በወዳጅነት ስሜት የሚደረጉ ውይይቶች የሰዎችን ልብ ሊነኩ ይችላሉ
1 ውይይት “በቃል የሚደረግ የሐሳብ ልውውጥ” የሚል ፍች ሊሰጠው ይችላል። ሰዎች በሚያሳስባቸው ጉዳይ ላይ ወዳጃዊ የሆነ ውይይት ማድረግ የሰዎቹን ስሜት ሊማርክና በመንግሥቱ መልእክት አማካኝነት ልባቸውን ለመንካት ሊረዳን ይችላል። ከሰዎች ጋር በሰበካ መልክ ከመነጋገር ይልቅ ወዳጃዊ የሆነና የተዝናና ውይይት ማድረግ ይበልጥ ውጤታማ እንደሆነ ከተሞክሮ ታይቷል።
2 ወዳጃዊ የሆነ ውይይት መጀመር የሚቻልበት ዘዴ፦ ከሌሎች ጋር መወያየት ማለት አስገራሚ የሆኑ ነጥቦች ወይም ጥቅሶች መጥቀስ ማለት አይደለም። ሌላው ወገን ከእኛ ጋር እንዲነጋገር ማድረግ ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል ጎረቤታችን ካለ ሰው ጋር በወዳጅነት መንፈስ ውይይት ስናደርግ ተዝናንተን እንናገራለን እንጂ ድርቅ ያለ ውይይት አናደርግም። ለሰነዘረው ሐሳብ መልስ የሚሆን ነገር በተለመደው መንገድ እንናገራለን እንጂ ቀጥሎ ምን እላለሁ ብለን አናስብም። የሚናገረውን ነገር ከልብ መከታተላችን ከእኛ ጋር መወያየቱን እንዲቀጥል ሊያበረታታው ይችላል። ለሌሎች ስንመሠክርም እንደዚሁ መሆን ይኖርበታል።
3 ወንጀል፣ የወጣቶች ችግር፣ በአካባቢው ያሉ አሳሳቢ ጉዳዮችና የአየር ጠባዩ ሳይቀር ወዳጃዊ የሆነ ውይይት ለመጀመር መግቢያ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ። ከሰዎች ሕይወት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ርዕሰ ጉዳዮች የሰዎችን ፍላጎት በመቀስቀስ በኩል በጣም ውጤታማ ናቸው። አንዴ ውይይቱ ከተከፈተ በኋላ ቀስ ብለን ወደ መንግሥቱ መልእክት ልንቀይረው እንችላለን።
4 ሆኖም ዘና ብሎ ውይይት ለማድረግ ዝግጅት አያስፈልግም ማለት አይደለም። ዝግጅት ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ ውይይቱ እንደ ሁኔታው የማይለዋወጥና ችክ ያለ እንዳይሆን መናገር ያለብኝ እንዲህ ብቻ ነው ብለን መወሰን አይኖርብንም ወይም ደግሞ በቃል የተሸመደደ ስብከት መሆን የለበትም። (ከ1 ቆሮንቶስ 9:20-23 ጋር አወዳድር።) ከሁሉ የተሻለው የዝግጅት ዘዴ ውይይት ሊደረግባቸው የሚችሉ አንድ ወይም ሁለት ቅዱስ ጽሑፋዊ ርዕሶች መምረጥ ነው። በዚህ ረገድ ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን የመወያያ ርዕሶች መከለሱ ጠቃሚ ይሆናል።
5 ወዳጃዊ የሆነ ውይይት ለማድረግ የግድ የሚያስፈልጉ ባሕርያት፦ ከሌሎች ጋር ውይይት ስናደርግ ፍቅራዊ ስሜትና ከልባችን መሆን ይኖርበታል። ፈገግታና ብሩሕ የሆነ ፊት እነዚህን ባሕርያት ለማሳየት ይረዳናል። መልእክታችን በዓለም ውስጥ ካለው ከየትኛውም መልእክት የላቀ ነው፤ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ሁሉ ይማርካል። ሰዎች ከልባችን ተነሣስተን መልካም ምሥራች ልናካፍላቸው በማሰብ ከእነርሱ ጋር ለመወያየት እንደሄድን ከተሰማቸው ለማዳመጥ ይገፋፋሉ።— 2 ቆሮ. 2:17
6 ከሌሎች ጋር የምናደርገው ውይይት አስደሳች መሆን ይኖርበታል። በመሆኑም የመንግሥቱን መልእክት ስናቀርብ ደግና ዘዴኛ መሆን ይኖርብናል። (ገላ. 5:22፤ ቆላ. 4:6) ግለሰቡ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች መጥፎ ስሜት እንዳያድርበት በሚያደርግ መንገድ ውይይቱን ለመደምደም ጣር። እንዲህ ካደረግን መጀመሪያ ላይ ልቡን ለመንካት ባይሳካልን እንኳ በሚቀጥለው ጊዜ ሌላ ምሥክር ሲያነጋግረው ይበልጥ ተቀባይ ሊሆን ይችላል።
7 ወዳጃዊ የሆነ ውይይት ማስጀመር በተራቀቀ የስብከት ችሎታ የተካኑ መሆንን አይጠይቅም። አንድን ሰው በሚያሳስበው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ፍላጎቱን የመቀስቀስ ጉዳይ ነው። ቀደም ብለን ከተዘጋጀን ከሰዎች ጋር ወዳጃዊ ውይይት ለማድረግ እንችላለን። ከዜናዎች ሁሉ የሚበልጠውን ዜና ማለትም የመንግሥቱን ዘላለማዊ በረከቶች ለሌሎች በማካፈል የምናገኛቸውን ሰዎች ሁሉ ልብ ለመንካት እንጣር።— 2 ጴጥ. 3:13