ለአገልግሎት ስብሰባ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
1. የአገልግሎት ስብሰባ ዓላማ ምንድን ነው? ከስብሰባው ይበልጥ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
1 የአገልግሎት ስብሰባ በአገልግሎት ውጤታማ እንድንሆን እኛን ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። የአገልግሎት ስብሰባ በዋነኝነት የሚያተኩረው የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ፣ ደቀ መዛሙርት በማድረግና አምላክ በቅርቡ የሚያመጣውን የፍርድ እርምጃ በማወጅ ላይ ነው። (ማቴ. 28:20፤ ማር. 13:10፤ 2 ጴጥ. 3:7) አስፈላጊ ከሆነው ከዚህ ስብሰባ ይበልጥ ጥቅም ማግኘት የምንችለው በደንብ ስንዘጋጅና ተሳትፎ ስናደርግ ነው።
2. አንድን ንግግር ለመስማት መዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው?
2 ንግግር፦ ለተናጋሪው በሚሰጠው መመሪያ ላይ አንድ ንግግር ከምን ላይ መቅረብ እንዳለበት የሚገልጽ ሐሳብ ይሰጣል። ንግግሩ የሚመሠረትበትን ጽሑፍና በጽሑፉ ላይ ያሉትን ጥቅሶች በሙሉ ማንበብ እንዲሁም ትምህርቱን በአገልግሎት ላይ እንዴት ተግባራዊ እንደምታደርግ ማሰላሰል ትችላለህ።
3. በጥያቄና መልስ ለሚቀርቡ ክፍሎች ለመዘጋጀት ምን ማድረግ እንችላለን?
3 በጥያቄና መልስ የሚቀርብ ውይይት፦ ይህ ክፍል በአብዛኛው የሚቀርበው መጠበቂያ ግንብ በሚጠናበት መንገድ ሲሆን አጠር ያለ መግቢያና መደምደሚያ ይኖረዋል። ይህን ክፍል ስትዘጋጅ በእያንዳንዱ አንቀጽ ውስጥ በሚገኙ ቁልፍ ነጥቦች ላይ አስምር፤ እንዲሁም አጠር ያለና ትርጉም ያለው ሐሳብ ለመስጠት ተዘጋጅ።
4. ከአድማጮች ጋር በሚደረግ ውይይት የሚቀርቡ ክፍሎችን መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
4 ከአድማጮች ጋር የሚደረግ ውይይት፦ ይህ ክፍል መቅረብ ያለበት በንግግር ነው፤ ሆኖም ተናጋሪው አልፎ አልፎ አድማጮች ሐሳብ እንዲሰጡ ይጋብዛል። በምትዘጋጅበት ጊዜ ቁልፍ በሆኑ ነጥቦች ላይ ካሰመርክ እንዲሁም ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተሰጡ ጥቅሶችን ካነበብክ ጥያቄ በሚጠየቅበት ጊዜ ሐሳብ መስጠት ትችላለህ። ይህን ክፍል የሚያቀርበው ወንድም አድማጮች በዋና ዋና ነጥቦች ላይ ሐሳብ እንዲሰጡ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል።
5. ከሠርቶ ማሳያዎች ይበልጥ ጥቅም ለማግኘት ምን ሊረዳን ይችላል?
5 ሠርቶ ማሳያዎች፦ አንዳንድ ክፍሎች ሲቀርቡ ውይይት የተደረገበት ነጥብ በአገልግሎት ክልሉ ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ለመጠቆም ሲባል ሊያጋጥሙ የሚችሉ ነገሮችን የሚያሳዩ ሠርቶ ማሳያዎች እንዲካተቱ ይደረጋል። ሠርቶ ማሳያዎቹን ሽማግሌዎች፣ ተሞክሮ ያላቸው አስፋፊዎች ወይም አቅኚዎች እንዲያቀርቧቸው ማድረግ ይቻላል። እንዲህ ያሉ ክፍሎችን ስትዘጋጅ ሠርቶ ማሳያዎቹ እንዴት ሊቀርቡ እንደሚችሉ አስቀድመህ ብታስብ ጥሩ ነው። ሠርቶ ማሳያዎቹ በሚቀርቡበት ጊዜ ደግሞ ሐሳቡን እንዴት አድርገህ በራስህ አባባል እንደምትናገረው እንዲሁም እንደ ቤቱ ባለቤት ሁኔታ በመግቢያው ላይ ምን ማስተካከያ እንደምታደርግ አስብ። ለሠርቶ ማሳያው የሚያስፈልገውን ጽሑፍ ወይም መጽሔት ይዘህ መሄድ እንዳለብህ አትዘንጋ። የቤተሰብ አምልኮ በምታደርጉበት ምሽት በአንዳንድ አቀራረቦች ላይ ልምምድ ማድረጋችሁ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
6. ለአገልግሎት ስብሰባ እንድንዘጋጅ የሚገፋፉን አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
6 የአገልግሎት ስብሰባ ይበልጥ አስደሳች የሚሆንልን ስንዘጋጅና በስብሰባው ላይ ለምናገኘው ግሩም ትምህርት ጉጉት ሲያድርብን ነው። ከላይ የተጠቀሱትን ሐሳቦች ተግባራዊ ማድረጋችን እርስ በርሳችን ይበልጥ እንድንበረታታ ያስችለናል። (ሮም 1:11, 12) ለአገልግሎት ስብሰባ ጊዜ መድበን የምንዘጋጅ ከሆነ የተሰጠንን ተልእኮ ለመወጣት የተሻለ ብቃት ያለን እንሆናለን።—2 ጢሞ. 3:17