ዘወትር የምስጋናን መሥዋዕት በማቅረብ የአምላክን መንግሥት አስቀድሙ
1 የአምላክን መንግሥት አስቀድመው የሚፈልጉ ሁሉ ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ መናገርን አይዘነጉም። (መዝ. 145:11–13) በየቀኑ ስሙን ለመባረክና ምሥራቹን ለመናገር ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። (መዝ. 96:2) “ቀኑን ሙሉ በአምላክ ውዳሴ እናቀርባለን” በማለት የተናገረው መዝሙራዊ ይሖዋን ማወደስ ያስደስተው ነበር። (መዝሙር 44:8 አዓት) እኛም ተመሳሳይ ስሜት ካለን ዘወትር በመንግሥቱ አገልግሎት ለመሳተፍ እንጓጓለን።
2 ይሖዋ ምን ያህል ጊዜ በአገልግሎት እንደምናሳልፍ የተወሰነ ጊዜ አልመደበም፤ ይሁን እንጂ “ዘወትር” እንድናወድሰው ያበረታታናል። (ዕብ. 13:15) ሁኔታችን የሚፈቅድልን ከሆነ በየሳምንቱ የተወሰነ ጊዜ ይሖዋን በማወደስ ለማሳለፍ ግብ ማውጣት አለብን። ይህን ያደረጉ ጉዳዮቻቸውን አስተካክለው አልፎ አልፎ ወይም ከተቻለ ላልተወሰነ ጊዜ በረዳት አቅኚነት ሊካፈሉ ይችላሉ። በረዳት አቅኚነት የተካፈሉ አንዳንዶች በዘወትር አቅኚነት ሊሰለፉ ይችሉ ይሆናል።
3 ሁኔታችን ምንም ይሁን ምን የውዳሴ መሥዋዕታችንን ከፍ ለማድረግ እንችላለንን? አድናቆት ቀናተኛ ያደርጋል። የአምላክን ቃል በግል ማጥናት አድናቆትን ይገነባል። የጉባኤ ስብሰባዎች ይህን አድናቆት ተግባራዊ በሆነ መንገድ እንድንገልጽ ይገፋፉናል። ይሖዋን በቅንአት ከሚያወድሱት ጋር በቅርብ እየተገናኘን መሥራታችን ‘ለመልካም ሥራ ያነቃቃናል።’ (ዕብ. 10:24) በጉባኤ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ በመጠቀም የውዳሴ መሥዋዕታችንን ከፍ ማድረግ እንችል ይሆናል።
4 ነብይቷ ሐና በይሖዋ አገልግሎት ጥሩ ምሳሌ የምትሆን ነበረች። የ84 ዓመት አረጋዊት ብትሆንም “እያገለገለች ከቤተ መቅደስ አትለይም ነበር።” (ሉቃስ 2:37) በጉባኤው ተግባራት በሙሉ ልብ ታደርግ የነበረው ተሳትፎ እርካታ እንድታገኝ አስችሏት ነበር። በታማኝነት ታከናውን ስለ ነበረው አገልግሎቷ የሚተርከው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በዛሬው ጊዜ እኛን ያበረታታናል።
5 ጳውሎስ ‘እኛ ኃይለኛ የሆንን የደካሞችን ድካም ልንሸከም ይገባል’ ሲል መክሯል። (ሮሜ 15:1) በጉባኤህ ውስጥ አንተ ከምትሰጣቸው የደግነት እርዳታና ማበረታቻ ሊጠቀሙ የሚችሉ አንዳንዶች ሊኖሩ ይችላሉ። የሚያስፈልገው ነገር አብረውህ እንዲያገለግሉ መጋበዝ ብቻ ይሆን ይሆናል። አንድ አስፋፊ ለትራንስፖርት የሚከፍልለት ወይም አብሮት የሚያገለግል የአገልግሎት ጓደኛ ያስፈልገው ይሆናል። ሌላው ደግሞ አንድ ችግር ተስፋ አስቆርጦት ሊሆንና ግለሰቡ ለመንግሥቱ አገልግሎት የነበረውን ቅንዓት የሚያድስ ገንቢ ድጋፍ ልትሰጠው የምትችለው አንተ ትሆን ይሆናል። (1 ተሰ. 5:14) ‘ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው ለመርዳት’ የምታሳየው ፈቃደኝነት ለይሖዋ ስም የምታቀርበውን ውዳሴ ከፍ ለማድረግ ያለህን ልባዊ ምኞት ያሳያል። — ሮሜ 12:13
6 ይሖዋ እስካሁን ያደረገልንንና ወደፊት የሚያደርግልንን ነገሮች ቆጥረን መጨረስ አንችልም። ለእነዚህ በረከቶች ወሮታውን አሟልተን ልንከፍል የምንችልበት አንዳችም መንገድ የለም። ይህም ‘እስትንፋስ ያለው ሁሉ ይሖዋን እንዲያወድስ’ የሚያስገድድ እንዴት ያለ ምክንያት ነው!— መዝ 150:6 አዓት