ምን ዓይነት መንፈስ ታሳያላችሁ?
1 ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለሚገኘው ጉባኤ የጻፈውን ደብዳቤ በዚህ ጥብቅ ማሳሰቢያ ደመደመ:- “ይገባናል የማንለው የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግነት ከምታሳዩት መንፈስ ጋር ይሁን።” (ፊልጵ. 4:23 አዓት) ምሥራቹን ለመስበክ ስለነበራቸው ልባዊ ፍላጎትም ሆነ አንዱ ለሌላው ደኅንነት ላሳየው ሞቅ ያለ ፍቅራዊ አሳቢነት አመሰገናቸው።— ፊልጵ. 1:3–5፤ 4:15, 16
2 በጉባኤያችንም ተመሳሳይ መንፈስ ለማንጸባረቅ መፈለግ አለብን። ሁሉም ቅንዓትን፣ ደግነትንና እንግዳ ተቀባይነትን ሲያሳዩ ተመልካቾች ይህን ሁኔታ በግልጽ ይመለከታሉ። አዎንታዊና ፍቅራዊ የሆነ መንፈስ አንድነትና መንፈሳዊ እድገት ያስገኛል። (1 ቆሮ. 1:10) አሉታዊ መንፈስ ግን ተስፋ መቁረጥንና በግማሽ ልብ መሥራትን ያስከትላል። — ራእይ 3:15, 16
3 ሽማግሌዎች ቀዳሚ ይሆናሉ፦ ሽማግሌዎች በመካከላቸውና በጉባኤው ውስጥ ጥሩ የሆነ አዎንታዊ መንፈስ እንዲኖር የማድረግ ኃላፊነት አላቸው። ለምን? ምክንያቱም ጉባኤው እነርሱ በሚያሳዩት መንፈስና ጠባይ ሊነካ ስለሚችል ነው። በመስክ አገልግሎት ቀናተኛ የሆኑ፣ ሞቅ ባለ ፈገግታና ደግነት በታከለበት ቃል ሰላም የሚሉን እንዲሁም በግልም ሆነ ከመድረክ አዎንታዊና የሚገነባ ምክር በሚሰጡ ሽማግሌዎች ደስ ይለናል። — ዕብ. 13:7
4 እርግጥ ጉባኤው የወዳጅነት መንፈስ የሚያንጸባርቅ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ቀናተኛና መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያለው እንዲሆን ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽዖ ማድረግ አለብን። በግላችን ከሌሎች ጋር በመቀራረብ ሞቅ ያለ ስሜትና ፍቅር ልናሳይ እንችላለን። (1 ቆሮ. 16:14) በመካከላችን በዕድሜ፣ በዘር፣ በትምህርት ደረጃ ወይም በሀብት ልዩነት የመፍጠር አዝማሚያ መኖር የለበትም። (ከኤፌሶን 2:21 ጋር አወዳድር።) ባለን ተስፋ ምክንያት የደስታ፣ በልግስና እንግዳ የመቀበልና በአገልግሎት ቀናተኛ የመሆን መንፈስ ልናሳይ እንችላለን። — ሮሜ 12:13፤ ቆላ. 3:22, 23
5 አዲሶችን ጨምሮ ከእኛ ጋር የሚሰበሰቡ ሁሉ ጥሩ መስተንግዶ እንደተደረገላቸው እንዲረዱና የወንድማማችነትን ፍቅርና አድናቆት እንዲሰማቸው ሊደረግ ይገባል። በአገልግሎታችንና ጥሩ መንፈሳዊ ባሕርያትን በማንጸባረቅ ጉባኤው “የእውነት አምድና ድጋፍ” መሆኑን እናረጋግጣለን። (1 ጢሞ. 3:15 አዓት) በተጨማሪም ልባችንንና የማሰብ ኃይላችንን በሚጠብቅ “የእግዚአብሔር ሰላም” አማካኝነት መንፈሳዊ መረጋጋት እናገኛለን። (ፊልጵ. 4:6, 7) በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ይገባናል የማንለውን የይሖዋን ደግነት የሚያተርፍልን መንፈስ ለማሳየት ሁላችንም በትጋት እንጣር። — 2 ጢሞ. 4:22 አዓት