የ2002 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት
1 ብዙ ሰዎች የመናገር ችሎታን አቅልለው ይመለከቱታል። ይሁን እንጂ አንደበት የይሖዋ ስጦታ ነው። ከሌሎች ጋር የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ እንዲሁም ሐሳባችንንና ስሜታችንን ለመግለጽ ያስችለናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ አምላካችንን ልናወድስበት እንችላለን።—መዝ. 22:22፤ 1 ቆሮ. 1:4-7
2 ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች የይሖዋን ስም ለማወጅ እንዲችሉ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሥልጠና ይሰጣቸዋል። (መዝ. 148:12, 13) የ2002 የትምህርት ቤቱ ፕሮግራም በግል ሕይወታችንም ሆነ በአገልግሎት ሊጠቅሙን የሚችሉ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳዮች ይሸፍናል። ለትምህርት ቤቱ በመዘጋጀትና ተሳትፎ በማድረግ እውቀታችንንና የአምላክን ቃል የማስተማር ችሎታችንን ማሳደግ እንችላለን።—መዝ. 45:1
3 መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ አንብቡ:- ብዙውን ጊዜ በቅርብ ማግኘት በምንችልበት ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስን የምንይዝ ከሆነ ያለንን ማንኛውንም ነጻ ጊዜ ለንባብ ልንጠቀምበት እንችላለን። አብዛኞቻችን በቀኑ ውስጥ በዚህ መንገድ ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው ጥቂት ትርፍ ደቂቃዎች ይኖሩናል። በየዕለቱ ቢያንስ አንድ ገጽ ማንበብ እንዴት ጠቃሚ ነው! እንዲህ በማድረግ ከትምህርት ቤቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ጋር እኩል መጓዝ እንችላለን።—መዝ. 1:1-3
4 መጽሐፍ ቅዱስን ጥሩ አድርጎ የማንበብ ችሎታ የአድማጮቻችንን ልብ ለመንካትና ይሖዋን እንዲያወድሱ ለማነሳሳት ሊረዳን ይችላል። ክፍል ቁጥር 2ን የሚያቀርቡት ወንድሞች የተመደበውን የንባብ ክፍል ጮክ ብለው በማንበብ ደግመው ደጋግመው መለማመድ ይኖርባቸዋል። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ክፍሉን ያቀረበውን ወንድም ያመሰግናል እንዲሁም ንባቡን ለማሻሻል የሚረዱትን ሐሳቦች ይጠቁመዋል።
5 በማመራመር መጽሐፍ ተጠቀም:- ክፍል ቁጥር 3 እና 4 ከማመራመር መጽሐፍ ላይ የሚቀርቡ ናቸው። አብዛኞቻችን ይህን ግሩም የሆነ መሣሪያ በመስክ አገልግሎት ላይ ለመጠቀም ይበልጥ ንቁ መሆን ያስፈልገን ይሆናል። ክፍሎቹን የሚያቀርቡት እህቶች ለአገልግሎት ክልሉ ተስማሚ የሆነ መቼት መምረጥ ይኖርባቸዋል። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ስለሚያስተምሩበትና ቅዱሳን ጽሑፎችን ስለሚጠቀሙበት መንገድ ልዩ ትኩረት መስጠት አለበት።
6 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሁላችንም አምላክ የሰጠንን የመናገር ችሎታ በመጠቀም ምሥራቹን ማወጃችንንና ታላቁን አምላካችንን ይሖዋን ማወደሳችንን እንድንቀጥል የሚረዳን እንዲሆን እንመኛለን!—መዝ. 34:1፤ ኤፌ. 6:19