1 የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን በትኩረት ሲከታተሉ ቆይተዋል። ስለዚህ የዚህ ዓመት የአውራጃ ስብሰባ ጭብጥ “የአምላክ ትንቢታዊ ቃል” የሚል መሆኑን ስናውቅ በጣም ተደስተናል። በዚህ ስብሰባ ላይ ይሖዋ ‘በተገቢው ጊዜ ያዘጋጀልን ምግብ’ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጓጉተን ነበር። (ማቴ. 24:45) በእርግጥም አምላክ አትረፍርፎ ሰጥቶናል።
2 የስብሰባው ጎላ ጎላ ያሉ ነጥቦች፦ ዓርብ ዕለት የቀረበው የጭብጡ ቁልፍ ንግግር “የአምላክን ትንቢታዊ ቃል በትኩረት መከታተል” የሚል ሲሆን የኢየሱስን በተአምራዊ ሁኔታ መለወጥ በተመለከተ የእውቀት ብርሃን የሚሰጥ ሐሳብ ያካተተ ንግግር ነበር። (ማቴ. 17:1-9) ይህ ንግግር ወደ መጨረሻው ቀን ጠልቀን የገባን በመሆኑ ወደተሻለ ዘመን በምንሸጋገርበት ደፍ ላይ እንደምንገኝና አዲሱ ሥርዓት በደጅ እንደቀረበ ጠበቅ አድርጎ ገልጿል! ለአምላክ ቃል ትኩረት እንደሰጠን የምናሳየው አዘውትረን የምናነበው ከሆነ ነው። “የአምላክን ቃል በማንበብ ተደሰቱ” የሚለው ሲምፖዚየም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችንን ይበልጥ አስደሳችና ጠቃሚ ለማድረግ የሚረዱ ተግባራዊ ምክሮችን የያዘ ነበር።
3 በቅዳሜ ከሰዓት በኋላው ፕሮግራም ላይ በመጨረሻ ቀኖች ውስጥ የምንኖር መሆናችንን እንድናምን የሚያደርጉንን ምክንያቶች የሚያስገነዝብ ንግግር ቀርቦ ነበር። እነዚህን ሁሉ ታስታውሳላችሁን? እሁድ ጠዋት በቀረበው ንግግር እኛ ያለንበት ዘመን ነቢዩ ዕንባቆም ከነበረበት ዘመን ጋር በጣም እንደሚመሳሰል ሕያው በሆነ መንገድ የተብራራ ሲሆን ይሖዋ በቅርቡ ክፉዎችን በማጥፋትና ጻድቃንን በማዳን ከፍተኛ እርምጃ ሲወስድ የነቢዩ ዕንባቆም ትንቢት ሁለተኛ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ተገልጿል። ስለ ያዕቆብና ስለ ኤሳው የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ ፍሬ ነገር ተገንዝበሃል? የግዴለሽነትንና የቸልተኝነትን መንፈስ በመቋቋም ከይሖዋ የምናገኛቸውን በረከቶች በንቃት መከታተል አለብን።
4 የስብሰባው ፕሮግራም በአሁኑ ጊዜ ያልተፈጸሙት አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ያለንን ጠንካራ እምነት በከፍተኛ ሁኔታ አጠናክሮልናል። ከዚህም በላይ የአምላክን ትንቢታዊ ቃል ለሌሎች ማወጃችንን እንድንቀጥል አበረታቶናል!