ከ1996 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ጥቅም ማግኘት— ክፍል 2
1 በ1943 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከተጀመረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከማኀበሩ ቅርንጫፎች አንዱ “ይህ ግሩም የሆነ ዝግጅት የሕዝብ ተናጋሪ እንሆናለን ብለው ፈጽመው አስበው የማያውቁ ብዙ ወንድሞች ጥሩ ተናጋሪዎች እንዲሆኑና በመስኩ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ በመርዳት በኩል በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሳካ ውጤት አስገኝቷል” በማለት ሪፖርት አድርጎ ነበር። ትምህርት ቤቱ ለሁላችንም የሚያስፈልገንን ጥሩ ማሠልጠኛ መስጠቱን ቀጥሏል።
2 የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ ከትምህርት ቤቱ የሚጠቀሙት ክፍል የሚያቀርቡት ብቻ አይደሉም። ሳምንታዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የሁላችንም ክፍል ነው። የትምህርት ቤቱ ፕሮግራም በየሳምንቱ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች እንደሚነበቡ ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የማንበብን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርገው የሚገልጹ ብዙ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማሳሰቢያዎች አሉ። (ኢያሱ 1:8 አዓት፤ መዝ. 1:2 አዓት፤ ሥራ 17:11) የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ለጥሩ መንፈሳዊ ጤንነት አስፈላጊ ነው። አእምሮንና ልብን ይመግባል። በየቀኑ ቢያንስ ለአምስት ደቂቃ መጽሐፍ ቅዱስ የምናነብ ከሆነ ከፕሮግራሙ እኩል መራመድ እንችላለን። እንዲህ ካደረግን በአንድ ዓመት ውስጥ ከአምላክ ቃል ከ150 የሚበልጡ ምዕራፎች ማንበብ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ በቅርብ የምንይዝ ከሆነ በየዕለቱ ትንሽ ትንሽ ማንበብ እንችላለን።
3 የመምሪያ ንግግር፦ የመምሪያ ንግግሩን የሚያቀርበው ተናጋሪ ወንድሞች በታማኝነትና በቅንዓት እንዲያገለግሉ ለማነሳሳት ጥሩ የማስተማር ዘዴ መጠቀም፣ ነጥቡን ማስጨበጥ እንዲሁም ለይሖዋ፣ ለቃሉና ለድርጅቱ ያላቸውን አድናቆት መገንባት ይፈለግበታል። ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ጥሩ አድርገው በመዘጋጀት፣ በጭብጡ ላይ ያተኮሩ ሐሳቦችን በማዘጋጀት፣ በእምነት በመናገርና ትምህርቱን ሕያው አድርገው በማቅረብ እንዲህ ሊያደርጉ ይችላሉ። (ዕብ. 4:12) ተናጋሪው የተሰጠውን ጊዜ መጠበቅ ይፈለግበታል። “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ” የተባለው መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ለመንፈሳዊነታችን ሊጠቅሙን በሚችሉ ብዛት ባላቸው የተለያዩ አስደሳች ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶች የተሞላ ነው።
4 ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የተገኙ ጎላ ያሉ ነጥቦች፦ ይህ ክፍል የተሰጣቸው ወንድሞች ጉባኤውን በሚጠቅም ተግባራዊ መንገድ ሊቀርቡ የሚችሉ የተወሰኑ ቁጥሮች መምረጥ አለባቸው። ይህም የተሰጡትን ምዕራፎች ማንበብ፣ በምዕራፎቹ ላይ ማሰላሰልና የጥቅሶቹን ትርጉም የሚያብራሩ ነጥቦች ለማግኘት በመረጧቸው ጥቅሶች ላይ ምርምር ማድረግ ይጠይቃል። በመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ርዕስ ማውጫ የመጨረሻዎቹ ገጾች ላይ “የጥቅስ ማውጫ” አለ። ይህም በተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ማብራሪያ ለማግኘት ይረዳል። ይህንን ክፍል የሚያቀርቡ ወንድሞች ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ሊኖራቸው ይገባል። በተጨማሪም ከትምህርቱ ጋር የማይሄዱ ነጥቦች መጨመር የለባቸውም። በስድስት ደቂቃ ውስጥ ለመሸፈን የሚያዳግት ብዙ ነገር መዘጋጀት የለባቸውም።
5 ሁላችንም ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ጥቅም ማግኘት እንችላለን። የመናገርና የማስተማር ችሎታችንን ለማሻሻል ሊረዳን ይችላል። በዚህ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ ከተጠቀምን ‘እድገታችንን ለሰዎች ሁሉ በግልጥ ለማሳየት’ እንደሚረዳን ምንም ጥርጥር የለውም።— 1 ጢሞ. 4:15