“በአምላክ ቃል ማመን” የ1997 የአውራጃ ስብሰባ
1 ሐዋርያው ጳውሎስ “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ” ነው በማለት ጢሞቴዎስን አሳስቦታል። (2 ጢሞ. 3:16 NW) የአምላክ ቃል በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ስለሆነ በዚህ ቃል ለማመን በቂ ምክንያት አለን። የዚህ ዓመት የአውራጃ ስብሰባ ጭብጥ “በአምላክ ቃል ማመን” የሚል ነው። ፕሮግራሙ በእውነት ውስጥ ለብዙ ዓመታት ለቆየንም ሆነ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከይሖዋ ድርጅት ጋር መተባበር ለጀመርን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለንን እምነት ያጠነክርልናል። ሁላችንም በጠቅላላው ፕሮግራም ላይ ለመገኘት እንድንችል ዝግጅት ልናደርግ ይገባናል። ፍላጎት ያሳዩ አዲሶች በተለይም መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናቸው ሰዎች አብረውን ቢገኙ እንዴት የሚያንጽ ይሆናል!
2 የሦስት ቀን የአውራጃ ስብሰባ፦ በዚህ ዓመት ጠቃሚ የሆነ የሦስት ቀን የአውራጃ ስብሰባ ፕሮግራም ተዘጋጅቶልናል። ጉባኤያችሁ በየትኛው ስብሰባ እንደሚካፈል እስካሁን ተነግሯችሁ ስለሚሆን በሦስቱም ቀናት ፕሮግራም ላይ ለመገኘት ቁርጥ ያለ እቅድ አውጥታችሁ መሆን አለበት። አስፈላጊውን ዕረፍት ማግኘት እንድትችሉ አሠሪያችሁን ቀርባችሁ አነጋግራችሁታልን? ትምህርት ቤት የሚማሩ ልጆች ካሏችሁና ስብሰባው የሚደረገው በትምህርት ወቅት ከሆነ ልጆቻችሁ ሃይማኖታዊ ስልጠና በሚያገኙበት በዚህ ጠቃሚ የሆነ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ሲሉ አርብ ቀን ከትምህርታቸው እንደሚቀሩ ለአስተማሪዎቻቸው በደግነት ነግራችኋቸዋልን?—ዘዳ. 31:12
3 ፕሮግራሙ በሦስቱም ቀናት የሚጀምረው ከጠዋቱ 3:30 ላይ ነው። በሮቹ ከጠዋቱ 2:00 ላይ ይከፈታሉ። ከዚያ በፊት መግባት የሚችሉት ለሥራ የተመደቡ ብቻ ናቸው፤ እነርሱም ቢሆኑ በሮቹ ለሁሉም ሰው ከመከፈታቸው በፊት መቀመጫ መያዝ አይችሉም።—ፊልጵ. 2:4
4 በትኩረት መከታተላችሁ የተገባ ነው፦ ሐዋርያው ጴጥሮስ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን በጨለማ ስፍራ እንደሚበራ መብራት ለትንቢታዊው ቃል መጠንቀቃቸው መልካም እንደሚሆን አሳስቧቸዋል። (2 ጴጥ. 1:19) ይህ ለእኛም ይሠራል። በሰይጣን ቁጥጥር ሥር በሚገኘው በዚህ አሮጌ ዓለም ውስጥ መኖር በጨለማ ቦታ ውስጥ ከመሆን ተለይቶ አይታይም። ከመንፈሳዊ ጨለማ እንድንወጣ በመጠራታችን አመስጋኞች ነን። (ቆላ. 1:13፣ 1 ጴጥ. 2:9፣ 1 ዮሐ. 5:19) በብርሃኑ ውስጥ ለመቆየት እንድንችል በመንፈስ አነሳሽነት ለተጻፈው የአምላክ ቃል ትኩረት በመስጠት እምነታችንን ማጠንከር ያስፈልገናል። የዚህ ዓመቱ የአውራጃ ስብሰባችን ይህንን እንድናደርግ ያበረታታናል።
