የመጽሔት ደንበኞች በማፍራት “የመንግሥቱን ዘር መዝራት”
1 ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ በተባለው ቡክሌት ውስጥ የሚገኘው መዝሙር 133 “የመንግሥቱን ዘር መዝራት” የሚል ርዕስ አለው። መዝሙሩ የተመሠረተው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ዘር ከሚዘራ ሰው ጋር በማመሳሰል በተናገረው ምሳሌ ላይ ነው። (ማቴ. 13:4-8, 19-23) በመዝሙሩ ውስጥ “በለም አፈር ላይ የሚወድቀው መጠን/ይመካል በእኛ ጥረት” የሚል ስንኝ እናገኛለን። በአገልግሎት ያለንን ውጤታማነት ከፍ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ የመጽሔት ደንበኞችን ማፍራትና ደንበኝነቱ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ማድረግ ነው።
2 የመጽሔት ደንበኞችን ስናፈራ ብዙ ነገሮችን ማከናወን እንችላለን። (1) በየሁለት ሳምንቱ የሚደረገው ቋሚ ጉብኝት ፍላጎት ካሳየው ግለሰብ ጋር ወዳጃዊ ግንኙነት እንድትመሠርቱ ያስችላችኋል። (2) ግለሰቡ በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ውስጥ የሚወጡትን ሕይወት አድን መልእክቶች ያለ ማቋረጥ እንዲያገኝ ታስችሉታላችሁ (3) ከሰውየው ጋር በምታደርጉት ውይይት ለቅዱሳን ጽሑፎች እውነት ጥማት እንዲኖረው ልትረዱት ትችላላችሁ፤ ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር መንገድ ሊጠርግ ይችላል።—1 ጴጥ. 2:2
3 የመጽሔት ደንበኛ ማግኘት የሚቻልበት መንገድ፦ አንድ ሰው ፈቃደኛ ሆኖ መጽሔት በሚወስድበት ጊዜ እያንዳንዱ እትም ግሩም ርዕሶችን ይዞ እንደሚወጣና በየሁለት ሳምንቱ ልትወስዱለት እንደምትችሉ ንገሩት። ከተለያያችሁ በኋላ የግለሰቡን ስምና አድራሻ፣ ውይይት ያደረጋችሁበትን ዕለት፣ መጽሔቱ የመቼ እትም እንደሆነ፣ ያስተዋወቃችሁትን ርዕስና የሰውዬውን ትኩረት ይበልጥ የሳበውን ርዕስ በማስታወሻ ወረቀታችሁ ላይ አስፍሩ።
4 ጥቂት ሰዎችን ብቻ የመጽሔት ደንበኞች በማድረግ መጀመር ትችላላችሁ። ከዚያም መጽሔት የምታበረክቱላቸውን ሰዎች ሁሉ የመጽሔት ደንበኞቻችሁ በማድረግ ቁጥሩን ለማሳደግ ጥረት አድርጉ። የመጽሔት ደንበኞቻችሁ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ሳትቸገሩ ሁሉንም መጎብኘት ትችሉ ዘንድ እንደየመኖሪያ ቤታቸው ልትከፋፍሏቸው ትችላላችሁ። ለእያንዳንዱ ያበረከታችኋቸውን መጽሔቶችና ዕለቱን በጥንቃቄ መዝግቡ። በተጨማሪም ስላደረጋችሁት ውይይትና ዳግመኛ በምትሄዱበት ጊዜ ግለሰቡ ለእውነት ያለውን ጉጉት ለማሳደግ ምን እንደምታደርጉ በማስታወሻ ወረቀታችሁ ላይ አስፍሩ።
5 የንግድ ሥራና ሌላ ሙያ ያላቸውንም የመጽሔት ደንበኞች ማድረግ፦ የሱቅ ሠራተኞችና ሌላ ዓይነት ሙያ ያላቸው ሰዎች መጽሔቶቻችንን አዘውትረው የሚወስዱበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑን ከተሞክሮ ተምረናል። አንድ ሽማግሌ የሚኖርበትን ከተማ ከንቲባ ሳይቀር የመጽሔት ደንበኛው አድርጓቸዋል። አንድ አስፋፊ የሕንፃ መሣሪያዎች አቅራቢ ድርጅት ባለቤት ለሆኑ አንድ የ80 ዓመት ሰው ለአሥር ተከታታይ ዓመታት መጽሔት ሲያደርስላቸው ከቆየ በኋላ ጥናት አስጀምሯቸዋል!
