ሁላችንም ይሖዋን እና ልጁን እናክብር
ሚያዝያ 8 በሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ የሚገኙ ሁሉ የተሟላ ጥቅም ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?
1 በዛሬው ጊዜ ልዩ ክብር የሚሰጣቸው እነማን ናቸው? ባከናወኑት ተግባር የተነሳ ዓለም ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ሰዎች ናቸው። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ሥራዎቻቸው ቶሎ ይረሳሉ። ሆኖም መላውን የሰው ዘር ስለሚጠቅሙ ተግባራትስ ምን ለማለት ይቻላል? ሚያዝያ 8, 2001 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ በሚከበረው የጌታ እራት ላይ ስንገኝ ለእነዚህ የላቁ ተግባራት ልዩ ትኩረት የምንሰጥበት አጋጣሚ እናገኛለን።
2 የመጨረሻውን ከፍተኛ ክብር ማግኘት የሚገባው ማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና . . . ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል” በማለት መልስ ይሰጣል። (ራእይ 4:11) ይሖዋ ፈጣሪ እንደ መሆኑ መጠን የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ነው። ለዘላለም ሊከበር ይገባዋል!—1 ጢሞ. 1:17
3 የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ዘር ፍጻሜ የሌላቸው በረከቶችን የሚያስገኙ ታላላቅ ሥራዎችን ሠርቷል። ሙሉ በሙሉ አባቱን መስሏል። (ዮሐ. 5:19) ያሳየው ፍጹም ታዛዥነትና በታማኝነት ያከናወነው አገልግሎት “ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም” የሚገባው አድርጎታል። (ራእይ 5:12) አባቱ ንጉሥ አድርጎ በመሾም አክብሮታል። (መዝ. 2:6-8) እኛም ሚያዝያ 8, 2001 የሚውለውን የጌታ እራት ስናከብር አባቱንም ሆነ ልጁን የማክበር አጋጣሚ እናገኛለን።
4 የሚያሳዝነው ግን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለይሖዋና ለልጁ የሚገባቸውን ክብር የሰጡት ሰዎች ቁጥር በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በጣም አነስተኛ መሆኑ ነው። የአምላክ ሕዝብ የነበሩት የጥንት እስራኤላውያን ለይሖዋ እንዲያው የይስሙላ አገልግሎት ብቻ ያቀረቡበት ጊዜ ነበር። ይህ ትልቅ ንቀት ነበር። (ሚል. 1:6) ትክክለኛ አክብሮት ይሖዋና ልጁ ላደረጉልን ነገሮች ባለን ፍቅርና አድናቆት ላይ የተመሠረተ ልባዊ ታዛዥነት ማሳየትን የሚጠይቅ ነው። እንደዚህ ያለ ክብርና ከፍ ያለ ግምት መስጠት ማለት በምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ይሖዋና ኢየሱስ ያላቸውን ሥልጣን በመቀበል አምላካዊ ፍርሃትና ጥልቅ አክብሮት ማሳየት ማለት ነው። የክርስቲያን ጉባኤ ሌሎች ሰዎች እንዲህ እንዲያደርጉ ለማስተማርና ለመርዳት ይጥራል።
5 አክብሮት የምናሳይበት ልዩ አጋጣሚ:- የመታሰቢያው በዓል የይሖዋ ሕዝቦች በየዓመቱ ከፍተኛ ግምት የሚሰጡት ስብሰባ ነው። ይሖዋን የማገልገልና የማክበር ፍላጎት ያለው ማንኛውም ሰው በዚህ ስብሰባ ላይ መገኘት ይኖርበታል። (ሉቃስ 22:19) ከ6 ሚልዮን ምሥክሮች በተጨማሪ ፍላጎት ያላቸው ሌሎች ሰዎችም በበዓሉ ላይ ስለሚገኙ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ከ14 ሚልዮን በላይ ይደርሳል ብለን እንገምታለን። የሰማዩ አባታችንን ለማክበር የሚያስችል እንዴት ያለ ግሩም አጋጣሚ ነው! ምንም እንኳ በዓሉ በኢየሱስ ላይ የሚያተኩር ቢሆንም እሱ ላደረጋቸው ነገሮች የሚሰጠው ክብርና ከፍ ያለ ግምት እሱን የላከውን አባቱን የሚያስከብር ነው።—ዮሐ. 5:23
