በሚያዝያ 2000 ከምንጊዜውም የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ እንችል ይሆን?
1 ረቡዕ ሚያዝያ 19 ምሽት በአገልግሎት ዓመቱ ሁሉ የምናስበው ልዩ ጊዜ ይሆናል። በዚያ ዕለት ፀሐይ ስትጠልቅ በመላው ዓለም የሚገኝ እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤና ቡድን የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ በዓል ያከብራል። በየትኛውም የጊዜ ሰቅ ላይ እንኑር የኢየሱስ ክርስቶስን መሥዋዕታዊ ሞት ማሰብ የዓመቱ ጎላ ያለ ክንውን ነው። የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ቀን በ2000 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ሚያዝያ ወር ላይ ምልክት ተደርጓል።
2 የሚያዝያ ወር ይሖዋ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት ላሳየን ይገባናል የማንለው ደግነት ያለንን አድናቆት በሙሉ ነፍስ ለማሳየት ግሩም አጋጣሚ ይከፍትልናል። እንዴት? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ይህን ስለ ቈረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።” (2 ቆሮ. 5:14, 15) አዎን፣ የመንግሥቱ አገልጋዮች ከነበርንባቸው ጊዜያት ሁሉ ይልቅ በዚህ በሚያዝያ ወር ላቅ ያለ እንቅስቃሴ በማድረግ የምንኖረው ለራሳችን ሳይሆን ስለ እኛ ሞቶ ለተነሳው እንደሆነ ማሳየት እንችላለን!
3 በሚያዝያ ረዳት አቅኚ ለመሆን አመልክት፦ ሐዋርያው ጳውሎስ “ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቈጥራለሁ” ብሎ በተናገረ ጊዜ ቀስቃሽ ምሳሌ ትቶልናል። (ሥራ 20:24) እኛም ስለ ይሖዋ አምላክ የተሟላ ምሥክርነት የመስጠት መብት አግኝተናል። ይህን ከዳር ለማድረስ በሚያዝያ በረዳት አቅኚነት ረገድ ከዚህ በፊት ከነበረን የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ እንፈልጋለን!
4 አምስት ቅዳሜና እሁዶች ያሉት ሚያዝያ 2000 ብዙዎች ረዳት አቅኚ ሆነው እንዲያገለግሉ ግሩም አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። በመጋቢት 1997 1, 104 የደረሰ ከፍተኛ የረዳት አቅኚ ቁጥር በተገኘ ጊዜ በዚህ የአገልግሎት መስክ የተካፈሉት አስፋፊዎች ከጠቅላላው ቁጥር 20 በመቶው ነበሩ። ከሁለት ዓመት በኋላ ይኸውም በነሐሴ 1999 ሪፖርት ያደረጉት ጠቅላላ የአስፋፊዎች ቁጥር ከበፊቱ ከ15 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል። በፊት የነበረውን ከፍተኛ የረዳት አቅኚዎች ቁጥር እጅግ ማሳደግ እንደምንችል ከዚህ እንገነዘባለን። በተጨማሪም ከዚያ ወዲህ ረዳት አቅኚዎች እንዲያሟሉ የሚጠበቅባቸው የሰዓት ግብ መቀነሱ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ብዙዎች ወደዚህ የአገልግሎት መብት እንዲገቡ ሁኔታውን ቀላል ያደርግላቸዋል። እያንዳንዱ የተጠመቀ አስፋፊ በሚያዝያ ረዳት አቅኚ መሆን መቻል አለመቻሉን በጸሎት ሊያስብበት ይገባል።