5 በፕሮግራሙ ላይ ለማተኮር በበኩላችን ጥረት የሚጠይቅብን ቢሆንም ይህን በማድረጋችን በእርግጥ እንባረካለን። በፕሮግራሙ ወቅት ንቁ ሆነን ለመከታተል እንድንችል በቂ እረፍት አግኝተን ወደ ስብሰባው ቦታ ለመምጣት መጣር ይኖርብናል። ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት ቦታችሁን መያዝ ትችሉ ዘንድ ወደ ስብሰባው ቦታ ለመድረስ ለእያንዳንዱ ቀን በቂ ጊዜ መድቡ። በእያንዳንዱ ቀን ፕሮግራም የመክፈቻ መዝሙርና ጸሎት ተካፈሉ። አዋቂዎች ምሳሌ መሆንና ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን ማሰልጠን አለባቸው።—ኤፌ. 6:4
6 የቀኑ ፕሮግራም ከመጀመሩ በፊት የክፍሎቹን ርዕሶች ከተመለከትናቸው በስብሰባው ወቅት ምን ነጥቦች ሊቀርቡ እንደሚችሉ አስቀድመን ልናስብ እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን ክፍሉ በሚቀርብበት ጊዜ በከፍተኛ ጉጉት እንድንከታተል ያደርገናል። በራሱ በአምላክ እንዲሁም እርሱን ከልብ የሚፈልጉትን እንደሚክስ በገባው እርግጠኛ ተስፋ ላይ ለምን እንደምናምን ለሌሎች ሰዎች ለመግለጽ የሚያስችሉንን ነጥቦች ለማግኘት እንፈልግ ይሆናል። (ዕብ. 11:1, 6) የፕሮግራሙን ዋና ዋና ነጥቦች ለማስታወስ እንዲረዳን አጭር ማስታወሻ እንድንይዝ ሐሳብ ቀርቦልናል። ብዙ ማስታወሻ የምንይዝ ከሆነ ጊዜያችን በመጻፍ ስለሚያዝ አንዳንድ ቁልፍ ነጥቦች ሊያመልጡን ይችላሉ።
7 ባለፈውም ዓመት አንዳንድ ወጣቶች “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለእኛ ጥቅም በማሰብ ያዘጋጀውን ትምህርት ከማዳመጥ ይልቅ ፕሮግራሙ በመካሄድ ላይ እያለ ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወሩ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሲያወሩ ተስተውለዋል። ኢየሱስ በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ እንደሚሰጠን ቃል ገብቷል። (ማቴ. 24:45-47) ስለዚህ ወደ ስብሰባው የምንመጣው ከዚህ ምግብ ጥቅም ለማግኘት መሆን ይኖርበታል፤ አድናቆት እንደሌለን ልናሳይ አይገባም። (2 ቆሮ. 6:1) ልጆች መቀመጥ ሲሰለቻቸው ተነስተው በአካባቢያቸው ለመዘዋወር ሲሉ ወደ መጸዳጃ ቤት ለመሄድ ደጋግመው ይጠይቃሉ። በቤት ውስጥ ተገቢው ስልጠና ከተሰጣቸው አሁንም አሁንም ወደ መጸዳጃ ቤት አይሄዱም። አንዳንድ ጊዜ ትንሽ ከፍ ከፍ ያሉ ወጣቶች ገለልተኛ በሆኑ ቦታዎች አንድ ላይ በመቀመጥ ሲያወሩ፣ ሲያንሾካሽኩና እርስ በርሳቸው ማስታዎሻዎችን ሲለዋወጡ ይታያሉ። ዛሬ ብዙ ተጽዕኖዎች የሚገጥሟቸው ወጣቶቻችን ፕሮግራሙ በመካሄድ ላይ እያለ ሌሎች ነገሮችን ከመሥራት በመቆጠብ ትኩረታቸውን በሚቀርበው ትምህርት ላይ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የማይጣጣሙ የጎልማሳነት ምኞቶች ሊወገዱ ይገባቸዋል። (ከ 2 ጢሞቴዎስ 2:22 ጋር አወዳድር።) ሁሉም አዋቂዎችና ወጣቶች በአንክሮ መከታተላቸው ይሖዋን ያስከብረዋል እንዲሁም ያስደስተዋል።
