ለሕዝብ የምትሰጡትን የተስፋችሁን ምሥክርነት ሳትወላውሉ አጽንታችሁ ያዙ
1 ዛሬ ለአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ ‘ምግብ በተገቢው ጊዜ’ ከሚቀርብባቸው መንገዶች አንዱ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ነው። (ማቴ. 24:45) በዚህ በጣም አስፈላጊ የሆነ ስብሰባ ላይ የምንገኘው ለሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች ነው። ይኸውም በመንፈሳዊ ለመታነጽና ተስፋችንን በሌሎች ፊት ለመናገር ነው። — ዕብ. 10:23–25
2 ራሳችንን መጥቀም፦ በአንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ ትምህርቱን በቅድሚያ ተዘጋጅተው የሚመጡት ከተሰብሳቢዎቹ መካከል አንድ ሦስተኛዎቹ ብቻ እንደሆኑ ተገምቷል። ሐሳብ በመስጠት የሚካፈሉትም ይህንኑ የሚያክል ቁጥር ያላቸው ተሰብሳቢዎች ብቻ ናቸው። በመጠበቂያ ግንብ የሚቀርበውን ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ በጥናቱ ጊዜ ብቻ ሙሉ በሙሉ አላምጠን ልንውጠው አንችልም። በቅድሚያ ትምህርቱን ለማጥናት ጊዜ መመደብ ያስፈልጋችኋል።
3 ለጥናቱ በምትዘጋጁበት ወቅት በመጀመሪያ በሚጠናው ትምህርት መደምደሚያ ላይ ባለው ሣጥን ውስጥ ያሉትን ጥያቄዎች አንብባችሁ ብታሰላስሉባቸው ጠቃሚ ሆኖ ልታገኙት ትችላላችሁ። እንደዚያ ማድረጋችሁ በጥናቱ ውስጥ በሚሸፈኑት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ እንድታተኩሩ ሊረዳችሁ ይችላል።
4 በጥናቱ ወቅት የሚነገረውን ነገር በትኩረት አዳምጡ። ጥናቱን የሚመራው ወንድም የሚናገራቸው የመክፈቻ ቃላት የጥናቱን መንፈስ ስለሚገልጹ በትኩረት አዳምጡ። በኋላ መልስ የሚያገኙ ሦስት ወይም አራት ጥያቄዎችን ያነሳ ይሆናል። አለበለዚያም የዚህ ሳምንት ጥናት ባለፈው ሳምንት ከነበረው ርዕስ የሚቀጥል ከሆነ ያለፈውን ሳምንት ጥናት ጎላ ያሉ ነጥቦች ይከልስ ይሆናል። ስለአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ወይም የመሠረታዊ ሥርዓት እውቀት ላይ የተደረገ ማስተካከያ ካለ ይህንን ይጠቅሰዋል። እርግጥ ነው፣ የጥናቱ አንዱ ዓላማ የጉባኤው አባላት ተስፋቸውን እንዲገልጹ አጋጣሚ ለመስጠት ስለሆነ ጥናቱን የሚመራው ወንድም የሚሰጣቸው ሐሳቦች የተመጠኑ መሆን አለባቸው። ሌሎች ምን ትምህርት እንዳገኙ ሲናገሩ በትኩረት አዳምጡ፤ ምክንያቱም ይህ እምነታችሁን ያጠነክርላችኋል።
5 ተስፋችሁን ለሌሎች ግለጹ፦ በጥናቱ ወቅት አዘውትራችሁ ሐሳብ ትሰጣላችሁን? እጥር ምጥን ያሉ መልሶች ብትሰጡ ይመረጣል። (ከሉቃስ 21:1–4 ጋር አወዳድሩ።) ከልባችሁ ቀላል ሐሳብ ብትሰጡ ሰሚዎች ደስ ይላቸዋል። ብዙውን ጊዜ አንድ ጥያቄ ተጠይቆ መጀመሪያ የሚሰጠው መልስ አጭርና ቀጥተኛ መሆን አለበት። እንደዚህ ከተደረገ ሌሎች በጥቅሶች ላይ ሐሳብ እንዲሰጡ ወይም በአንቀጹ ውስጥ ያሉ ዝርዝር ጉዳዮችን እንዲጠቅሱ ያስችላቸዋል። በዚህ መንገድ ብዙዎቹ ተስፋቸውን በሌሎች ፊት ሊገልጹ ይችላሉ። የሚሰጧቸው ሐሳቦች ምንጊዜም አዎንታዊና ገንቢ መሆን ይኖርባቸዋል።
6 በጥናቱ ላይ ገና መገኘት መጀመርህ ከሆነ ወይም መልስ ለመስጠት የምትፈራ ከሆነ ጥናቱን የሚመራው ወንድም እንዲረዳህ ልትጠይቀው ትፈልግ ይሆናል። አንድ አንቀጽ ላይ ሲደርስ እጅህን እንደምታወጣ ነግረህ እርሱም ይህን እንዲከታተል ጠይቀው። ምናልባትም ጥቅስ አውጥተህ ለማንበብና ትርጉሙ ከትምህርቱ ጋር እንዴት እንደሚያያዝ ለማብራራት ፈቃደኛ ልትሆን ትችላለህ። ሐሳብ በምትሰጥበት ጊዜ ምን ለማለት እንደፈለግህ ለማስታወስ በኅዳጉ ላይ ጥቂት ማስታወሻ መጻፍ ትችላለህ። ልጅ ከሆንክ ደግሞ የምትሰጠውን ሐሳብ በደስታ እንደሚሰሙ አስታውስ። — ማቴ. 21:16
7 እምነታችንን ለሌሎች መግለጻችን በጣም አስፈላጊ ነው። እንዲህ ለማድረግም የመጠበቂያ ግንብ ጥናት አጋጣሚውን ይከፍትልናል። ሐሳብ ለመስጠት የምታመነታ ከሆነ ችግሩን ለመወጣት የምትችለውን ሁሉ አድርግ፤ ቢያንስ ቢያንስ አንድ መልስ እንኳን ለመስጠት ጣር። እንዲህ ስታደርግ ለስብሰባው አስተዋጽኦ ታደርጋለህ፤ ይህን በማድረግህም ትደሰትበታለህ። ታዲያ በዚህ ሳምንት በሚደረገው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ አንድ መልስ ለመስጠት ለምን ካሁኑ አታስብበትም? — ምሳሌ 15:23