5 በ2000 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ የሚገኘውን የሚያዝያ ወር በመጠቀም በሚቀጥለው ወር የምትመራበትን ፕሮግራም አሁኑኑ አውጣ። በዚያ ወር በየትኞቹ ቀናት በመስክ አገልግሎት መካፈል እንደምትችል ወስንና በስብከቱ እንቅስቃሴ ለማሳለፍ እችላለሁ የምትለውን ሰዓት በሙሉ ደምር። መደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለሌሎች በመመስከር የምታሳልፈውን ጊዜም ጨምር። ድምሩ ረዳት አቅኚዎች እንዲያሟሉ ከሚጠበቅባቸው የ50 ሰዓት ግብ ጋር ይቀራረባልን? የሚፈለገው የሰዓት ግብ የሚጎድልህ ከሆነ ረዳት አቅኚ ለመሆን የሚያስችልህን ጊዜ ለመዋጀት ባወጣኸው ፕሮግራም ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ ትችላለህ? በየዕለቱ በአማካይ አንድ ሰዓት ከ40 ደቂቃ በማገልገል በወር የሚፈለግብህን 50 ሰዓት ማሟላት ትችላለህ።
6 የዘወትር አቅኚዎች እንዲያሟሉ የሚጠበቅባቸው የሰዓት ግብም ቀንሷል። የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር አስበህ ታውቃለህን? ይህን ለማድረግ ለምን የሚቀጥለውን መስከረም ትጠብቃለህ? ሚያዝያ አቅኚነት ለመጀመር አመቺ ወር ነው! የዘወትር አቅኚዎች እንዲያሟሉ የሚጠበቅባቸውን 70 ሰዓት ማሟላት የማትችል ሆኖ ከተሰማህ ለምን በሚያዝያ ረዳት አቅኚ ሆነህ 70 ሰዓት ለማገልገል ግብ አታደርግም? ልታደርገው የምትችለው ነገር መሆኑን አንድ ጊዜ ካየህ ቶሎ ብለህ ወደ ዘወትር አቅኚነት ለመግባት ትገፋፋ ይሆናል።—አገልግሎታችን የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 113-14 ተመልከት።
7 የምሥራቹ አስፋፊ እንደመሆንህ መጠን ሙሉ ተሳትፎ አድርግ፦ ለአምላክና ለሰዎች ያለን እውነተኛ ፍቅር አስፋፊዎችም ሆንን አቅኚዎች የግል ሁኔታችን በሚፈቅድልን መጠን በይሖዋ አገልግሎት የቻልነውን ያህል በሙሉ ነፍስ እንድንሠራ ያንቀሳቅሰናል። (ሉቃስ 10:27) ‘ሰውን ሁሉ ይልቁንም የሚያምኑትን በሚያድን በሕያው አምላክ ተስፋ ስለምናደርግ በተቻለ መጠን ጠንክረን እንደምንሠራና እንደምንታገል’ በዚህ መንገድ እናሳይ። (1 ጢሞ. 4:10) ሁሉም አስፋፊ በሚያዝያ ወር በመንግሥቱ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ ያደርጋል ብለን የምንጠብቀው በዚህ ምክንያት ነው።
8 ኢየሱስ “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” በማለት የሰጠውን ማሳሰቢያ አንዘንጋ። ይህን ተናግሮ እንደጨረሰ 12 ሐዋርያቱን ጠርቶ እንዲሰብኩ ላካቸው። (ማቴ. 9:37, 38፤ 10:1, 5, 7) አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በስብከቱ እንቅስቃሴ ጥሩ ስልጠና ካገኙ ከአንድ ዓመት በኋላ ኢየሱስ ሌሎች ሰባ ደቀ መዛሙርት ሾመና “መከሩስ ብዙ ነው . . . እንግዴህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” የሚል ተመሳሳይ መመሪያ ሰጥቶ ላካቸው። (ሉቃስ 10:1, 2) የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ይሖዋ ለዚህ ጸሎት እንዴት መልስ እንደሰጠ ዘግቧል። በ33 እዘአ የደቀ መዛሙርት ቁጥር ወደ 120 አደገ። ቀጥሎ ከፍተኛው የደቀ መዛሙርት ቁጥር በተከታታይ 3, 000 እና 5, 000 ላይ ደረሰ። (ሥራ 1:15፤ 2:41፤ 4:4) ከዚያ በኋላ “የደቀ መዛሙርት ቊጥር እጅግ እየበዛ ሄደ።” (ሥራ 6:7) በተመሳሳይ በዚህ ዘመን የመከሩ ጌታ ተጨማሪ የመንግሥት ሰባኪዎችን እንዲሰጠን መለመናችንን መቀጠል አለብን! እያንዳንዱ የጉባኤ አስፋፊ በእያንዳንዱ ወር በአገልግሎት ለመሳተፍ ቁርጥ ያለ ዝግጅት በማድረግ ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ ነገር ማድረግ ይገባዋል።
