“በትክክለኛው ጊዜ የተነገረ ቃል”
1 ሕይወት የሚያስገኘውን መልእክት ለሌሎች ሰዎች ማካፈል ፈታኝ ሆኖብሃልን? አድማጮችህን ለመማረክ የተራቀቁ ቃላትን መጠቀም እንዳለብህ ይሰማሃልን? ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የላካቸው “ሄዳችሁም:- መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ” ብሎ ነበር። (ማቴ. 10:7) መልእክቱ ያልተወሳሰበና ለመናገር ቀላል ነበር። ዛሬም ቢሆን ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም።
2 ብዙውን ጊዜ ውይይት ለመጀመር ጥቂት ቃላትን መናገር ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ሲያገኘው “በእውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” በማለት ጠየቀው። (ሥራ 8:30) ‘በትክክለኛው ጊዜ የተነገረው ቃል’ እንዲህ ያለ አስደሳች ውይይት ለማድረግ አስችሏል!—ምሳሌ 25:11 NW
3 አንተም በአገልግሎትህ ተመሳሳይ አቀራረብ መጠቀም ትችላለህ። እንዴት? አስተዋይ በመሆንና ከሁኔታዎች ጋር የሚስማሙ ቃላትን በመምረጥ ነው። አንድ ጥያቄ ጠይቅና ለጥያቄው የሚሰጠውን መልስ አዳምጥ።
4 አንዳንድ መሠረታዊ ጥያቄዎች:- ውይይት ለመጀመር ከሚከተሉት ጥያቄዎች አንዱን መሞከር ትችላለህ:-
◼ “የጌታን ጸሎት (ወይም አባታችን ሆይ) ጸልየህ ታውቃለህ?” (ማቴ. 6:9, 10) ጥቂቱን ክፍል ከጠቀስክለት በኋላ እንደሚከተለው ማለት ትችላለህ:- “አንዳንድ ሰዎች ‘እዚህ ላይ ኢየሱስ ይቀደስ ያለው የአምላክ ስም የትኛው ነው?’ ብለው ይጠይቃሉ። አንዳንዶች ደግሞ ‘ኢየሱስ እንድንጸልይለት የነገረን መንግሥት ምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቃሉ። አንተ ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ አግኝተሃል?”
◼ “‘የሕይወት ትርጉም ምንድን ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቀህ ታውቃለህ?” አምላክ ከሚሰጠው እውቀት ጋር ዝምድና እንዳለው አሳየው።—መክ. 12:13፤ ዮሐ. 17:3
◼ “ሞት የማይኖርበት ጊዜ ይመጣል ብለህ አስበህ ታውቃለህ?” አሳማኝ መልስ ለመስጠት ኢሳይያስ 25:8ን እና ራእይ 21:4ን ተጠቀም።
◼ “በዓለም ላይ ለሚታየው ሁከትና ብጥብጥ ቀላል መፍትሔ ይኖር ይሆን?” አምላክ “ባልንጀራህን . . . ውደድ” ብሎ እንዳስተማረ አሳየው።—ማቴ. 22:39
◼ “ምድራችን አንድ ቀን በጠፈር አካል ተመትታ ትወድም ይሆን?” መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች የሚል ተስፋ እንደያዘ ንገረው።—መዝ. 104:5
5 ምሥራቹን ቀላል፣ ቀጥተኛና ደግነት በሚታይበት መንገድ አቅርብ። ይሖዋ የእውነትን አንድ “ቃል” እንኳ ለሌሎች ለማካፈል የምታደርገውን ጥረት ይባርክልሃል።