ጥሩ ጎረቤት በመሆን ምሥክርነቱን ስጡ
1 ኢየሱስ “ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 22:39) ለእምነት ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ‘መልካም እንደምታደርጉ’ ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም ፍቅራችሁን በአካባቢያችሁ ለሚኖሩ ሰዎች ማስፋት ትችሉ ይሆን? (ገላ. 6:10) በምን በምን መንገዶች?
2 ማንነታችሁን በማሳወቅ:- ጎረቤቶቻችሁ የይሖዋ ምሥክር መሆናችሁን ያውቃሉ? የማያውቁ ከሆነ ወደ መስክ አገልግሎት ስትሄዱ ለምን አታነጋግሯቸውም? የሚያስደንቅ ውጤት ታገኙ ይሆናል! ይበልጥ አመቺ ከሆነላችሁ ደግሞ መደበኛ ባልሆነም መንገድ ለመመሥከር ሞክሩ። ከቤት ወጣ ስትሉ በግቢያቸው ውስጥ ሲሠሩ ወይም መንገድ ላይ ሲንሸራሸሩ ትመለከቱ ይሆናል። ሞቅ ባለ ፈገግታ ቀርባችሁ አነጋግሯቸው። ስለምታምኑባቸው ነገሮች፣ የመንግሥት አዳራሹ የት እንደሚገኝና ስብሰባዎች እንዴት እንደሚካሄዱ እንዲሁም ከጎረቤቶቻችሁ እነማን በስብሰባዎች ላይ እንደሚገኙ እንዲያውቁ ለማድረግ ሞክሩ። በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ጋብዟቸው። ምሥራቹን ለምታውቋቸው ሰዎች በሙሉ ለመንገር ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ።—ሥራ 10:42፤ 28:23
3 መልካም ጠባይ በማሳየት:- የምታሳዩት ወዳጃዊ ጠባይ ስለ ማንነታችሁ ጥሩ አድርጎ የሚናገር ሲሆን ምሥክርነት ለመስጠትም በር ሊከፍትላችሁ ይችላል። ‘የአምላክንም ትምህርት ያስመሰግናል።’ (ቲቶ 2:7, 9) ለጎረቤቶቻችሁ ልባዊ አሳቢነት አሳዩ። ወዳጃዊና የሰው ችግር የሚገባችሁ ሁኑ። ብቻቸውን መሆን ወይም የሚረብሽ ድምፅ እንዲኖር በማይፈልጉበት ጊዜ ምርጫቸውን አክብሩላቸው። አንዳቸው ከታመሙ አሳቢነት በማሳየት እርዳታ ለመስጠት ራሳችሁን አቅርቡ። አንድ ቤተሰብ ቤት ቀይሮ ወደ እናንተ አካባቢ ከመጣ ገባ ብላችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ በሏቸው። እንደዚህ ያለው ደግነት ስለ እናንተ ጥሩ ስሜት ያሳድርባቸዋል እንዲሁም ይሖዋን ያስደስታል።—ዕብ. 13:16
4 ንብረታችሁን በእንክብካቤ በመያዝ:- ጥሩ ጎረቤት መሆን ቤትን በደንብ መያዝን የሚጨምር ነው። ቤትንና አጥር ግቢን ንጹሕ አድርጎ መያዝ ራሱ ምሥክርነት ነው። ሆኖም የቆሸሸ ወይም በየቦታው የወዳደቀ ነገር የሚታይበት ቤት ሌሎች የመንግሥቱን መልእክት እንዳይሰሙ እንቅፋት ሊሆን ይችላል። ስለሆነም ቤታችሁን፣ ግቢያችሁንና መኪናችሁን በንጽሕና መያዝና ተገቢውን ጥገና ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው።
5 ከክርስቲያን ጉባኤ ውጪ ላሉ ሰዎች አሳቢነት ማሳየት ባልንጀሮቻችሁን እንደምትወዱ ያንጸባርቃል። ውጤቱስ ምን ሊሆን ይችላል? አንዳንዶች ‘መልካም ሥራችሁን ተመልክተው አምላክን ማክበር’ ይጀምሩ ይሆናል።—1 ጴጥ. 2:12