9 እባክህ በ2000 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ላይ የሚያዝያን ወር በደንብ ተመልከተው። የወሩ ሁለት የመጀመሪያ ቀናት ቅዳሜና እሁድ ላይ ስለሚውሉ የወሩን አገልግሎት ቶሎ ለመጀመር በዚያ የሳምንት መጨረሻ በአገልግሎት ለመካፈል እቅድ ማውጣት ትችላለህ? በዚያ ወር ከጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ቡድንህ ጋር በመሆን ለእያንዳንዱ “የመጽሔት ቀን” ድጋፍ መስጠት ትችላለህ? በእያንዳንዱ እሁድ አንድ ሰዓት ወይም ከዚያ የበለጠ ጊዜ በአገልግሎት ማሳለፍ ትችላለህ? በወሩ ውስጥ ቢያንስ አንድ ብሔራዊ የበዓል ቀን ስለሚኖር በአገልግሎት ለመካፈል ሰፊ አጋጣሚ ይኖራል። በምሽት አገልግሎት ለመካፈል አንዳንድ ዝግጅቶችን ማድረግ ትችላለህ? በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት ወይም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በምታከናውንበት ጊዜ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት መስጠት የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች ሁሉ በደንብ መጠቀም እንደምትችል አትዘንጋ። በአገልግሎት የተወሰኑ ሰዓታት ልታሳልፍ በምትችላቸው ቀኖች ላይ ምልክት አድርግና የአገልግሎት ሰዓትህን በቀን መቁጠሪያው ላይ መዝግብ።
10 ብቃቱን የሚያሟሉና የሽማግሌዎችን የድጋፍ ሐሳብ ያገኙ ሁሉ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ሆነው ማገልገል ለመጀመር ሚያዝያ ምቹ ጊዜ ይሆንላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስን የምታስጠናው ሰው ካለ የምሥራቹ አስፋፊ መሆን እንደሚፈልግ ለሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ መንገር የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብለህ ታስባለህ? ያልተጠመቁ ልጆች ካሉህ መንፈሳዊ እድገታቸውን በተመለከተ ከሽማግሌዎች ጋር ተወያይተህበታል? አስፋፊነት ለመጀመር ይህ ተስማሚ ጊዜ እንደሆነ አይሰማህም?—አገልግሎታችን የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 97-100 ተመልከት።
11 በሚያዝያ 2000 ከዚህ በፊት ካደረግነው የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ ስንጥር ሁላችንም በአገልግሎት መካፈልና በወሩ መጨረሻ ላይ የመስክ አገልግሎት ሪፖርታችንን መመለስ ይገባናል። (ከማርቆስ 6:30 ጋር አወዳድር።) በመስክ አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈሉ ያልተጠመቁ አዲስ አስፋፊዎች የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን በተገቢው ጊዜ ሪፖርት እንዲያደርጉ ማበረታታት ያስፈልጋል። በእኛ በኩል የሚፈለግብንን በማከናወን በሚያዝያ ለሚሰበሰበው ሪፖርትና በምንሰጠው ምሥክርነት ለይሖዋ ከፍተኛ የውዳሴ ድምፅ ለማሰማት ጥሩ አስተዋጽዖ ማበርከት እንችላለን።