8 ከአስተናጋጆች አንዱ እነዚህን ጉዳዮች አስመልክቶ ለማንኛችንም ምክር መስጠቱን አስፈላጊ ሆኖ ቢያገኘው ይህን ጉዳይ የይሖዋ ፍቅራዊ ዝግጅት እንደሆነ አድርገን ልንቀበለው ይገባል። (ገላ. 6:1) ሁላችንም በስብሰባው ለመገኘት የምንጥረው ‘ለማዳመጥና ለመማር’ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። (ዘዳ. 31:12) በተጨማሪም “ጠቢብ እነዚህን ከመስማት ጥበብን ይጨምራል።” (ምሳሌ 1:5) በስብሰባው ላይ ከመገኘታችሁ በፊት ባሉት ቀናት ከፕሮግራሙ ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚዎች ለመሆን እንድትችሉ በመሰብሰቢያው ቦታ አንድ ላይ መቀመጥ፣ ፕሮግራሙ በሚካሄድበት ወቅት ወዲያ ወዲህ አለማለት እንዲሁም በንቃት መከታተል ስላለው ጥቅም በቤተሰብ መልክ ተወያዩ።
9 ይሖዋን የሚያስደስት አጋጌጥ፦ የይሖዋ ሕዝቦች ከመላው ዓለም እይታ የተሰወሩ አይደሉም። (1 ቆሮ. 4:9) በአጠቃላይ ሲታይ በሰዎች ዘንድ የምንታወቀው በጥሩ አለባበሳችንና አጋጌጣችን ነው። ብዙዎች በ1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10 እና በ1 ጴጥሮስ 3:3, 4 ላይ የሚገኙትን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች ተግባር ላይ ማዋላቸው ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር መተባበር ሲጀምሩ ከነበራቸው አቋም ጋር ሲወዳደር ትልቅ ለውጥ እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል። ይህ በዓለም ከምናየው በፍጥነት እያሽቆለቆለ ካለው የአለባበስና የአጋጌጥ የአቋም ደረጃ ምንኛ የተለየ ነው። እንግዳ የሆነ አለባበስ በመከተል፣ በአበጣጠራችን ዓለማዊ ፋሽኖችን በማራመድ ወይም ልከኛ ያልሆነ ልብስ በመልበስ በአጠቃላይ የሰውነት አያያዛችን ዓለምን እንዳንመስል ለመጠንቀቅ እንፈልጋለን። በአለባበስና በአጋጌጥ ምሳሌ በመሆን በስብሰባው ላይ የሚገኙ አዳዲስ ሰዎች ክርስቲያኖች ራሳቸውን ማስጌጥ ያለባቸው እንዴት እንደሆነ እንዲገነዘቡ ልንረዳቸው ይገባል።
