መጽሔት ለማበርከት የሚያስችልህን የራስህን አቀራረብ አዘጋጅ
1 መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ከዓለም ጉዳዮች አንሥቶ ‘ጥልቅ እስከሆኑት የአምላክ ነገሮች’ ድረስ የተለያዩ ሐሳቦችን የሚዳስሱ ወቅታዊና ትምህርት ሰጭ ርዕሶች ይዘው መውጣታቸውን እናደንቃለን። (1 ቆሮ. 2:10) ሁላችንም ይሖዋ እውነትን ቀስ በቀስ ለመግለጥ በሚጠቀምባቸው በእነዚህ መጽሔቶች ላይ ያነበብናቸውን ብዙ አዳዲስና የሚያንጹ ነገሮች እናስታውሳለን። (ምሳሌ 4:18) እነዚህን መጽሔቶች የሚቻለውን ያህል በስፋት ለማሠራጨት ከፍተኛ ጉጉት ሊኖረን ይገባል።
2 የአገልግሎት ክልልህን አጥና፦ በአንተ አካባቢ የሚኖሩት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? ኑሯቸው ሩጫ የበዛበት ከሆነ ተፈላጊውን ነጥብ ብቻ የሚያስጨብጥ አጭር አቀራረብ መዘጋጀት ያስፈልግህ ይሆናል። በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ብዙም የማይዋከቡ ከሆኑ ደግሞ ብዙ መናገር ትችል ይሆናል። አብዛኞቹ የቤት ባለቤቶች ቀን ሥራ የሚሄዱ ከሆነ ከሰዓት በኋላ ፀሐይ በረድ ሲል ወይም አመሻሹ ላይ ወደ ቤታቸው ብትሄድ የተሻለ ውጤት ታገኝ ይሆናል። አንዳንዶቹን ቀን በመንገድ ላይ ምሥክርነት ወይም ከሱቅ ወደ ሱቅ ስትሠራ ልታገኛቸው ትችል ይሆናል። አንዳንድ አስፋፊዎች በመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎችና በከተማ የመናፈሻ ቦታዎች የሚያገኟቸውን ሰዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ በማነጋገር ጥሩ ውጤቶች አግኝተዋል።
3 ከመጽሔቶቹ ይዘት ጋር ተዋወቅ፦ እያንዳንዱን መጽሔት እንደደረሰህ አንብበው። በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ትኩረት ይስባል ብለህ ያሰብከውን ርዕስ ምረጥ። ምን ነገሮች ያሳስቧቸዋል? ከእነርሱ ጋር ልትነጋገርበት ካሰብከው ርዕስ ውስጥ ልትጠቅሰው የምትችለው አንድ ነጥብ ምረጥ። የሰዎቹን ፍላጎት ለመቀስቀስ የሚያስችልህ አንድ ጥያቄ አስብ። አመቺ ሆኖ ካገኘኸው ለቤቱ ባለቤት የምታነብለትን ወቅታዊ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ምረጥ። ለተመላልሶ መጠየቅ መሠረት ለመጣል ምን ልትል እንደምትችል አስብ።
4 በመግቢያህ ላይ የምትናገራቸውን ቃላት አዘጋጅ፦ ራስህን ለማስተዋወቅና ውይይት ለመጀመር የምትጠቀምባቸውን ቃላት በጥንቃቄ ምረጥ። አንዳንዶች የሚከተለውን የመግቢያ ሐሳብ በመጠቀም ውጤት አግኝተዋል:- “በዚህ መጽሔት ውስጥ ለሌሎች ሰዎች ላካፍለው የምፈልገው አንድ አስደሳች ነገር አንብቤያለሁ።” ብዙዎች ደግሞ ሊጠቀሙበት ባሰቡት የመነጋገሪያ ነጥብ ላይ የሚያተኩር ጥያቄ በማቅረብ ውይይታቸውን ይከፍታሉ። ለምሳሌ ያህል:-
5 ስለ ዓመፅ መብዛት የሚናገር ርዕስ የምታስተዋውቅ ከሆነ እንዲህ ለማለት ትችላለህ:-
◼ “እዘረፋለሁ ወይም ጉዳት ይደርስብኛል ብለን ሳንሰጋ ተኝተን ማደር ወይም ከቤታችን መውጣት እንድንችል ምን የሚያስፈልግ ይመስልዎታል?” ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሆን አንድ የምትነግራቸው ነገር እንዳለህ ግለጽ። ይህ መፍትሔ በቅርቡ ሌሎች የማኅበራዊ ኑሮ ችግሮችን ሁሉ ያስወግዳል። ተመሳሳይ ተስፋ የሚሰጥ አንድ ነገር ከመጽሔቱ ላይ ጥቀስ። ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ስትሄድ የቤቱ ባለቤት ለዘላለም መኖር በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 1 ላይ እንዲያተኩር ልታደርግ ትችላለህ።
6 ስለ ቤተሰብ ኑሮ የሚናገር ርዕስ ስታበረክት እንዲህ ልትል ትችላለህ:-
