ከሌሎች ጋር በማገልገል የሚገኙ በረከቶች
1 ከሌሎች ጋር በማገልገል የሚገኙ ጥቅሞች እንዳሉ ይሰማሃልን? ኢየሱስ እንደዚያ ይሰማው ነበር። ምንም እንኳን መከሩ ብዙ፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ቢሆኑም 70 ደቀ መዛሙርቱን ‘ሁለት ሁለት አድርጎ’ ወደ መስኩ ላካቸው። “እርሱ ሊሄድበት ወዳለው ከተማና ስፍራ ሁሉ” በመስበካቸው ሁሉም በውጤቱ እንዴት ረክተው ነበር! — ሉቃስ 10:1, 17፤ ማቴ. 9:37
2 ከሌሎች ጋር ማገልገል ያነቃቃል። አንዳንዶቻችን ዓይነ አፋር ስለሆነን የማናውቃቸውን ሰዎች ማነጋገር ይከብደናል። ሌላ ሰው ከጎናችን መኖሩ የአምላክን ቃል በድፍረት ለመናገር የሚያስችል የመተማመን ስሜት ያሳድርብን ይሆናል። ሌላ ሰው አብሮን ሲሆን አገልግሎታችንን በሠለጠንበት መንገድ ለማከናወን ቀላል ሊሆንልን ይችላል። (ምሳሌ 27:17) ጠቢቡ “አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል” ብሏል።— መክ. 4:9
3 ከተለያዩ አስፋፊዎችና አቅኚዎች ጋር ማገልገል ጥሩ ነው። ከሐዋርያው ጳውሎስ የአገልግሎት ጓደኞች መካከል በርናባስ፣ ሲላስ፣ ጢሞቴዎስና ዮሐንስ ማርቆስ ይገኙበታል፤ አንድ ላይ ሲሰብኩም ብዙ በረከቶችን አግኝተዋል። ዛሬም ያው ነው። በእውነት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ከቆየ ወንድም ጋር አገልግለህ ታውቃለህን? ምሥክርነት የሚሰጥበትን ዘዴ ከተመለከትክ በኋላ አገልግሎትህን ለማሻሻል የሚረዱህን አንዳንድ ጥሩ ሐሳቦች አግኝተህ ይሆናል። ከሌሎች ጋር ሲነጻጻሩ አዲስ ከሆኑ አስፋፊዎች ጋር ታገለግላለህን? አገልግልህ ከነበረ የምታውቃቸውን አንዳንድ ነገሮች በማካፈል በአገልግሎታቸው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑና እንዲደሰቱ ልትረዳቸው ችለህ ይሆናል።
4 በአሁኑ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየመራህ ነውን? ታዲያ ከሽማግሌዎች አንዱን ወይም የክልል የበላይ ተመልካቹን አብሮህ እንዲያስጠና ለምን አትጋብዘውም? ተማሪዎቻችን ከበላይ ተመልካቾች ጋር መተዋወቃቸው ጠቃሚ ነው። ሽማግሌ እያለ ማስጠናት ካልፈለግህ ምናልባት ጥናቱን እሱ ለመምራትና እንድታይ ለማድረግ ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል። ከጥናቱ በኋላ ተማሪው በፍጥነት እንዲያድግ እንዴት ልትረዳው እንደምትችል አንዳንድ ሐሳቦችን እንዲሰጥህ ለመጠየቅ ነፃነት ይሰማህ።
5 ከሌሎች ጋር ስታገለግል የምታበረታታ የአገልግሎት ጓደኛ ሁን። ስለ አገልግሎት ክልሉ የምትሰጠው አስተያየት ገንቢ ይሁን። በጭራሽ ሌሎችን የሚጎዳ ሐሜት አትናገር ወይም የጉባኤውን አሠራር አትንቀፍ። አእምሮህ በአገልግሎቱና ከይሖዋ በሚገኙት በረከቶች ላይ እንዲያተኩር አድርግ። ይህን ካደረግህ አንተም ሆነ የአገልግሎት ጓደኛህ በመንፈሳዊ ታድሳችሁ ወደ ቤት ትመለሳላችሁ።
6 ሁኔታህ ከሌሎች ወንድሞችና እኅቶች ጋር ዘወትር እንድታገለግል አይፈቅድልህ ይሆናል። ሆኖም ከቻልክ ከሌላ አስፋፊ ጋር ለማገልገል ለምን እቅድ አታወጣም? ሁለታችሁም ትባረካላችሁ። — ሮሜ 1:11, 12