መጽሔቶችን ታነብባላችሁን?
1 በአፍሪካ የሚያገለግሉ ሚስዮናውያን ባልና ሚስት መጽሔቶቻችንን በማስመልከት እንዲህ ብለዋል:- “መጠበቂያ ግንብ በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን እንድንኖር ረድቶናል። ከእያንዳንዱ እትም ማበረታቻና ኃይል እናገኛለን።” ለመጽሔቶቻችን እንዲህ ዓይነት የጠለቀ አድናቆት አላችሁ? መጽሔቶቹን ለማንበብስ ተመሳሳይ ጉጉት ታሳያላችሁ?
2 በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ተነብበው የሚያልቁ የመጽሔት ርዕሶችን ማዘጋጀት የሚወስደው ጊዜ ቀላል አይደለም። ታዲያ ይህን ስታውቁ መጽሔቶቹን ገለጥ ገለጥ እያደረጋችሁ ሥዕሎች ብቻ አይታችሁና ምናልባትም አልፎ አልፎ ማራኪ ሆኖ ያገኛችሁትን ርዕስ ብቻ አንብባችሁ ታስቀምጡታላችሁ? ከዚህ የበለጠ ነገር ማድረጋችን ጥበብ ይሆናል። በእያንዳንዱ የመጽሔቶቻችን እትም ላይ የሚወጡትን ሁሉንም ርዕሶች ለማንበብና ለማገናዘብ ጊዜ መመደብ ይኖርብናል። መጠበቂያ ግንብ ወቅታዊ መንፈሳዊ ምግብ የምናገኝበት ዋነኛ መጽሔታችን ነው። ንቁ! የተለያዩ ትኩረት የሚስቡና ትምህርት ሰጪ ርዕሶችን ይዞ ይወጣል። እነዚህን መጽሔቶች በማንበብ የምናገኘው እውቀት በመንፈሳዊ ጠንካሮች እንድንሆን ብቻ ሳይሆን በአገልግሎትም ይበልጥ ውጤታማ ተሳትፎ እንድናደርግ ያዘጋጁናል። እኛ ራሳችን ትጉህ አንባቢዎች መሆናችን መጽሔቶቹን ለሌሎች በግለት እንድናበረክት ያነሳሳናል።
3 የማንበብ ልማዳችንን ማዳበር የምንችልበት መንገድ፦ መጽሔቶች እንደደረሷችሁ ተከታትላችሁ በማንበብ ረገድ የተሻለ ነገር ማድረግ ትችሉ ይሆን? ለብዙዎች ጥሩ ውጤት ያስገኙ ሁለት ሐሳቦች እነሆ:- (1) ቋሚ የንባብ ፕሮግራም አውጡ። በየዕለቱ ለንባብ 10 ወይም 15 ደቂቃ ብትመድቡ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ምን ያህል ልታነቡ እንደቻላችሁ ስታዩ ትገረማላችሁ። (2) የት ድረስ እንዳነበባችሁ መከታተል የምትችሉበት ዘዴ ፍጠሩ። ምናልባት ባነበባችሁት በእያንዳንዱ ርዕሰ ትምህርት መጀመሪያ ላይ ማንበባችሁን የሚጠቁም ምልክት ልታደርጉ ትችላላችሁ። እንዲህ የመሰለ ዘዴ ካልተጠቀማችሁ አንዳንድ ርዕሰ ትምህርቶችን ሌላው ቀርቶ ሙሉውን መጽሔት ሳታነቡ ልታልፏቸው ትችላላችሁ። ለእናንተ ሁኔታ የሚስማማ የንባብ ልማድ ማውጣቱና ይህንንም አጥብቆ መከተሉ ጠቃሚ ነው።—ከፊልጵስዩስ 3:16 ጋር አወዳድሩ።
4 “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሰዎችን ትክክለኛ ፍላጎት የሚዳስሱ ርዕሶችን በማውጣት ተለዋዋጭ ከሆነው ዓለም ጋር በሚስማማ መንገድ እየተንቀሳቀሰ ነው። (ማቴ. 24:45) በእርግጥም መጽሔቶች ሕይወታችንን ነክተዋል። በመንፈሳዊ እድገት የምናደርግበት ፍጥነት በአብዛኛው የተመካው በቲኦክራሲያዊ የንባብ ልማዳችን ጥራት ላይ ነው። ጊዜ መድበው ሁሉንም መጽሔቶች የሚያነቡ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ በረከት ያጭዳሉ።