12 ሌሎች በመታሰቢያው በዓል እንዲገኙ ጋብዝ:- በ2000 በሚከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ አዲስ ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ብንመለከት ደስ አይለንም? ደስ እንደሚለን የታወቀ ነው! ምክንያቱም ከምንጊዜውም ይበልጥ በጣም ብዙ ሰዎች ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ላሳዩን የላቀ ፍቅር አድናቆታቸውን ለመግለጽ ሲሰበሰቡ ማየት በእርግጥም ያስደስታል! (ዮሐ. 3:16፤ 15:13) እናንተንም ሆነ ቤተሰባችሁን በመታሰቢያው በዓል ላይ ከመገኘት ሊያስቀር የሚችል ምንም ነገር እንዳይፈጠር አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ አድርጉ።
13 ሌሎች ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ከአሁኑ መጋበዝ መጀመር አለብን። መጋበዝ የምትፈልጋቸውን ሰዎች ስም በዝርዝር ጻፍ። ከዚህ በፊት ሲያጠኑ የነበሩትን፣ አሁን በማጥናት ላይ ያሉትን ሁሉና ተመላልሶ መጠይቅ የምታደርግላቸውን ሁሉ ጨምረህ መዝግብ። በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤትና በጉርብትና የምታውቃቸውን እንዲሁም ከአንተ የሚያገናኝ ጉዳይ ያለውን ማንኛውንም ሰው በያዝከው ዝርዝር ውስጥ ጨምር። የምታውቃቸውን ሌሎች ሰዎችና ዘመዶችህንም አትርሳ። መዝግበህ ከጨረስክ በኋላ ለእያንዳንዱ በግል ልባዊ ግብዣ ማቅረብ ጀምር። የመታሰቢያው በዓል መቼ እና የት እንደሚከበር በግልጽ ንገራቸው። ሚያዝያ 19 ሲቃረብ ለእያንዳንዳቸው በግል ወይም ስልክ እየደወልክ አስታውሳቸው። በዓሉ በሚከበርበት ምሽት አብራችሁ መሄድ እንደምትችሉ ንገራቸው።
14 ማኅበሩ ከዚህ ቀደም በላከው መመሪያ መሠረት በጉባኤው የአገልግሎት ክልል ውስጥ የሚገኙ አገልግሎት ያቆሙ አስፋፊዎች በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ለማበረታታት የሽማግሌዎች አካል ልዩ ጥረት ማድረግ ይገባዋል። (ማቴ. 18:12-14) ሽማግሌዎች ማኅበሩ የካቲት 2, 1999 የላከውን ደብዳቤ እንደገና ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። የጉባኤው ጸሐፊ አገልግሎት ያቆሙ አስፋፊዎችን ስም በሙሉ ሲጽፍ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ደግሞ ሄደው የሚያነጋግሯቸውንና ወደ መታሰቢያው በዓል የሚጋብዟቸውን ሽማግሌዎች ይመድባል። እነዚህ አገልግሎት ያቆሙ አስፋፊዎች በተቻለ መጠን አሁኑኑ የሚያበረታታ የእረኝነት ጉብኝት ከተደረገላቸው ተነቃቅተው ሌላው ቀርቶ በሚያዝያ ወር በመስክ አገልግሎት እንደገና መካፈል ይጀምሩ ይሆናል። በመስክ አገልግሎት ጥሩ ልምድ ካለው አስፋፊ ጋር እንዲያገለግሉ ቢጋበዙ የሚያንጽ ሆኖ ያገኙት ይሆናል።
15 በሚያዝያ ለሚደረገው እንቅስቃሴ ጥሩ ድጋፍ እንዲገኝ አበረታቱ! በሚያዝያ 2000 ከዚህ በፊት ካደረግነው የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሽማግሌዎች፣ የጉባኤ አገልጋዮችና የቤተሰብ ራሶች ሁሉ የየበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ጥሩ ቅንጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሽማግሌዎች ሁሉን ነገር በሚገባ ለማደራጀትና አመራር ለመስጠት ትጋት