በየቀኑ ይሖዋን አወድሱ
1. የአምላክ አገልጋዮች ምን ለማድረግ ተነሳስተዋል? ለምንስ?
1 ንጉሥ ዳዊት “በየቀኑ” ሌላው ቀርቶ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሖዋን ለማወደስ ያደረገውን ቁርጥ ውሳኔ ገልጿል። (መዝ. 145:2, 7, 21) እኛም ይሖዋን በየቀኑ ለማወደስ የሚያበቃ አጥጋቢ ምክንያት አለን።—መዝ. 37:10፤ 145:14, 18፤ 2 ጴጥ. 3:13
2. ቤተሰቦች በየቀኑ ይሖዋን ማወደስ የሚችሉት እንዴት ነው?
2 በቤታችን፦ የዕለት ጥቅስና የቤተሰብ አምልኮ በምናደርግበት እንዲሁም ለጉባኤ ስብሰባዎች በምንዘጋጅበት ጊዜ ትርጉም ያለው መንፈሳዊ ውይይት እንድናደርግ የሚያስችሉን የሚያንጹ ጽሑፎች አሉን። ብዙ ቤተሰቦች በቀን ቢያንስ አንድ ጊዜ አብረው የመመገብ ልማድ አላቸው። ይህ አጋጣሚ ሳይጣደፉ ዘና ብለው ጭውውት እንዲያደርጉና ይሖዋን እንዲያወድሱ ያስችላቸዋል። ወላጆች እንዲህ ባለው አጋጣሚ ላይ የሚያንጽ ጭውውት ማንሳታቸው “በይሖዋ ተግሣጽ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ በውስጣቸው በመቅረጽ” ልጆቻቸውን ለማሳደግ በእጅጉ ይረዳቸዋል።—ኤፌ. 6:4፤ ዘዳ. 6:5-7
3. ከወንድሞቻችን ጋር ስንሆን ምን ለማድረግ አጋጣሚ እናገኛለን?
3 ከወንድሞቻችን ጋር ስንሆን፦ በመስክ አገልግሎት ወይም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስንሆን ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ሆነን ይሖዋን የማወደስ ግሩም አጋጣሚ እናገኛለን። (ምሳሌ 15:30፤ ፊልጵ. 4:8፤ ዕብ. 13:15) ሁላችንም ይሖዋን ስለምንወድ በጭውውታችን መሃል ስለ ይሖዋ ቸርነት አንስተን ከልብ በመነጨ የአድናቆት ስሜት መናገር ከባድ ሊሆንብን አይገባም።—መዝ. 106:1
4. ይሖዋን ለማወደስ የሚያስችሉን ሌሎች አጋጣሚዎች የትኞቹ ናቸው?
4 ከማያምኑ ሰዎች ጋር ስንሆን፦ በመስክ አገልግሎት በየቀኑ ለመካፈል ሁኔታችን ባይፈቅድልንም እንኳ ከሥራ ባልደረቦቻችን፣ አብረውን ከሚማሩ ልጆች እንዲሁም ከሌሎች ሰዎች ጋር ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማው አጠር ያለ ውይይት ማድረጋችን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በተስፋ እንዲሞሉ ሊያደርግ ይችላል። (መዝ. 27:14፤ 1 ጴጥ. 3:15) አንዲት እህት በአውሮፕላን ስትጓዝ አጠገቧ ለተቀመጠች ሴት መሠከረችላት፤ ሴትየዋም ከውይይቱ ማጽናኛና ማበረታቻ በማግኘቷ ከእህት ጋር ሌላ ጊዜ ተገናኝታ ለመወያየት አድራሻዋንና የስልክ ቁጥሯን ሰጠቻት። ችግሮች በተባባሱበትና ሁኔታዎች እየከፉ በመጡበት በዚህ ዓለም፣ የይሖዋ ሕዝቦች ሰሚ ጆሮ ላላቸው ሰዎች “መልካም ዜና” ማብሰራቸውን ቀጥለዋል። ይህም እነዚህ ሰዎች ተስፋቸው እንዲለመልምና እነሱም ይሖዋን ለማወደስ እንዲነሳሱ ያደርጋል።—ኢሳ. 52:7፤ ሮም 15:11
5. ይሖዋን ለማወደስ የምንፈልገው ለምንድን ነው? ይህን ማድረጋችንስ ምን ውጤት ያስገኛል?
5 ይሖዋ አገልጋዮቹ በየቀኑ እሱን ሲያወድሱ መስማቱ በጣም እንደሚያስደስተው ምንም ጥርጥር የለውም! በዙሪያችን እንዳሉት የይሖዋ ፍጥረታት ሁሉ እኛም በቤታችንና በጉባኤ ስንሆን እንዲሁም ገና ይሖዋን ማወደስ ካልጀመሩ ሰዎች ጋር ስንጨዋወት በየቀኑ እሱን ማወደስ እንችላለን።—መዝ. 19:1-4