10 መልካም ጠባይ ይኑራችሁ፦ መልካም ጠባይ የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ነው። (1 ጴጥ. 2:12) በስብሰባው ላይ፣ በምግብ ቤቶች፣ በሆቴሎች እንዲሁም በምንጓዝበት ጊዜ ሁሉ የምናሳየው ጠባይ ጥሩ ምስክርነት ሊሰጥ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች በአምላክና በቃሉ ማመን በሰዎች ላይ ምን ለውጥ እንደሚያመጣ እንዲያዩ ሊረዳቸው ይችላል። ይህ ምናልባት አንዳንዶች ይሖዋን እንዲያውቁ ያነሳሳቸው ይሆናል። (ከ1 ጴጥሮስ 3:1, 2 ጋር አወዳድር።) አምላክን በጠባያችን የማስከበር ልዩ መብት አግኝተናል። ይህ ንጹህ መሆንንም ይጨምራል። ወረቀቶችን በመቀመጫችን ስር ወይም በሌሎች ቦታዎች መጣል አይኖርብንም። የወዳደቁ ነገሮችን ማለትም እንደ ምግብ፣ ወረቀቶች፣ መጠቅለያዎችና ሌሎችንም ነገሮች ስናይ በማንሳት ለዚህ አገልግሎት በተዘጋጁት ማጠራቀሚያዎች ውስጥ መጨመራችን የተገባ ነው። በተጨማሪም በመተላለፊያዎች ላይ ሌሎችን ልንገፋቸው አንፈልግም።
11 የስብሰባውን ወጪዎች መሸፈን፦ ሁላችንም በስብሰባው ላይ ለመገኘት ስንል የምናወጣቸው ወጪዎች ይኖሩናል። ልናስብበት የሚገባ ሌላም ወጪ አለ። ለአውራጃ ስብሰባው የምንጠቀምባቸው መሰብሰቢያዎች ብዙ ወጪ የሚጠይቁ ናቸው። በተጨማሪም ሊሸፈኑ የሚገባቸው ሌሎች ወጪዎች አሉ። በፈቃደኝነት የምታደርጉት የለጋስነት መዋጮ እጅግ የሚደነቅ ነው።—ሥራ 20:35፤ 2 ቆሮ. 9:7, 11, 13
12 መቀመጫዎች፦ በርከት ላሉ ዓመታት ይሠራበት የነበረው መቀመጫ መያዝ የሚቻለው ለቤተሰባችሁ አባሎችና በመኪናችሁ አብሮ ለሚጓዝ ሰው ብቻ ነው የሚለው መመሪያ አሁንም ይሠራል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙዎች ከዚህ መመሪያ ጋር መስማማታቸውን ማየቱ ደስ የሚል ሲሆን ይህም በስብሰባዎቹ ላይ የሚታየው የፍቅር መንፈስ እንዲጨምር አድርጓል። በአብዛኞቹ የስብሰባ ቦታዎች በቀላሉ ለመግባትና ለመውጣት አመቺ የሆኑት መቀመጫዎች ጥቂት ናቸው። እባካችሁ ይበልጥ አመቺ የሆኑትን መቀመጫዎች ሁኔታቸው ሌላ ቦታ መቀመጥ ለማይፈቅድላቸው ሰዎች በመልቀቅ አሳቢነታችሁን አሳዩ። በተጨማሪም ለጥንቃቄና ለሥርዓታማነት ሲባል ማንም ሰው በደረጃዎች ላይ መቀመጥም ሆነ መተላለፊያዎችን መዝጋት አይኖርበትም።
13 የምስልና የድምፅ መቅረጫ መሣሪያዎች፦ በስብሰባው ወቅት በካሜራዎችና በሌሎች ድምፅ መቅረጫ መሣሪያዎች መጠቀም ይቻላል። ይሁን እንጂ አጠቃቀማችን የሌሎችን ሐሳብ የሚከፋፍል ሊሆን አይገባውም። ፕሮግራሙን በትኩረት ለመከታተል ጥረት የሚያደርጉትን ሌሎች ሰዎች ስለምንረብሽ ፕሮግራሙ እየተካሔደ እያለ ወዲያና ወዲህ እያልን ፎቶግራፍ ማንሳት አይኖርብንም። የትኛውም ዓይነት የመቅረጫ መሣሪያ በስብሰባው ቦታ ካለው የኤሌክትሪክ መስመር ወይም የድምፅ ማስተላለፊያ መሣሪያ ጋር እንዲያያዝ የማይፈቀድ ከመሆኑም በላይ መሣሪያው ክፍት የተተዉ መተላለፊያዎችንና መንገዶችን የሚዘጋ ወይም የሌሎችን እይታ የሚጋርድ መሆን የለበትም።
