የሰዎች ሕይወት አደጋ ተጋርጦበታል!
1 የይሖዋ ፈቃድ ‘ሰዎች ሁሉ መዳንን እንዲያገኙ’ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። ይሁን እንጂ በቢልዮን የሚቆጠሩት የምድር ነዋሪዎች የወደፊት ዕጣ የተመካው ለይሖዋ አምላክና በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚመራው መንግሥት ባላቸው ዝንባሌ ላይ እንደሆነ የታወቀ ነው። ተገቢውን ዝንባሌ መያዝ የሚቻለው ‘ትክክለኛ የእውነት እውቀት’ በማግኘት ብቻ ነው። (1 ጢሞ. 2:3, 4) ለአምላክ አዲስ የጽድቅ ዓለም መንገድ ለማዘጋጀት በቅርቡ ክፋት ከምድር ላይ የሚወገድበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቅን በጣም አስፈላጊ የሆነውን ሕይወት አድን ሥራ እንድናከናውን ተልዕኮ ተሰጥቶናል።—ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20፤ ሮሜ 10:13-15
2 ይህን ያህል አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው? ኢየሱስ “ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ . . . ታላቅ መከራ” እንደሚመጣ አስጠንቅቋል። (ማቴ. 24:21) ይህ ታላቅ መከራ የሚደመደመው በአርማጌዶን ነው። (ራእይ 16:16) የማያምኑ ዘመዶቻችንን፣ ጎረቤቶቻችንን፣ የሥራ ባልደረቦቻችንን፣ የትምህርት ቤት ጓደኞቻችንንና ሌሎች የምናውቃቸውን ሰዎች ጨምሮ በጣም ብዙ ሰዎች ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ ካልሰጡ በስተቀር ጥፋት ተደቅኖባቸዋል። ሆኖም ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ለመላው የሰው ዘር ዓለም ያለውን ፍቅር የገለጸውን የአምላክን ምሳሌ በመኮረጅ ምሥራቹን ‘ለሰዎች ሁሉ’ ማዳረስ ይኖርብናል። (ዮሐ. 3:16) ሁሉም፣ አምላክ ለደህንነት ወዳዘጋጀው ስፍራ እንዲሸሹ ለመጋበዝ በቅንዓት መንቀሳቀስ ይገባናል። በስብከቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ በመካፈል የደም ዕዳ እንዳይኖርብን ማድረግ እንችላለን።—ሕዝ. 33:1-7፤ 1 ቆሮ. 9:16
3 ዓላማችን ምንድን ነው? የስብከቱ ሥራ አስፈላጊነት በአምላክ ቃል ውስጥ ጠበቅ ተደርጎ ተገልጿል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው ከአምላክ መንገድ ጋር ተስማምተን እንድንኖር ‘የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል።’ (2 ቆሮ. 5:14) በተጨማሪም መጠበቂያ ግንብ ብዙውን ጊዜ የመስበክ ግዴታችንን ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል። የመንግሥት አገልግሎታችን የስብከቱን ሥራ እንዴት እንደምናከናውን የሚጠቁም መመሪያ በየጊዜው ይዞ ይወጣል። ሽማግሌዎች ሥራውን ያደራጃሉ እንዲሁም እንድንካፈል ማበረታቻ ይሰጡናል። ሌሎች አስፋፊዎችም አብረናቸው እንድናገለግል ይጋብዙናል። አቀራረባችንን ስለመዘጋጀት፣ መጽሔቶችንና ሌሎች ጽሑፎችን ስለማበርከት፣ ተመላልሶ መጠየቆችን ስለማድረግ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ስለመምራት እንዲሁም በእያንዳንዱ አጋጣሚ ምሥክርነት ስለመስጠት ብዙ ተመክረናል። ይህ ሁሉ ሕይወትን የማዳን ዓላማችንን ከግብ ለማድረስ ይረዳናል።—1 ቆሮ. 9:22, 23፤ ኤፌ. 1:13