◼ “በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ወላጆች ልጆችን ማሳደግ በጣም ተፈታታኝ ነገር ሆኖ አግኝተውታል። ስለዚህ ጉዳይ ብዙ መጻሕፍት የተጻፉ ቢሆንም ባለሙያዎቹ እንኳ የሚሰጡት ሐሳብ እርስ በርሱ የሚቃረን ነው። አስተማማኝ መመሪያ ሊሰጥ የሚችል ሰው ይኖራል ብለው ያስባሉ?” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ የሞላበት ምክር የሚያስረዳ አንድ ነጥብ ከመጽሔቱ ላይ ጥቀስለት። ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ወቅት ለዘላለም መኖር በተባለው መጽሐፍ ገጽ 245-9 ላይ ያለውን ልጆችን ስለ ማሳደግ የሚናገረውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ አወያየው።
7 ስለ አንድ ማኅበራዊ ችግር የሚናገር ርዕስ ስታስተዋውቅ እንደሚከተለው ለማለት ትችላለህ:-
◼ “ብዙ ሰዎች በጊዜያችን ባሉት አስጨናቂ ሁኔታዎች ምክንያት ውጥረት ውስጥ እንዳሉ ሆኖ ይሰማቸዋል። አምላክ በዚህ ዓይነት መንገድ እንድንኖር አስቦ የነበረ ይመስልዎታል?” ዛሬ ያሉትን ችግሮች እንዴት መወጣት እንደሚቻል የሚጠቁም ወይም ወደፊት ከጭንቀት ነጻ የሆነ ጊዜ ይመጣል ብለን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ምክንያቶችን የሚገልጽ አንድ ርዕስ አሳየው። በሚቀጥለው ጊዜ ልታነጋግረው ስትሄድ ለዘላለም መኖር በተባለው መጽሐፍ ገጽ 12-13 ላይ የሚገኘውን ሥዕል ካሳየኸውና አንቀጽ 12ን ካነበብክለት በኋላ በቀጥታ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር አድርግ።
8 ከቤቱ ባለቤት ሁኔታ ጋር የሚስማማ አቀራረብ ይኑርህ፦ የተለያየ ዓይነት ፍላጎትና አስተዳደግ ካላቸው ሰዎች ጋር ትገናኛለህ። እንደ እያንዳንዱ የቤት ባለቤት ሁኔታ ልትለዋውጠው የምትችል አቀራረብ ተዘጋጅ። ወንድ፣ ሴት፣ በዕድሜ የገፋ፣ ወይም ወጣት ብታገኝ የምትናገራቸውን ነገሮች እንደ ሁኔታው ለማስተካከል ተዘጋጅ። እንዲህ ማለት አለብህ የሚል ድርቅ ያለ ደንብ የለም። አመቺ ሆኖ ያገኘኸውንና ውጤት ይኖረዋል የምትለውን ነገር መናገር ትችላለህ። ይሁን እንጂ ግለት ይኑርህ፤ ከልብህ ተናገር እንዲሁም ጥሩ አዳማጭ ሁን። ‘ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው’ ሰዎች ከልብህ እንደምትናገር አስተውለው ጥሩ ምላሽ ይሰጣሉ።— ሥራ 13:48
9 እርስ በርሳችሁ ተረዳዱ፦ እርስ በርሳችን ሐሳብ ስንለዋወጥ መልእክታችንን ማድረስ የምንችልባቸውን አዳዲስ መንገዶች እንማራለን። አቀራረባችንን አንድ ላይ ሆነን መለማመዳችን ተሞክሮና በራስ የመተማመን ስሜት ለማዳበር ያስችለናል። (ምሳሌ 27:17) አስቀድመህ ምን እንደምትል ከተለማመድክ በር ላይ ስትደርስ የበለጠ የመረጋጋት ስሜት ይኖርሃል። ወላጆች ጊዜ ወስደው ልጆቻው እንዲዘጋጁ መርዳት፣ አቀራረባቸውን ሲለማመዱ ማዳመጥና የማሻሻያ ሐሳብ መስጠት ይገባቸዋል። አዲሶች ይበልጥ ተሞክሮ ካላቸው አስፋፊዎች ጋር መሥራታቸው ሊጠቅማቸው ይችላል።
10 መጽሔት ለማበርከት የሚያስችልህን የራስህን አቀራረብ መዘጋጀት ሊያስቸግርህ አይገባም። ባጭሩ የምትናገረውን አንድ ነጥብ በአእምሮህ የመያዝና አስደሳች በሆነ መንገድ የማቅረብ ጉዳይ ነው። በራስህ አነሣሽነትና ስለነገሩ አስቀድመህ በማሰብ ጥሩ ምላሽ የሚያስገኝ ግሩም አቀራረብ ልታዘጋጅ ትችላለህ።
11 መጽሔቶችን ማሠራጨት በዓለም ዙሪያ የመንግሥቱን መልእክት ከምናዳርስባቸው ዋነኛ መንገዶች አንዱ ነው። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ቅን ልብ ባላቸው ሰዎች እጅ ማስገባት ከቻልክ መጽሔቶቹ ራሳቸው ይናገራሉ። አጋጣሚውን ስታገኝ በአንድ ጊዜ ሁለት መጽሔቶችን እንዲወስድ ለማድረግ ሞክር። ሁልጊዜ መጽሔቶቹ ያላቸውን ጠቀሜታና መልእክታቸው ሕይወት ሊያድን የሚችል መሆኑን አስታውስ። በዚህ መንገድ ‘መልካም ማድረግና ለሌሎች ማካፈል’ ይሖዋን በጣም ያስደስተዋል።— ዕብ. 13:16