6 ለዚህ ልዩ በዓል ድጋፍ ለመስጠት ምን ማድረግ እንችላለን? ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎች ከበዓሉ የተሟላ ጥቅም እንዲያገኙ ልንረዳቸው እንችላለን። በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ደጋግመህ ከማሳሰብም በተጨማሪ አስፈላጊ ከሆነ ወደ ስብሰባው ቦታ መምጣት የሚችሉበትን መንገድ በማመቻቸት በደግነት እርዳቸው። የንግግሩን ዓላማ ንገራቸው። ከሌሎች ጋር አስተዋውቃቸው። የሚያዩትና የሚሰሙት ነገር ይሖዋን በማክበር ከእኛ ጋር እንዲተባበሩ ሊገፋፋቸው ይችላል።
7 ፕሮግራሙ በሌሎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አቅልላችሁ አትመልከቱ። አንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል:- “በነበርኩበት ቤተ ክርስቲያን በቁርባን ሥርዓት ላይ ብዙ ጊዜ ተገኝቻለሁ፤ ሆኖም ይህ ፍጹም የተለየ ነው። እናንተ ያደረጋችሁት ልክ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው መሆኑን አስተውያለሁ። እውነት ያለው እናንተ ጋ ነው ብዬ አስባለሁ።” ይህ ሰው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት የጀመረ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ተጠምቋል።
8 አዲሶች እድገት እንዲያደርጉ እርዷቸው:- በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙ አዳዲስ ሰዎችን በማስታወሻ ደብተራችሁ ላይ ጽፋችሁ የተማሩትንና ያዩትን አእምሮን የሚያድስ ነገር ለመከለስ ብዙም ሳትቆዩ ጎብኟቸው። ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማግኘት የሚያስችሏቸው ሌሎች ስብሰባዎችም እንዳሉ ንገሯቸው። “በአምላክ ሕዝብ መካከል ተረጋግተህና ተማምነህ ኑር” የሚለውን የእውቀት መጽሐፍ 17ኛ ምዕራፍ አብሮ ማየቱ በጉባኤው አማካኝነት ሰፊ መንፈሳዊ ዝግጅት ያለላቸው መሆኑን እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። የይሖዋ ሕዝቦች ያላቸውን አንድነት፣ ደስታና የአገልግሎት ቅንዓት በገዛ ዓይናቸው ማየት እንዲችሉ መላው የወንድማማች ማኅበር የተባለውን ቪዲዮ እንዲመለከቱ ዝግጅት አድርጉላቸው!
9 ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ይሖዋን ስለሚያከብሩበትና ከፍ ከፍ ስለሚያደርጉበት መንገድ መማራቸው አስፈላጊ ነው። ከልብ የመነጨ ጸሎት ይሖዋን ከማስደሰቱም በተጨማሪ ዘወትር በመንፈሳዊ እንድንታደስ እንደሚያደርግ ግለጽላቸው። (1 ዮሐ. 5:14) አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ከተባለው ብሮሹር ከትምህርት 8 እስከ 12 ድረስ ያለውን በመጠቀም ለይሖዋ ክብር ስለሚያመጡ ባሕርያት መግለጽ ትችላለህ። የይሖዋ ምሥክሮች በተባለው ብሮሹር ከገጽ 30-1 ላይ የተጠቀሱትን ሐሳቦች በመጠቀም አዲሶች በስብከቱ ሥራ ተሳትፎ በማድረግ ይሖዋን ማክበር ስለሚችሉበት አጋጣሚ እንዲያስቡ አበረታታቸው።
10 ለኢየሱስ መሥዋዕትና ላገኘነው የእርሱ ደቀ መዛሙርት ሆነን የማገልገል መብት ያለን አድናቆት አባቱን ከማስከበሩም በላይ ለሌሎች በረከት ያስገኝላቸዋል። ኢየሱስ “የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል” በማለት ቃል ገብቷል።—ዮሐ. 12:26