ፍላጎት ያሳዩትን ሁሉ ተከታትሎ በመርዳት እንዲጠቀሙ ማድረግ
1 ለአንድ ሰው ጽሑፍ ማበርከት እንዳለብንና እንደሌለብን ለመወሰን የሚረዳን ቁልፍ ነገር ምንድን ነው? የሰውዬው ፍላጎት ነው! ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አንድ ሰው ለመንግሥቱ መልእክት ትንሽ እንኳ ፍላጎት ካሳየ ይህንን ሰው ለመጥቀም የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። ስለዚህ ተመላልሶ መጠየቅ የምናደርገው የሰውዬውን ፍላጎት መኮትኮትንና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመርን ግብ በማድረግ ነው። ጽሑፍ ባናበረክትም እንኳ ግባችን ይኸው ነው። ይህንን እንዴት ማከናወን ይቻላል?
2 ባለፈው ጊዜ የተወያያችሁት በጊዜያችን ስለተስፋፉት የትዳር ችግሮች ከሆነና “ለዘላለም መኖር ” የተባለውን መጽሐፍ አበርክተህለት ከነበረ ውይይትህን እንደሚከተለው በማለት ልትጀምር ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው መጥቼ ሳለ ስለ ትዳርና የተሻለ ደስታ እንድናገኝ ስለሚረዱን ተግባራዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ተነጋግረን ነበር። ከሌላው ሁሉ የተሻሉ ናቸው በሚባሉት ቤተሰቦች ውስጥ እንኳ አልፎ አልፎ ችግሮች መነሳታቸው እውነት አይደለምን? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ በቤተሰብ ውስጥ የሚነሱትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችለን ግሩም ምክር ይሰጠናል። አንድ ቤተሰብ መጽሐፍ ቅዱስን አብሮ በማጥናት በረከት ሊያገኝ ይችላል።” ገጽ 246 አውጣና በአንቀጽ 23 ላይ ተወያዩ። ዮሐንስ 17:3ን አንብብና ቤታቸው ሆነው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ቤተሰቡን ለመርዳት ዝግጁ መሆንህን ግለጽላቸው።
3 ስለ ልጆችና ስለሚያስፈልጋቸው ሥልጠና ተነጋግራችሁ ከነበረ ውይይቱን በሚከተለው መንገድ መቀጠል ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ ልጆች ስለሚያስፈልጋቸው መንፈሳዊ ሥልጠናና ወላጆች እንዴት ሊረዷቸው እንደሚችሉ ተነጋግረን ነበር። ያነጋገርኳቸው አብዛኞቹ ወላጆች በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ወጣቶች የሚያሳዩት መጥፎ ጠባይ አሳስቧቸዋል። እርስዎ ስለ . . . ምን ያስባሉ? [በአካባቢያችሁ የተለመደ የወጣቶችን ምግባረ ብልሹነት የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ጥቀስ። መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተሰጡ ሊሠሩ የሚችሉ ምክሮች ውስጥ ጥቂቶቹን ላሳይዎት።” ለዘላላም መኖር በተባለው መጽሐፍ ገጽ 246 የሚገኘውን አንቀጽ 22 አውጥተህ በዋናው ነጥብ ላይ ካወያየኸው በኋላ ኤፌሶን 6:4ን አንብብ። አብዛኞቹ ልጆች ተግሣጽና መመሪያ እንደሚፈልጉ ግለጽ። ወላጆች ይህንን በማድረግ ረገድ ትጉዎች ከሆኑ ልጆች ይበልጥ ደስተኛና ሰው አክባሪ ይሆናሉ። ከልጆቻችን ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደምናጠና ግለጽለት።
4 ቀደም ሲል የተወያያችሁት ስለ ገነቲቱ ምድር ከነበረ ፍላጎቱን እንደገና ለማነሳሳት እንደሚከተለው ማለት ትችላለህ:-
◼ “አምላክ ምድርን ገነት ሲያደርጋት ምን እንደምትመስል የሚያሳዩ ጥቂት ሥዕሎች በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ተመልከተን ነበር። በዚያ የምንወዳቸው ሰዎች የማይገኙ ቢሆን ብዙም አንደሰትም ነበር። በዚህ አይስማሙምን?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ከዚያም ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 162 አውጣ። ራእይ 21:3, 4ን አንብብና የምንወዳቸው ሰዎች ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አብራራለት። ጥሩ ምላሽ ካሳየ የሞቱ ሰዎች እንደሚነሱ ለማሳየት ዮሐንስ 5:28, 29ን አንብብ። የመጽሐፉን ሽፋን አሳየውና እንደዚህ በለው:- “ይህ እውነት መሆኑ አያጠራጥርም። በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር እንችላለን!” ይህ ጊዜ በቅርቡ እንደሚመጣ እንዴት ማወቅ እንደምንችል ለመወያየት ቀጠሮ ያዝ።
5 የተመላልሶ መጠየቅ ዋነኛ ዓላማ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ከመንግሥቱ መልእክት እንዲጠቀሙ መርዳት ነው። አብዛኞቹ ሰዎች ለመንፈሳዊ ነገሮች ያላቸውን ፍላጎት ለመቀስቀስ ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ጽሑፉ መጽሐፍ ቅዱስን በተሻለ ሁኔታ እንዲገነዘቡት ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት እንደሆነ አጽንኦት በመስጠት በጽሑፉ ውስጥ በሚገኙ የተወሰኑ ጠቃሚ ነጥቦች ላይ እንዲያተኩሩ አድርጉ። እነዚህን ግቦች ከዳር የሚያደርሱ ተመላልሶ መጠየቆች ሰዎች ከሁሉ በተሻለው መንገድ ራሳቸውን እንዲጠቅሙ ይረዷቸዋል።