ውድ ሀብት የሆነውን የመንግሥት አገልግሎትህን አስፋው
1 ኢየሱስ የመንግሥቱን ተስፋ ዋጋ ከማይተመንለት ሀብት ጋር አመሳስሎታል። (ማቴ. 13:44-46) በኢየሱስ ምሳሌዎች ላይ እንደተጠቀሱት አንድ ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ነገር ለማግኘት ሲሉ ንብረታቸውን ሁሉ እንደ ሸጡት ዓይነት ሰዎችን ነንን? እንዲህ ከሆነ ምንም እንኳን አስቸጋሪና የራስን ጥቅም መሠዋትን የሚጠይቅ ቢሆንም ለአምላክ መንግሥት አንደኛ ቦታ እንሰጣለን።—ማቴ. 6:19-22
2 የመንግሥት አገልግሎታችን ውድ ሀብት ስለሆነ ይህን ሀብታችንን የማስፋት ጉጉት ሊኖረን ይገባል። የግል አኗኗራችን የሚያሳየው ምንድን ነው? የመንግሥት አገልግሎት እንቅስቃሴአችንን እያሰፋን ነውን? ከቤት ወደ ቤት እንደ ማገልገል፣ ተመላልሶ መጠየቅ እንደ ማድረግ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እንደ መምራትና መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንደ መመሥከር ባሉት ልዩ ልዩ የአገልግሎት ዘርፎች በመሳተፍ አገልግሎታችንን ልናሰፋው እንችላለን።
3 ‘ተሳትፎዬን ከፍ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?’ አዲሱ የአገልግሎት ዓመት ሲጀምር በመስክ አገልግሎት የሚያሳልፈውን ጊዜ ከፍ ማድረግ እንዲችል እያንዳንዱ ሰው የግል እንቅስቃሴውን ቢመረምርና እንዲህ በማለት ራሱን ቢጠይቅ ጥሩ ነው፦ ‘አልፎ አልፎ ወይም ከተቻለ ላልተወሰነ ጊዜ ረዳት አቅኚ ለመሆን ሲባል ጉዳዮቼን ማደራጀት እችላለሁን? ጥቂት ማስተካከያዎችን በማድረግ የዘወትር አቅኚነት ግብ ላይ ለመድረስ እችላለሁን?’ በመስከረም 1 ዘወትር አቅኚነትን የጀመሩ አዲስ አቅኚዎች በሚቀጥለው ዓመት በሚደረገው የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት ለመካፈል ብቁ ይሆናሉ።
4 አንዳንድ አስፋፊዎች በተሻለ ሁኔታ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር ግብ ያወጣሉ። ብዙውን ጊዜ ይህ የአገልግሎት ዘርፍ ግሩም ፍሬ ያስገኛል። ሌሎች አስፋፊዎች ውጤታማ ተመላልሶ መጠየቆችን በማድረግ ወይም አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በማስጀመር ረገድ ያላቸውን ችሎታ ማሻሻል እንደሚያስፈልጋቸው ይሰማቸው ይሆናል። አንዳንዶች ደግሞ መጽሔት የሚያበረክቱበትን ቀን መድበዋል። በመስክ አገልግሎት ቦርሣቸውም በየወሩ የሚያበረክቱትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ጽሑፎችን ለመያዝ አቅደዋል።
5 አገልግሎታችንን ስንገመግም በአንዱ በኩል ውስን እንደሆነ ከተሰማን እንዴት ልናሰፋው እንችላለን? ከፍ ያሉ ግቦችን አውጥተው የተሳካላቸው ወንድሞች ምንም ዓይነት መሥዋዕትነት ቢጠይቅብንም የመንግሥቱን ፍላጎቶች ለማስቀደም በመጀመሪያ ደረጃ ቁርጥ ውሳኔ እንድናደርግ ይመክሩናል። (ማቴ. 6:33) እምነትና በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መደገፍ አስፈላጊ ነው። (2 ቆሮ. 4:7) ሳታቋርጥ ከልብ በመጸለይ የይሖዋን እርዳታ አጥብቀህ ፈልግ። (ሉቃስ 11:8, 9) ይሖዋ በአገልግሎቱ ያለንን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ የምናደርጋቸውን ልባዊ ጥረቶች እንደሚባርክልን ልንተማመን እንችላለን።—1 ዮሐ. 5:14
6 አገልግሎታቸውን ለማስፋት ከተሳካላቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር ተነጋገሩ። ተስፋ የሚያስቆርጡ መሰናክሎችን እንዴት ሊወጡ እንደቻሉ ጠይቋቸው። አገልግሎትህን ከፍ ማድረግ የምትችል መሆኑን ለማመን የግል ተሞክሯቸው ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል።
7 በመጠበቂያ ግንብ ወይም በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የመስክ አገልግሎትን የሚመለከቱ ትምህርቶችን ስታነብ የተሰጡትን ሐሳቦች በአገልግሎትህ እንዴት ልትሠራባቸው እንደምትችል በጸሎት በጥንቃቄ መርምር። በጉባኤ ስብሰባዎች ወይም በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ስትገኝም እንዲሁ አድርግ። በዚህ ርዕስ ላይ የቀረቡት ሐሳቦች ባለፈው ዓመት በክልል ስብሰባ ፕሮግራም ላይ የተሰጠውን ማብራሪያ የተመረኮዙ ናቸው። በዚያ ፕሮግራም ላይ የቀረበውን ማበረታቻ በሥራ ላይ ለማዋል እንዲረዱን ከተዘጋጁት ተከታታይ ትምህርቶች መካከል የመጀመሪያው ይህ ነው።
8 ኢየሱስ አገልግሎቱን እንደ ከፍተኛ ቁም ነገር አድርጎ በመመልከት አንደኛ ቦታ ይሰጠው ነበር። እንዲህ አለ፦ “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው።” (ዮሐ. 4:34) እኛስ እንደዚህ ይሰማናልን? ከሆነ ተሳትፏችንን ከፍ ለማድረግና ካካበትነው ሀብት ውስጥ ብዙ “መልካም ነገሮች” ለሌሎች ለማካፈል ብዙ መንገዶችን እንፈልጋለን።—ማቴ. 12:35፤ ሉቃስ 6:45