ከእውነተኛው አምላክ የሚገኘው እውቀት ወደ ሕይወት ይመራል
1 ኢየሱስ ወደ አባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል። (ዮሐ. 17:3) ይህ እንዴት ያለ ትልቅ ሽልማት ነው! ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ በመጠቀም ሌሎች ሰዎች ለዘላለም ለመኖር ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው እንዲማሩ መርዳት እንችላለን። የሰዎችን ፍላጎት ለመቀስቀስና እውቀት የተባለውን መጽሐፍ እንዲያነቡ ለመገፋፋት ምን ለማለት እንችላለን?
2 መጽሐፍ ቅዱስ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መመሪያ እንደሚሰጥ ለማሳየት የሚከተለውን አቀራረብ ልትጠቀም ትችላለህ:-
◼ “በኑሮ ውስጥ የሚገጥሙንን ችግሮች መፍታት የሚያስችል ተግባራዊ መመሪያ ከየት ማግኘት እንደሚቻል ከጎረቤቶቻችን ጋር እየተወያየን ነበር። በቀደሙት ዘመናት ብዙ ሰዎች መፍትሔ ለማግኘት በቅድሚያ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘወር ይሉ ነበር። ዛሬ ግን የሰዎች አመለካከት ተቀይሯል፤ በሰዎች የተጻፈ ተራ መጽሐፍ እንደሆነ በማሰብ ብዙዎቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥርጣሬ አድሮባቸዋል። እርስዎስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ ለዘመናችን ጠቀሜታ እንዳለው ለመናገር የሚያስችል በቂ ምክንያት አለ። [2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17ን አንብብ።] የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን ባጻፈበት ዘመን የሚሠሩ የነበሩትን ያህል በአሁኑ ጊዜም ይሠራሉ።” እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 16 ላይ ግለጽና በኢየሱስ የተራራ ስብከት ውስጥ ስለሚገኙት ተግባራዊ መመሪያዎች አጠር ያለ ሐሳብ ስጥ። በአንቀጽ 11 ወይም 13 ላይ የሚገኘውን አስተያየት አንብብ። መጽሐፉን እንዲወስድ ጋብዘውና በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው እውቀት በግል መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ተመልሰህ የምትሄድበትን መንገድ አመቻች።
3 ጸሎት የብዙ ሰዎችን ትኩረት የሚስብ ጉዳይ በመሆኑ በሚከተለው ጥያቄ ላይ ውይይት ማድረግ ትፈልግ ይሆናል:-
◼ “በአሁኑ ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ የሚገጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት ጸሎት በእርግጥ ሊረዳን ይችላል ብለው ያስባሉ? [መልስ እስኪሰጥ ድረስ ጠብቀው።] ብዙ ሰዎች ወደ አምላክ በመጸለያቸው ከእርሱ ጋር ይበልጥ እንደተቀራረቡ ሆኖ እንደሚሰማቸውና እንዲህ ማድረጋቸው ውስጣዊ ጥንካሬ እንደሰጣቸው ይናገራሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስም ወደ አምላክ ስንጸልይ ከእርሱ ጋር በይበልጥ እንደምንቀራረብና ውስጣዊ ጥንካሬ እንደምናገኝ ይናገራል። [እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 156 ላይ ግለጥና ፊልጵስዩስ 4:6, 7ን አንብብ።] ይሁንና አንድ ሰው ጸሎቶቹ አንዳንድ ጊዜ መልስ ሳያገኙ እንደሚቀሩ ሊሰማው ይችላል። ይህ ምዕራፍ ‘ከአምላክ ጋር እንዴት መቀራረብ እንደሚችሉ’ ይናገራል። [መጽሐፉን እንዲወስድ ጋብዘው።] ከዚህም በተጨማሪ ከአምላክ ጋር የምናደርገው የሐሳብ ግንኙነት በአንድ አቅጣጫ ብቻ ስለማይወሰን አምላክን እንዴት ማዳመጥ እንደምንችል በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ ተብራርቷል። በሚቀጥለው ጊዜ ስመጣ ስለዚህ ጉዳይ ልንወያይ እንችላለን።”
4 ቀጥተኛ አቀራረብ በመጠቀም ጥናት ለማስጀመር መሞከር ትፈልጋለህን? የሚከተለው መግቢያ የተሳካ ውጤት ሊያስገኝልህ ይችላል:-
◼ “ለሰዎች ነጻ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንደምንሰጥ አየገለጽን ነው። ከአሁን ቀደም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ተከታትለው ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ሰዎችን ለማስጠናት የምንጠቀምበትን መጽሐፍ ላሳይዎት።” እውቀት የተባለውን መጽሐፍ አውጣና የቤቱ ባለቤት የርዕስ ማውጫውን ማየት እንዲችል ገጽ 3ን ገልጠህ “መጽሐፍ ቅዱስ ስለነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ምን ይል ይሆን ብለው አስበው ያውቃሉ?” ብለህ ጠይቅ። የሰውዬውን ትኩረት በይበልጥ የሳበውን ምዕራፍ አውጥተህ ንዑስ ርዕሶቹን አንብብ። ይህን ትምህርት እንዴት እንደምናጠናው በአጭሩ ልታሳየው እንደምትፈልግ ግለጽለት። ከዚያም በኋላ መጽሐፉን እንዲወስድ ጋብዘው።
5 ዛሬ ብዙ ሰዎች ከእውነተኛው አምላክ ለሚገኘው ትክክለኛ እውቀት አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ ነው። (ኢሳ. 2:2-4) በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩና ወደ ሕይወት ጎዳና እንዲያመሩ የመርዳት መብት አለን።— 1 ጢሞ. 2:4