት መስጠትንም ይጨምራል። ይህም በመሥዋዕቱ ላይ እምነት የሚያሳድሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በገነቲቱ ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ያስችላቸዋል። — ዮሐ. 3:16
3 እውነትንና ሕይወትን የሚያፈቅሩ ሁሉ የኢየሱስን ትዕዛዝ በመከተል የጌታን ራት በዓል ለማክበር በጉጉት ይጠባበቃሉ። (ሉቃስ 22:19) በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት በኩል ለተደረገልን ዝግጅት ያለንን አድናቆት በግለሰብ ደረጃ ለማሳየት ምን ልናደርግ እንችላለን? የዚህን በዓል አስፈላጊነት በመገንዘብ ነገሮችን በጥሩ ሁኔታ ማደራጀት በጣም አስፈላጊ ነው። ለዚህ ልዩ በዓል ምን ዝግጅቶች እያደረጋችሁ ነው?
4 በቅድሚያ ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ ነው፦ እያንዳንዱ የቤተሰባችን አባል በበዓሉ ላይ እንዲገኝ እንደምናደርግ የተረጋገጠ ነው። በተጨማሪም በ1993 የቀን መቁጠሪያ ላይ ከሚያዝያ 1–6 ድረስ እንዲነበቡ የተሰጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በማንበብና በእነርሱም ላይ በማሰላሰል በአእምሮም ጭምር መዘጋጀት ይኖርብናል። ወደ ሚያዝያ 6 አቅራቢያ በግልና በቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ላይ የመታሰቢያ በዓሉን አስፈላጊነት የሚመለከቱ ሐሳቦችን ብንጨምር ተገቢ ይሆናል። ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባው ላይ የተገኙትን አዲሶች ለመቀበል ትችሉ ዘንድ ቀደም ብላችሁ ለመድረስና የመታሰቢያው በዓል ተከብሮ ካበቃ በኋላም ጥቂት ለመቆየት ዕቅድ አውጡ።
5 ከመታሰቢያው በዓል በፊት ባሉት ሳምንታት ውስጥ ፍላጎት ያላቸውን የምታውቋቸውን ሰዎች ሁሉ በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ጋብዟቸው። የግብዣ ወረቀት ለጉባኤያችሁ ተልኳል። እነዚህን የግብዣ ወረቀቶች በምትጠቀሙበት ጊዜ በአካባቢው በዓሉ የሚከበርበትን አድራሻና ሰዓት ፍላጎት ላለው ሰው መንገራችሁን አትርሱ። ልትጋብዟቸው የምትፈልጓቸው ሰዎች ስም ዝርዝር በጽሑፍ አዘጋጁ። በበዓሉ ላይ ለመገኘት የሚፈልጉ ሁሉ መጓጓዣ አላቸውን? ከሌላቸው እነሱን ለመርዳት ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? በመኪናችሁ ውስጥ ትርፍ ቦታ ካላችሁ ወይም የምትወስዱት ሰው ከሌላችሁ እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው ይኖር እንደሆነ ሽማግሌዎችን ለምን አትጠይቁም?
6 ይህ በዓመቱ ውስጥ ያለው ታላቅ በዓል ስለሆነ ብዙ ተሰብሳቢ እንደሚኖር ይጠበቃል። በዚህ ምክንያት ሽማግሌዎች አስቀድመው ልዩ ዝግጅቶችን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። (1 ቆሮ. 14:40) በበዓሉ ላይ አገልግሎት የሚሰጡ ወንድሞች የመቀመጫውን አዘገጃጀት እንዲሁም ምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን ጠጅ እንዴት መዞር እንዳለባቸው ገብቷቸው እንደሆነ ለማረጋገጥ ከሚያዝያ 6 አንድ ሳምንት ቀደም ብለው ወይም ከዚያ በፊት ጀምረው ሽማግሌዎች ከእነዚህ ወንድሞች ጋር ስብሰባ ለማድረግ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል። በዓሉ በሚከበርበት ጊዜ አስተናጋጅ እንድትሆን አለዚያም ቂጣውን ወይም ወይኑን እንድታዞር ተመድበህ ከሆነ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ሽማግሌዎች የሚሰጡትን መመሪያዎች በጥብቅ መከተልህን አረጋግጥ። ሽማግሌዎች በገጽ 7 ላይ ባለው ሣጥን ውስጥ ያሉትን ማስታወሻዎች በማየት ተሰብሳቢዎቹን፣ ምሳሌያዊዎቹን ቂጣና ወይን እንዲሁም አዟሪዎቹን እና ተናጋሪውን በተመለከተ አስፈላጊዎቹ ዝግጅቶች በቅድሚያ የተደረጉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ይችላሉ።
7 በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የቀሩት የክርስቶስ ወንድሞች ጥቂት ናቸው። በጣም ሩቅ ባልሆነ ጊዜ ውስጥ የጌታ ራት መከበሩ ያበቃል። (1 ቆሮ. 11:25, 26) በዓሉን የማክበሩ መብት እስካለን ድረስ ግን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ላስገኘው ሞት የተዘጋጀውን በዓል ማክበራችን ተገቢ ነው።