የ2000 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት
1 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለይሖዋ ሕዝቦች ትልቅ በረከት ሆኖ ቆይቷል። ባለፉት 50 ዓመታት ትምህርት ቤቱ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሕዝብ ተናጋሪነትና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማስተማር ችሎታቸው ረገድ መሻሻል እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። (መዝ. 145:10-12፤ ማቴ. 28:19, 20) ትምህርት ቤቱ በምን መንገድ እገዛ እንዳደረገልህ ማሰብ ትችላለህ? በ2000ም በትምህርት ቤቱ ሙሉ በሙሉ ከተሳተፍክና የሚሰጥህን ምክር ከሠራህበት ከትምህርት ቤቱ መጠቀምህን ትቀጥላለህ።
2 ለ2000 በወጣው የትምህርት ቤቱ ፕሮግራም የመጀመሪያ ገጽ ላይ ክፍሎቹን በተመለከተ የቀረቡት መመሪያዎችና የምንጠቀምባቸው ጽሑፎች ተዘርዝረዋል። ለእያንዳንዱ ክፍል የተመደበው ጊዜ፣ ክፍሉ የሚገኝበት ጽሑፍ፣ ትምህርቱ እንዴት መቅረብ እንዳለበት፣ እንዲሁም ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ሠፍረዋል። እባካችሁ፣ መመሪያዎቹን በጥንቃቄ ለማንበብ ጊዜ መድቡ፤ ሥራ ላይም አውሏቸው።
3 ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ በትምህርት ቤቱ ፕሮግራም ላይ ሁለት የተለያዩ ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራሞች ቀርበዋል። አንደኛው ወደ አምስት ገጾች ገደማ የሚሸፍነው መደበኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጎላ ያሉ ነጥቦች የሚቀርበው ከዚህ የንባብ ክፍል ነው። ሌላው ተጨማሪ የንባብ ፕሮግራም ሲሆን ይህም ከመደበኛው ንባብ በእጥፍ ይሰፋል። ይህን ፕሮግራም በመከተል በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር አንብባችሁ መጨረስ ትችላላችሁ። አንዳንዶች በተጨማሪ የንባብ ፕሮግራሙ ላይ ከተመደበው አልፈው ማንበብ እንደሚፈልጉና ሌሎች ደግሞ ከፕሮግራሙ እኩል መሄድ ሊያቅታቸው እንደሚችል የታወቀ ነው። ራሳችሁን ከሌሎች ጋር ከማወዳደር ይልቅ ማድረግ በቻላችሁት ነገር ተደሰቱ። (ገላ. 6:4) ዋናው ቁም ነገር የአምላክን ቃል በየዕለቱ ማንበቡ ነው።—መዝ. 1:1-3
4 በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ለመመዝገብ የትምህርት ቤቱን የበላይ ተመልካች ማነጋገር አለባችሁ። እባካችሁ፣ የሚሰጣችሁን ክፍል በቁም ነገር ተመልከቱት፤ እንዲሁም በሆነው ባልሆነው ክፍሉን ሳታቀርቡ አትቅሩ። ትምህርት ቤቱ የይሖዋ ዝግጅት እንደሆነ በመቁጠር አድናቆት አሳዩ። በደንብ ተዘጋጁ፣ ክፍሉ የተወሰደበትን ጽሑፍ ጥሩ አድርጋችሁ አንብቡ እንዲሁም ልባዊ በሆነ መንገድ ሐሳባችሁን ግለጹ። እንዲህ በማድረግ በዓይነቱ ልዩ ከሆነው ከዚህ ትምህርት ቤት የተሟላ ጥቅም ታገኛላችሁ።