ግንባር ቀደም ሆነው የሚያገለግሉ የበላይ ተመልካቾች—የመጠበቂያ ግንብ ጥናት መሪ
1 የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለእኛ “በጊዜው” መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ የሚጠቀምበት ዋነኛ ዝግጅት ነው። (ማቴ. 24:45) የመጠበቂያ ግንብ ጥናቱን የሚመራው ሽማግሌ በክርስቲያናዊ አኗኗር ግሩም አርአያ የሚሆን ብቃት ያለው አስተማሪ በመሆን ረገድ ከባድ ኃላፊነት ተጥሎበታል።—ሮሜ 12:7፤ ያዕ. 3:1
2 የመጠበቂያ ግንብ ጥናት መሪው ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተማር በየሳምንቱ ልባዊ ጥረት የታከለበት ዝግጅት ማድረግ አለበት። ይህንም የሚያደርገው በትጋትና በጥንቃቄ ነው። ጉባኤውን ለመጥቀም ያለው ከፍተኛ ጉጉት በሚጠናው ጽሑፍ አማካኝነት ልባችንን ለመንካት በሚያደርገው ልባዊ ጥረት ይንጸባረቃል። ትምህርቱ በያዛቸው ዓበይት ነጥቦች ላይ ትኩረት በማድረግ ከጥናቱ ጭብጥ ጋር ምን ዝምድና እንዳላቸው እንድናስተውል ይረዳናል።
3 በግሉ የሚያደርገው ጥልቀት ያለው ዝግጅት ጥቅሶች የተጠቀሱበትን ዓላማ ለማወቅ አስቀድሞ ማንበብን ያጠቃልላል። በጥናቱ ወቅት ጉባኤው በመጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ አድርጎ እንዲጠቀም በማበረታታት ለአምላክ ቃል ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል። ተሰብሳቢዎች በሚሰጡት ሐሳብ ላይ አንድ አስፈላጊ ነጥብ ሳይጠቀስ ከታለፈ ወይም አንድ ቁልፍ የሆነ ጥቅስ በተጠቀሰበት ምክንያት ላይ ትኩረት ካልተደረገ ነጥቡ እንዲጠቀስ ሲል በዚያ ላይ የሚያተኩር ተጨማሪ ጥያቄ ያቀርባል። እንዲህ በማድረግ ትክክለኛ መደምደሚያዎች ላይ እንድንደርስና የምንማራቸውን ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ ሥራ ላይ ማዋል የምንችልበትን መንገድ እንድንገነዘብ ይረዳናል።
4 የመጠበቂያ ግንብ ጥናት መሪው የማስተማር ችሎታውን ለማሻሻል የማያቋርጥ ጥረት ያደርጋል። በራሳችን አባባል፣ በአጭሩና ቀጥተኛ የሆነ መልስ እንድንሰጥ ያበረታታናል እንጂ እሱ ራሱ ብዙ ሐሳብ አይሰጥም። በአንድ አንቀጽ ላይ ለቀረበው ጥያቄ የመጀመሪያውን ሐሳብ የሚሰጠው ሰው አጭርና ቀጥተኛ መልስ መስጠት እንዳለበት አልፎ አልፎ ሊያሳስበን ይችላል። አድማጮች የሚሰጧቸው ተጨማሪ ሐሳቦች ጥቅሱ የተጠቀሰበትን ዓላማ የሚገልጹ፣ ነጥቡን የሚደግፉ ወይም ትምህርቱ ተግባራዊ ስለሚሆንበት መንገድ የሚገልጹ ሐሳቦች ሊሆኑ ይችላሉ። የመጠበቂያ ግንብ ጥናት መሪው በግልና በቤተሰብ መልክ እንዲዘጋጁ በማበረታታት እያንዳንዱ ሰው ተሳትፎ ለማድረግ ያለውን ፍላጎት ለማነቃቃት ይጥራል።
5 ‘ከይሖዋ የተማርን ሰዎች’ እንደመሆናችን መጠን የመጠበቂያ ግንብ ጥናት መሪዎች የመሳሰሉትን “በማስተማር የሚደክሙ” ‘የወንድ ስጦታዎችን’ እናደንቃለን።—ኢሳ. 54:13፤ ኤፌ. 4:8, 11፤ 1 ጢሞ. 5:17