14 የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና እርዳታ፦ የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና እርዳታ ክፍሉ አገልግሎት የሚሰጠው ለድንገተኛ አደጋ ብቻ ነው። ሥር የሰደደ በሽታ ላለባቸው እርዳታ ሊሰጥ አይችልም። ስለዚህ ለራሳችሁም ሆነ ለቤተሰባችሁ ጤንነት ስለሚያስፈልገው ነገር አስቀድማችሁ ማሰብ ይኖርባችኋል። እባካችሁ እንደ አስፕሪን፣ ምግብ ለመፍጨት የሚረዱ መድሃኒቶች፣ ፋሻዎችና መርፌ ቁልፍ ያሉትን ነገሮች ለማምጣት ሞክሩ፤ እነዚህ ነገሮች በስብሰባው ላይ አይገኙም። በጣም የታመሙ የቤተሰብ አባላት ያሉት ማንኛውም ሰው እነዚህ ሰዎች በየትኛውም ጊዜ ብቻቸውን እንዳይሆኑ መከታተል ይኖርበታል። ለየት ያለ የጤና እክል ያለባቸው አንዳንዶች የሚንከባከባቸው የቤተሰብ አባል ከሌላቸው ለጉባኤያቸው ሽማግሌዎች ሁኔታውን አስታውቆ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ይገባል።
15 የአውራጃ ስብሰባው የምግብ አቅርቦት፦ በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የሚኖረው የምግብ አቅርቦት በጣም ውስን መሆኑ ወይም ደግሞ ጭራሹኑ አለመኖሩ ብዙዎች በሁሉም የስብሰባ ክፍለ ጊዜ ላይ ተገኝተው በሚቀርበው መንፈሳዊ ምግብ ላይ እንዲያተኩሩ ነፃነት ሰጥቷቸዋል። ይህ ቀላል ዝግጅት ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ ብዛት ያላቸው የአድናቆት መግለጫዎች ደርሰውናል። ሁሉም ሰው በሐምሌ 1995 የመንግሥት አገልግሎታችን ወደ ገጽ ሁለት በዞረው አባሪ ጽሑፍ አንቀጽ 17 ላይ እንደተጠቀሱት ያሉ ጠቃሚና ገንቢ የሆኑ ምግቦችን ለምሳ እረፍት ይዞ ለመምጣት እቅድ ማውጣት ይኖርበታል። ጠርሙሶችንም ሆነ የአልኮል መጠጦችን ወደ ስብሰበው ቦታ ይዞ መምጣት አይቻልም። ከበላችሁ በኋላ የተቀመጣችሁበትን አካባቢ ማጽዳታችሁ የሚያስመሰግን ነው።
16 የተዘጋጀልንን መንፈሳዊው ድግስና አጭር በሆነው የምሳ እረፍታችን ወቅት የሚኖረውን የተዝናና እንዲሁም ሰላማዊ የሆነ ወዳጃዊ መንፈስ ከልብ እናደንቃለን። ከዚህ ዝግጅት ዓላማ ጋር በመስማማት በምሳ እረፍት ጊዜ ምግብ ለመግዛት የስብሰባውን ቦታ ለቅቃችሁ ከመሄድ ይልቅ እባካችሁ የምትበሉትን ይዛችሁ ለመምጣት ሞክሩ። እንዲህ ካደረጋችሁ ከወንድሞቻችሁና ከእህቶቻችሁ ጋር ለመደሰት ሰፊ ጊዜ ይኖሯችኋል።
17 “በአምላክ ቃል ማመን” የተባለው የአውራጃ ስብሰባ በቅርቡ እንደሚጀምር በማወቃችን እጅግ ተደስተናል! ይሖዋ በድርጅቱ በኩል ባዘጋጀልን መንፈሳዊ ግብዣ ሙሉ በሙሉ መደሰት እንችል ዘንድ ሁላችንም በጠቅላላው ፕሮግራም ላይ ለመገኘት የሚያስችሉንን ዝግጅቶች ማጠናቀቃችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል። በዚህ መንገድ ከፊታችን ባሉት ቀናት ‘ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀን’ እንሆናለን።—2 ጢሞ. 3:17