አስቀድሞ ዕቅድ ማውጣት—ምን ለማድረግ?
1 ሁላችንም ወደፊት ማድረግ ስለምንፈልጋቸው ነገሮች እናስባለን። ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች አምላክ በሚያዘጋጀው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም ለመኖር በተስፋ ይጠባበቃሉ። ሆኖም ይህን ተስፋ ከልባችን ነቅለው ሊያወጡ የሚችሉ ተጽእኖዎች ያጋጥሙናል። ሕይወታችን በአምላክ መንግሥት ፍላጎቶች ላይ እንዲያተኩር እንዲሁም ሐሳባችን ፈታኝ በሆነው የሥጋ ምኞት እንዳይከፋፈልብን ብርቱ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል።—1 ዮሐ. 2:15-17
2 የመንፈሳዊ ሰዎች ምኞት ለዚህ ዓለም እንቆቅልሽ ነው። (1 ቆሮ. 2:14) የቀረው የሰው ዘር ዝና፣ ሥልጣን ወይም ሃብት ሲያሳድድ እኛ መንፈሳዊ ሃብት ለማግኘት እንጣጣራለን። (ማቴ. 6:19-21) አስተሳሰባችን ዓለም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ካለው አስተሳሰብ ጋር እንዲመሳሰል ለማድረግ የምንሞክር ከሆነ መንፈሳዊ ግባችን ላይ መድረስ እንችላለንን? ብዙም ሳይቆይ ልባችን በዓለማዊ ጉዳዮች ይዋጣል። ይህ እንዳይደርስብን መከላከል የምንችለው እንዴት ነው?
3 “ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት”:- የወደፊቱ ሕይወታችንን በመንግሥቱ ጉዳዮች ዙሪያ እየገነባን መሆን አለመሆኑን የምንመዝንበት አንዱ መንገድ አነጋገራችንን መመርመር ነው። ዘወትር የምናወራው ስለ ቁሳዊ ነገሮችና ስለ ሰብዓዊ ጥቅሞች ነውን? ከሆነ ልባችን በመንፈሳዊ እሴቶች ላይ ከማተኮር እያፈገፈገ እንዳይሆን ማጤን ይኖርብናል። ‘ምኞቱን እንዲፈጽም ለሥጋ ከማሰብ ይልቅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመልበስ’ ትልቅ ትኩረት መስጠት ያስፈልገን ይሆናል።—ሮሜ 13:14
4 ወጣቶች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ከወዲሁ እቅድ በማውጣት ‘ክርስቶስን መልበስ’ ይችላሉ። የዘወትር አቅኚ የመሆን ግብ የነበረው አንድ ወጣት ያደገው ወንዶች ልጆች የገንዘብ አቅማቸውን ማጠናከር አለባቸው የሚል አመለካከት በሰፈነበት ባህል ውስጥ ነበር። ስለሆነም ከሚገባው በላይ በሥራ ከመጠመዱ የተነሳ በስብሰባዎች ላይ የሚገኘውና በመስክ አገልግሎት የሚካፈለው እንዲያው ለይስሙላ ያህል ብቻ ሆነ። በማቴዎስ 6:33 ላይ በሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ላይ መተማመን ከጀመረ በኋላ ግን ማብቂያ ከሌለው እሽክርክሪት ወጥቶ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመረ። አሁን በንጹሕ ሕሊና ይሖዋን ‘በሙሉ ኃይሉ’ በማገልገል ላይ እንዳለ ተናግሯል።
5 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ እቅድ ማውጣት ጥበብ እንደሆነ ይናገራል። (ምሳሌ 21:5 NW ) ሁላችንም ለአምላክ ፈቃድ የላቀውን ሥፍራ በመስጠት እንዲህ እናድርግ።—ኤፌ. 5:15-17