ያሳያሉ። (ዕብ. 13:7) በሥራ ቀኖች እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ለሚደረጉት የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎች ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል። ከሰዓት በኋላ እና አመሻሹ ላይ ለሚደረግ የአገልግሎት እንቅስቃሴ ተጨማሪ የመስክ ስምሪት ስብሰባዎች እንዲኖሩ ማድረግ ይቻላል። በሚያዝያ ሊደረግ የታቀደውን የሥራ እንቅስቃሴ የሚያሳይ የተሟላ ፕሮግራም በማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ መለጠፍ ይገባል። በፕሮግራሙ ላይ የወጣውን እያንዳንዱን የመስክ ስምሪት ስብሰባ የሚመራ አንድ ሰው መመደብ አስፈላጊ ነው። እያንዳንዱ ቡድን የሚፈልገውን ያህል ማግኘት እንዲችል በቂ የአገልግሎት ክልሎች አዘጋጁ።
16 በሚያዝያ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ይበረከታሉ። ፍላጎት ለሚያሳዩ ሰዎች ሁሉ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው የተባለው ብሮሹር በማበርከት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለማስጀመር ጥረት ይደረጋል። በመሆኑም በቂ መጠን ያላቸው መጽሔቶችና ብሮሹሮች ማዘጋጀት ያስፈልጋል።
17 በወሩ መጨረሻ ላይ የመጽሐፍ ጥናት መሪዎችና ረዳቶቻቸው በሙሉ በቡድናቸው ውስጥ ያሉ አስፋፊዎች ሁሉ የአገልግሎት ሪፖርታቸውን ሳይዘገዩ እንዲመልሱ ማበረታታት አለባቸው። ምናልባትም እሑድ ሚያዝያ 30 ይህን ማድረግ ይቻል ይሆናል። የጉባኤው ጸሐፊ ሪፖርቱን በሚመዘግብበት ጊዜ አንዳንድ አስፋፊዎች እንዳልመለሱ ካስተዋለ የጉባኤውን ሪፖርት ወደ ማኅበሩ ከሚልክበት ከግንቦት 6 በፊት እንዲመልሱ በደግነት ሊያስታውሳቸው ይችላል። ሪፖርት ያልመለሱ አስፋፊዎችን ለማግኘት የመጽሐፍ ጥናት መሪዎች እንዲረዱት መጠየቅ ይችላል።
18 የአምላክ ሕዝቦች የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበትን ወር በዓመቱ ውስጥ ካሉት ሁሉ እጅግ ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። ይህ ወቅት ሁላችንም በይሖዋ አገልግሎት ሥራ የሚበዛልን ጊዜ ሊሆንልን ይገባል። የምሥራቹ አስፋፊ እንደመሆኑ መጠን እያንዳንዱ የቻለውን ያክል ሙሉ ተሳትፎ ካደረገ፣ ረዳት አቅኚ መሆን የሚችሉ ሁሉ ረዳት አቅኚ ከሆኑና ሌሎች ሰዎች በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ እንዲገኙ በመጋበዝ ረገድ ትጋት ካሳየን ሥራ የሚበዛልን ወቅት ይሆንልናል። በሚያዝያ 2000 ከዚህ በፊት ካደረግነው ሁሉ የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ለአምላክ ውዳሴና ክብር ለማምጣት ስንጥር ይሖዋ አብዝቶ እንዲባርከን ከልብ እንጸልይ!—ዕብ. 13:15
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ረዳት አቅኚዎች
የተገኘው ከፍተኛ ቁጥር:- 1, 104
(መጋቢት 1997)
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ጠቅላላ አስፋፊዎች
የተገኘው ከፍተኛ ቁጥር:- 6, 118
(ነሐሴ 1999)
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች
የተገኘው ከፍተኛ ቁጥር:- 15, 987
(1999)