የመጽሔት ደንበኞች ማፍራት ጥናት ለማስጀመር ጥሩ በር ይከፍታል
1. የይሖዋ ድርጅት ከረጅም ጊዜ ጀምሮ አስፋፊዎች የመጽሔት ደንበኞችን እንዲያፈሩ ሲያበረታታ የቆየው ለምንድን ነው?
1 ብዙ ሰዎች ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ባይፈልጉም እንኳ መጽሔቶቻችንን ማንበብ ያስደስታቸዋል። በመሆኑም የይሖዋ ድርጅት ከረጅም ጊዜ ጀምሮ አስፋፊዎች የመጽሔት ደንበኞችን እንዲያፈሩ ሲያበረታታ ቆይቷል። ሰዎች ዘወትር መጽሔቶቻችንን የሚያነቡ ከሆነ ብዙውን ጊዜ የአምላክን ቃል ለማወቅ ጉጉት ያድርባቸዋል። (1 ጴጥ. 2:2) ያነበቡት ነገር ውሎ አድሮ ጥሩ ምላሽ እንዲሰጡና መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ የሚቀርብላቸውን ግብዣ እንዲቀበሉ ሊያነሳሳቸው ይችላል።
2. የመጽሔት ደንበኞቻችንን ፍላጎት ማሳደግ የምንችለው እንዴት ነው?
2 የእውነትን ዘር ‘አጠጡ’፦ ለመጽሔት ደንበኛችን መጽሔቶችን ሰጥቶ ከመሄድ ይልቅ ግለሰቡን ለማወያየትና ከእሱ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን የግለሰቡን ሁኔታ፣ ፍላጎትና አመለካከት ተረድተን በማስተዋል እንድንናገር ያስችለናል። (ምሳሌ 16:23 NW) ግለሰቡን ለማነጋገር በሄዳችሁ ቁጥር ጥሩ ዝግጅት አድርጉ። የሚቻል ከሆነ ከሰጣችሁት መጽሔት ላይ አንድ ሐሳብ ወይም ጥቅስ ወስዳችሁ ባጭሩ በማብራራት በልቡ ውስጥ የተዘራውን የእውነት ዘር አጠጡ። (1 ቆሮ. 3:6) ግለሰቡን ሄዳችሁ ባነጋገራችሁት ቁጥር ቀኑንና የሰጣችሁትን መጽሔት እንዲሁም የተወያያችሁበትን ርዕሰ ጉዳይና ጥቅስ በማስታወሻችሁ ላይ አስፍሩ።
3. የመጽሔት ደንበኞቻችንን ለመጠየቅ ተመልሰን መሄድ ያለብን በየስንት ጊዜው ነው?
3 ተመልሰን መሄድ ያለብን በየስንት ጊዜው ነው? ለመጽሔት ደንበኞቻችን አዲስ የወጡትን መጽሔቶች ለመስጠት በወር አንዴ መሄድ እንዳለብን የታወቀ ነው። ሆኖም ሁኔታችን የሚፈቅድልን ከሆነና ግለሰቡ ፍላጎት ካለው ከአንድ ጊዜ በላይ ሄደን ልናነጋግረው እንችላለን። ለምሳሌ ያህል መጽሔቱን ከሰጠነው ከአንድ ወይም ከሁለት ሳምንት በኋላ ተመልሰን በመሄድ “ዛሬ ጎራ ያልኩት ከሰጠሁህ መጽሔቶች ላይ አንድ ሐሳብ ባጭሩ ላሳይህ ፈልጌ ነው” ልንለው እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን ግለሰቡ ያን ርዕሰ ጉዳይ የማንበብ ፍላጎቱ እንዲቀሰቀስ ሊያደርግ ይችላል። መጽሔቱን አንብቦት ከሆነ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ልንጠይቀውና በዚያ ላይ ባጭሩ ልናወያየው እንችላለን። ወይም ደግሞ ግለሰቡ መጽሔቶቻችንን ማንበብ የሚያስደስተው ከሆነ ተመልሰን በምንሄድበት ጊዜ በዚያን ወር የምናበረክተውን ትራክት፣ ብሮሹር ወይም መጽሐፍ ልናበረክትለት እንችላለን።
4. የመጽሔት ደንበኞቻችን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኞች መሆን አለመሆናቸውን ለማወቅ አልፎ አልፎ ምን ማድረግ እንችላለን?
4 ግለሰቡ መጽሐፍ ቅዱስን እንድታስጠኑት እስኪጠይቃችሁ ድረስ አትጠብቁ። እናንተ ራሳችሁ ቅድሚያውን ውሰዱ። ቀደም ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፍላጎት እንደሌለው ገልጾልን የነበረ ቢሆንም እንኳ በመጠበቂያ ግንብ ላይ የሚወጣውን “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው” የተባለውን ዓምድ አልፎ አልፎ በመጠቀም የመወያየት ፍላጎት እንዳለውና እንደሌለው ለማወቅ ጥረት ማድረግ እንችላለን። ምናልባትም እዚያው በር ላይ እንደቆመ ልናስጠናው እንችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ግለሰቡን ጥናት ማስጀመር ባንችልም እንኳ ፍላጎቱን ለማሳደግ መጽሔቶቹን መስጠታችንን እንቀጥላለን።