በመንፈሳዊ ምን ያህል በሚገባ ትመገባለህ?
1 ‘ሰው ካለህል ምን ያህል’ የሚል አባባል አለ። እውነት ነው፤ የአመጋገብ ልማዳችን በአካላዊ ጥንካሬያችንና በጤናችን ላይ ተጽዕኖ አለው። በተመሳሳይም ኢየሱስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ብሎ ስለ ተናገረ መንፈሳዊ የአመጋገብ ልማዳችን በእኛ ላይ በጎ ወይም መጥፎ ተጽዕኖ ይኖረዋል። (ማቴ. 4:4) እንግዲያው በመንፈሳዊ ምን ያህል በሚገባ ትመገባለህ? አጉል መራጭ ነህን? በችኮላ ቀመስ ቀመስ እያደረግህ ነው የምትመገበው? ወይስ ዘወትር የተመጣጠኑና ገንቢ የሆኑ መንፈሳዊ ምግቦችን ለመመገብ በቂ ጊዜ ትመድባለህ?
2 የአመጋገብ ልማድህን መርምር:- ይሖዋ ‘በታማኝና ልባም ባሪያው’ አማካኝነት “በጊዜው” “ታላቅ የሰባ ግብዣ” ያቀርባል። (ማቴ. 24:45፤ ኢሳ. 25:6) ከእነዚህ ፍቅራዊ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ እንድንሆን በመንፈሳዊ በደንብ ለመመገብ ጥረት ማድረግ አለብን።
3 ራስህን እንዲህ ብለህ ልትጠይቅ ትችላለህ:- ‘የዕለቱን ጥቅስና በጥቅሱ ላይ የተሰጠውን ሐሳብ በየቀኑ አነብባለሁ? መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የማንበብና የማሰላሰል ልማድ አለኝ? የሚጠናውን ጽሑፍ አስቀድሜ በማንበብ ለጉባኤ ስብሰባዎች እዘጋጃለሁ? የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን የተባለውን መጽሐፍ ጨምሮ በቅርብ የወጡትን ጽሑፎች አንብቤያለሁ?’
4 ኢየሱስ “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው . . . ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው፣ ይጠግባሉና” በማለት ተስፋ ሰጥቶናል። (ማቴ. 5:3, 6 NW ) ስለዚህ አእምሮአችሁንና ልባችሁን በአምላክ እውቀት በመሙላት በመንፈሳዊ በደንብ ተመገቡ።