“በመድረክ ላይ እንዳለ ተዋናይ” ናችሁ!
1 ሐዋርያው ጳውሎስ “በዓለም፣ በመላእክትና በሰዎች ፊት በመድረክ ላይ እንዳለ ተዋናይ ሆነናልና” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 4:9 NW ) ይህ ምን ማለት ነው? በዛሬ ጊዜ ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ ሊነካን የሚገባው እንዴት ነው?
2 ለአንድ የቆሮንቶስ ሰው “በመድረክ ላይ እንዳለ ተዋናይ” የሚለው አነጋገር እንደ ወንጀለኛ የሚታዩ ሰዎች በጭካኔ ከመገደላቸው በፊት በሺህ በሚቆጠሩ ተመልካቾች ፊት እንዲያልፉ የሚደረግበትን የሮማውያን የግላድያተር ግጥሚያ የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ሳያስታውሰው አይቀርም። በተመሳሳይ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ስለ መንግሥቱ በመመስከራቸው ምክንያት የጭካኔ ድርጊት ሲፈጸምባቸው ብዙ ሰዎችና መላእክት ተመልክተዋል። (ዕብ. 10:32, 33) በእነርሱ የአቋም ጽናት የተነኩት ተመልካቾች ጥቂት አይደሉም። ዛሬም የእኛ ጽናት በዘመናችን የዓለም መድረክ ላይ ተመሳሳይ ውጤት አለው። እንደ ተዋናይ የምንታየው ለእነማን ነው?
3 በዓለምና በሰዎች ፊት:- አንዳንድ ጊዜ መገናኛ ብዙሃን ስለ ይሖዋ ሕዝቦች እንቅስቃሴ ይዘግባሉ። ስለ ሥራችን የሚቀርበውን እውነተኛና ከአድሎ የጸዳ መልካም ወሬ ብናደንቅም ስማችንን ለማጥፋት የሚፈልጉ ሰዎች በየጊዜው ክፉ ወሬ ሊያናፍሱብን እንደሚችሉ እንጠብቃለን። ‘ክፉም ሆነ መልካም’ ቢወራብንም የአምላክ አገልጋዮች መሆናችንን ከማስመስከር ወደኋላ ማለት አይገባንም። (2 ቆሮ. 6:4, 8) ቅን ልብ ላላቸው ተመልካቾች የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት መሆናችን በግልጽ ይታያቸዋል።
4 በመላእክት ፊት:- መንፈሳዊ ፍጥረታትም ይመለከቱናል። ዲያብሎስና አጋንንቱም ‘ስለ ኢየሱስ የሚሰጠውን ምሥክርነት’ ለማስተጓጎል በመፈለግ “በታላቅ ቁጣ” ይመለከቱናል። (ራእይ 12:9, 12, 17) የታመኑ የአምላክ መላእክትም የሚመለከቱን ሲሆን አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ ሲገባ ሲያዩ ይደሰታሉ። (ሉቃስ 15:10) መላእክት አገልግሎታችንን የሚያዩት ዛሬ በምድር ላይ ከሚሠሩት ሥራዎች ሁሉ ይበልጥ አጣዳፊና ጠቃሚ ሥራ እንደሆነ አድርገው መሆኑን ማወቃችን ሊያበረታን ይገባል!—ራእይ 14:6, 7
5 ተቃውሞ ሲያጋጥማችሁ ወይም አገልግሎታችሁ ውጤት እንዳላስገኘ ሲሰማችሁ የጽንፈ ዓለሙ ትኩረት እንዳረፈባቸሁ አስታውሱ። በታማኝነት የምታሳዩት ጽናት ስለ አቋም ጽናታችሁ ብዙ ይናገራል። ውሎ አድሮ ‘ለእምነት የምታደርጉት መልካም ተጋድሎ የዘላለምን ሕይወት አጥብቃችሁ እንድትይዙ’ ያስችላችኋል።—1 ጢሞ. 6:12