6 አንዲት አቅኚ እህት ወደ አንድ መደብር ገብታ አንድ ባልና ሚስት ታነጋግራለች። ሆኖም ባልና ሚስቱ በጥሩ ፊት አልተቀበሏትም። ሆኖም መጽሔት ወስደው ስለነበረ የመጽሔት ደንበኛ ልታደርጋቸው ወሰነች። ይሁን እንጂ ፊት ስለሚነሷትና የአመለካከት ጥያቄ ብታቀርብላቸውም እንኳ ብዙም ሊያነጋግሯት ስለማይፈልጉ እነርሱን መጎብኘቷን ለማቆም ፈለገች። ሆኖም እህት ስለ ጉዳዩ ከጸለየች በኋላ ቆየት ብላ ለባልና ሚስቱ ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ አበረከተችላቸው። መጽሐፉን ካነበበች በኋላ ሚስትየው “በመጨረሻ እውነትን አገኘሁ!” በማለት ደስታዋን ገለጸች። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላቸውና ከጊዜ በኋላ ባልና ሚስቱ ተጠመቁ። አቅኚዋ ያሳየችው መንፈሰ ጠንካራነት ውሎ አድሮ ፍሬ አስገኝቶላታል።
7 ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ፦ አዲስ መጽሔት በሚደርሳችሁ ጊዜ እያንዳንዱን ርዕስ አንብቡ። የእያንዳንዱን ደንበኛችሁን ስሜት ሊማርክ የሚችል ነጥብ ፈልጉ። ከዚያም ተመልሳችሁ ስትሄዱ “ይህን ርዕስ ሳነብ እርስዎ ትዝ አሉኝ፤ ይወዱታል ብዬ አስባለሁ” ለማለት ትችላላችሁ። በየትኛውም የዕድሜ ክልል ላይ ያሉ አስፋፊዎች የመጽሔት ደንበኞች በማፍራት ሊደሰቱ ይችላሉ። ሌላው ቀርቶ ትንንሽ ልጆችም እንኳ እንዲህ ለማለት ይችላሉ:- “እንደገና ስላገኘሁዎት ደስ ብሎኛል። በቅርብ የወጡት የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት የግል ቅጂዎን ይዤልዎት መጥቻለሁ። . . . የሚለውን ርዕስ ይወዱታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።”
8 “በሚቀጥለው እትማችን” የሚለውን ሣጥን በማሳየት ቀጥለው የሚወጡትን ርዕሰ ትምህርቶች በጉጉት እንዲጠባበቁ አድርጉ። ተከታታይ ክፍል ያላቸው ርዕሶች የሚወጡ ከሆነ ይህንኑ በመንገር የትኛውም ክፍል እንዳያመልጣቸው አበረታቷቸው። ለመጽሔት ደንበኞቻችሁ መጽሔት ለማድረስ በምትሄዱበት ጊዜ ሁሉ አንድ ተመላልሶ መጠየቅ ብላችሁ ልትሞሉት እንደምትችሉ አትዘንጉ። ከሁሉም በላይ ግን ግባችን እነዚህን የመጽሔት ደንበኞች የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር እንደሆነ አትዘንጉ።
9 የመጽሔት ደንበኞቻችሁን ዘወትር ጎብኟቸው፦ የመጽሔት ደንበኞቻችሁን አመቺ ሆኖ ባገኛችሁት ሰዓት ልትጎበኟቸው ትችላላችሁ። ለምሳሌ ቅዳሜና እሁድ ጠዋት፣ ከሰዓት በኋላ አመሻሹ ላይ፣ ጠዋት በማለዳ ወይም ቅዳሜና እሁድ ከቤት ወደ ቤት የተወሰነ ሰዓት ከሠራችሁ በኋላ ልትሄዱ ትችላላችሁ። በመታመማችሁ ወይም ለእረፍት ራቅ ወዳለ ቦታ በመሄዳችሁ ደንበኞቻችሁ ዘንድ መሄድ የማትችሉ ከሆነ ከቤተሰባችሁ ወይም ከጉባኤያችሁ አንድ አስፋፊ መጽሔቶቹን እንዲያደርስላቸው ልታደርጉ ትችላላችሁ። በዚህ መንገድ የመጽሔት ደንበኛችሁ የግል የመጽሔት ቅጂያቸው ሳይጓደል እንዲደርሳቸው ማድረግ ትችላላችሁ።
10 የመንግሥቱን ዘር መዝራት የሚቻልበት አንዱ መንገድ የመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ያለማቋረጥ ለመጽሔት ደንበኞች ማድረስ ነው። ለእነዚህ የመጽሔት ደንበኞቻችሁ የቅዱስ ጽሑፉን እውነት ባስተማራችኋቸው መጠን እነርሱም የመንግሥቱን ቃል ሊያስተውሉና አልፎ ተርፎም ከእናንተ ጎን ተሰልፈው የመንግሥቱን ፍሬ ሊያፈሩ ይችላሉ።—ማቴ. 13:8, 23