የሚያስፈልግ ነገር እንዳለ ትመለከታለህን?
1 ይሖዋ ረዳትና መጠጊያ እንደሆነ ተገልጿል። እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ እርሱን ልንጠይቅ እንደምንችልና እርሱም እንደሚረዳን እናውቃለን። (መዝ. 18:2፤ 46:1) እኛም ሌሎች ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር በመረዳት ይህንን የደግነት ባሕርይ ልንኮርጅ እንችላለን።
2 አንድ ሰው ሌሎችን በመርዳት ረገድ ልዩ ጥረት እንዲያደርግ የሚገፋፋው ምንድን ነው? አብዛኞቹ ሰዎች እንዲህ ማድረግ ከፍቅር የሚመነጭ ሰብአዊ ተግባር እንደሆነ ይገነዘባሉ። የአምላክ ቃልም ይህንን ያበረታታል። (ሮሜ 15:1) ጳውሎስ ‘የራሳችንን የግል ጥቅምና ፍላጎት ብቻ እንዳንመለከት ከዚህ ይልቅ የሌሎችንም ጥቅም እንድናስብ’ አጥብቆ መክሮናል።— ፊልጵ. 2:4
3 ሁላችንም ደስታ ለመግኘት የምንችልበት አንዱ መንገድ ይህ ነው። (ሥራ 20:35) ጳውሎስ ስለ ወንድሞቹ ‘ኑሮ ከልብ በመጨነቅ’ ረገድ ወጣቱን ጢሞቴዎስን እንደ ምሳሌ አድርጎ ለይቶ ጠቅሷል። (ፊልጵ. 2:20) በዛሬው ጊዜም በጉባኤዎቻችን ውስጥ ይህን የሚመስል ባሕርይ ያላቸው በርካታ ወጣቶች መኖራቸው የሚያስደስት ነው። ነገር ግን ወጣቶችም ሆንን በዕድሜ የገፋን የሚያስፈልግ ነገር አንዳለ ካስተዋልን ማድረግ የምንችለው ብዙ ነገር አለ።
4 አንዳንዶች የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ችግር እንዳለባቸው ተሰምቶህ ያውቃልን? ምናልባት አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ሆስፒታል ገብተው በነበረበት ጊዜ ሄደው የጠየቋቸው ሰዎች ጥቂት ይሆናሉ፤ ወይም አንድ ሰው አካለ ስንኩል ይሆንና የሚላላከው ወይም በቤት ውስጥ ሥራ የሚያግዘው ሰው የለው ይሆናል። ኢየሱስ ይሖዋን የሚያገለግሉትን ሰዎች እርስ በእርሳቸው ከልብ እንደሚዋደዱ የአንድ ቤተሰብ አባላት አድርጎ ይመለከታቸዋል። (ማር. 3:33–35) ስለ በጎችና ስለ ፍየሎች በሰጠው ምሳሌ ላይ በቀኝ እጁ በኩል የነበሩትና የንጉሡን ሞገስ አግኝተው ሐሴት የሚያደርጉት ለንጉሡ ወንድሞች መልካም ያደረጉት እንደሆኑ ጠቁሟል።— ማቴ. 25:40
5 መርዳት የምችለው እንዴት ነው? እርዳታ ማድረግን የሚጠይቅ አንድ ግልጽ የሆነ ችግር እንዳለ በሚታይበት ጊዜ እርዳታ ለመስጠት ምን ሊደረግ ይቻላል? በሆነ መንገድ እርዳታ ለመስጠት ቅድሚያውን መውሰድ እንችላለንን? ምናልባት በዕድሜ የገፉ ማበረታቻ የሚፈልጉ ነገር ግን ሊረዳቸው የሚችል የቅርብ ዘመድ የሌላቸው ይኖሩ ይሆናል። ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወጣቶችም ይኖሩ ይሆናል። በቅርቡ ጥናት የጀመረ ብዙ ልጆች ያሉት አንድ ቤተሰብ አስጠኚያቸው በሌለበት በመንግሥት አዳራሹ ይገኙ ይሆናል። ልጆቹን በመርዳት በኩል የሚያግዛቸው ፈቃደኛ ሰው በማግኘታቸው ሊያደንቁ ይችላሉ።
6 ለእውነትና ለይሖዋ ድርጅት ያለን አድናቆት እያደገ ሲሄድ በጉባኤ ውስጥ ላሉ ለሌሎች ያለን አድናቆትና አሳቢነትም በዚያው ልክ ያድጋል። ጳውሎስ በዚህ ረገድ ያለንን አሳቢነት እንድናሰፋው አበረታቶናል። (2 ቆሮ. 6:11–13) ኢየሱስ በእርግጥም የእሱ ተከታዮች መሆናችንን የምናሳይበት ዋነኛ መንገድ እርስ በእርሳችን በምናሳየው ፍቅር እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገልጿል።— ዮሐ. 13:35
7 ስለዚህ ችግር እንዳለ ስንመለከት ለወንድሞቻችንና ለጉባኤው ያለን ከልብ የመነጨ ፍቅር በምንችለው መንገድ ሁሉ ድጋፋችንን ለመስጠት ቀዳሚዎች እንድንሆን ሊያነሳሳን ይገባል። (ገላ. 6:9, 10) እንዲህ ያለው ለሌሎች ያለን አሳቢነት በፍቅርና በአንድነት ማሰሪያ እርስ በእርስ ያስተሳስረናል። (1 ቆሮ. 10:24) በዚህ መንገድ በጉባኤው ውስጥ ያለውን ችግር ለመድፈን የበኩላችንን እናደርጋለን።