ውጤታማ ሆኖ ካገኛችሁት ተጠቀሙበት!
1 የመንግሥት አገልግሎታችን ለአገልግሎት እንድንጠቀምባቸው የተለያዩ የመግቢያ ሐሳቦችን በየጊዜው ያቀርብልናል። ይህም ለመንግሥቱ መልእክት እንዴት ፍላጎት መቀስቀስ እንደምንችል የሚያሳዩ አዳዲስ ሐሳቦች ይሰጠናል። ከእነዚህ መግቢያዎች ውስጥ አንዱን ወይም ከዚያ በላይ ለማጥናት በየወሩ ጥረት ታደርግ ይሆናል። ሆኖም አንዳንድ አስፋፊዎች ከመግቢያዎቹ መካከል በአንዱ ጥቂት ጊዜ ከተጠቀሙ በኋላ ሌላ የመንግሥት አገልግሎታችን እትም አዳዲስ መግቢያዎችን ይዞ ይወጣል። የበፊተኛውን መግቢያ በደንብ ከመልመዳችን በፊት አንድ አዲስ መግቢያ ማጥናት ለሁሉም ሰው ቀላል እንደማይሆን የታወቀ ነው።
2 በመስክ አገልግሎት ላይ ብዙ ሰዓት የሚያሳልፉ በሺህ የሚቆጠሩ አቅኚዎችና ሌሎች አስፋፊዎች መኖራቸው የታወቀ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ብዙ ጉባኤዎች በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ክልላቸውን እንዳለ ይሸፍናሉ። እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲኖሩ አስፋፊዎች አዳዲስ መግቢያዎችንና መልእክቱን ለማቅረብ የሚረዱ ሐሳቦችን በማግኘታቸው ይደሰታሉ። ይህ ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ይረዳቸዋል። አገልግሎታቸው ይበልጥ አስደሳችና ፍሬያማ እንዲሆን ከማስቻሉም በላይ የሚገጥሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዲቋቋሙ ይረዳቸዋል።
3 ያም ሆነ ይህ የሰዎችን ፍላጎት ለመቀስቀስ የሚያስችል ውጤታማ መግቢያ ካለህ በዚያ መግቢያ መጠቀምህን ቀጥል! አንድ መግቢያ ውጤታማ ሆኖ እስከተገኘ ድረስ በዚያ መግቢያ መጠቀምን ማቆም አስፈላጊ አይደለም። መግቢያህን በወሩ ከሚበረከተው ጽሑፍ ጋር እንዲዛመድ አድርገው። በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የሚወጡትን ሐሳቦች በምታነብበት ጊዜ በምትጠቀምበት መግቢያ ውስጥ ለማካተት የምትፈልገው ጥሩ ነጥብ ለማግኘት ጥረት አድርግ።
4 ስለዚህ አዲስ የመንግሥት አገልግሎታችን እትም ሲደርስህ እዚያ ላይ የቀረቡት መግቢያዎች በሐሳብ ደረጃ የቀረቡ መሆናቸውን አስታውስ። የምትጠቀምባቸው ከሆነ ጥሩ ነው። ሆኖም በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ አስቀድሞም ውጤት ያስገኘ መግቢያ ካለህ ተጠቀምበት! ዋናው ቁም ነገር የሚገባቸውን ሰዎች በመፈለግና ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ በመርዳት በጥሩ ሁኔታ ‘አገልግሎትህን መፈጸምህ’ ነው።—2 ጢሞ. 4:5