ለትምህርታችሁ የማያቋርጥ ትኩረት ስጡ
1 አዲሱ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም በጥር 1995 ይጀምራል። ለትምህርታችን ትኩረት ለመስጠትና ከፕሮግራሙ የተቻለንን ያህል ለመጠቀም ምን ልናደርግ እንችላለን?— 1 ጢሞ. 4:16
2 ብዙዎቻችን አምልኮ የተባለውን መጽሐፍ ቀደም ሲል ያጠናነው ቢሆንም በትምህርት ቤቱ ፕሮግራም መሠረት ትምህርቱን መመርመራችን ሁላችንንም ለቅዱሳን ጽሑፎች ያለንን መረዳት ከፍ እንድናደርግ ይረዳናል። አምልኮ ከተባለው መጽሐፍ ውስጥ የተወሰደውን ሐሳብ ለመከለስ በየሳምንቱ ለምን ጥቂት ጊዜ አትመድብም?
3 ሕያውና ትኩረት የሚስቡ መምሪያ ንግግሮች፦ አምልኮ ከተባለው መጽሐፍ የሚቀርቡ መምሪያ ንግግሮች ሕያው በሆነና ትኩረት በሚስብ መንገድ መቅረብ አለባቸው። በተጨማሪም የትምህርቱን ተግባራዊ ጠቀሜታ የሚያጎሉና ስለ መሠረተ ትምህርቶች ጥልቅ መረዳት የሚሰጡ መሆን ይኖርባቸዋል። በትምህርት ቤቱ ስብሰባ ላይ የሚገኝ እያንዳንዱ ቤተሰብ አምልኮ የተባለውን መጽሐፍ ካመጣ የቤተሰቡ አባሎች ሁሉ መምሪያ ንግግሩን በትኩረት ሊከታተሉና ከመጽሐፉ ሊጠቀሙ ይችላሉ።
4 አእምሮን የሚያመራምሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦች፦ በስሜትና ሐሳቡን የሚያስተላልፉትን ቃላት በማጥበቅ በደንብ ማንበብ አንዱ ውጤታማ የማስተማር ክፍል ነው። ከዚህም በተጨማሪ በንግግር ቁ. 2 እንዲነበብ የሚመደበው ክፍል መጠን ብዙ ስላልሆነ ብዙውን ጊዜ ተናጋሪው የመግቢያና የመደምደሚያ ሐሳቦችን ማቅረብ የሚችልበት በቂ ጊዜ ያገኛል። መግቢያው ለክፍሉ አድናቆት የሚያሳድርና አድማጮች ተግባራዊ ጠቀሜታውን እንዲያስተውሉ በቅድሚያ የሚያዘጋጃቸው መሆን አለበት። ተናጋሪው የተመደበለትን ጊዜ ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀም ከተፈለገ መደምደሚያው የትምህርቱን ማብራሪያና ተግባራዊ ጠቀሜታ የሚጠቁሙ ሐሳቦችን ሊጨምር ይችላል።
5 ስለ ትምህርት ቤቱ ፕሮግራምና የተሰጠው ክፍል እንዴት እንደሚቀርብ የሚጠቁም ተጨማሪ መረጃ “የ1995 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም” ላይ ይገኛል። በዚህ ፕሮግራም ላይ የተሰጡትን መመሪያዎች ስንከልስ፣ የተሰጠንን ክፍል በደንብ ስንዘጋጅና የንግግርና የማስተማር ችሎታችንን እንድናሻሽል የሚለገሰንን ምክር በሥራ ላይ ስናውል ለትምህርታችን ትኩረት እንሰጣለን። እስካሁን በትምህርት ቤቱ ያልተመዘገቡ ሁሉ እንዲመዘገቡ ሞቅ ያለ ግብዣ ቀርቦላቸዋል።