“ስጦታ የሆኑ ወንዶች” የአምላክን መንጋ በትጋት ይጠብቃሉ
1 ይሖዋ በልጁ በኩል ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶችን’ በመስጠት እንዴት ያለ ፍቅራዊ ዝግጅት አድርጎልናል! (ኤፌ. 4:8, 11, 12 NW ) እነዚህ ወንዶች የአምላክን መንጋ በትጋትና በንቃት መጠበቅን ጨምሮ ብዙ ኃላፊነቶች አሉባቸው። (1 ጴጥ. 5:2, 3) ሁላችንም ከዚህ በጣም አስፈላጊ ከሆነ ዝግጅት ጥቅም እናገኛለን። እነዚህ ወንዶች ችግር ለገጠማቸውም ሆነ ለአዲሶች፣ አንድ ዓይነት ድካም ላለባቸውም ሆነ ለባዘኑ መንፈሳዊ ደህንነት ከልባቸው ያስባሉ።—ፊልጵ. 2:4፤ 1 ተሰ. 5:12-14
2 የሚረብሹ የዓለም ክስተቶች ስጋት በሚፈጥሩበት ጊዜ እነዚህ የበታች እረኞች “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ” ይሆናሉ። ዝለን ወይም ሸክማችን ከብዶን መጽናኛ ማግኘት በምንፈልግበት ጊዜ ያነቃቁናል። እንደነዚህ ባሉ ጊዜያት “በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ” ወይም “በበረሀም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ” ይሆኑልናል።—ኢሳ. 32:2
3 የማያዘወትሩትንና አገልግሎት ያቆሙትን ማበረታታት፦ ሽማግሌዎች የማያዘወትሩ ወይም አገልግሎት ያቆሙ አስፋፊዎች በሁሉም የጉባኤ እንቅስቃሴዎች ቋሚ ተሳትፎ ማድረግ ይችሉ ዘንድ ለማበረታታት ልዩ ጥረት ያደርጋሉ። ፍቅራዊ የእረኝነት ጉብኝቶች ብዙዎች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው እንዲገኙና በመንፈሳዊ ታንጸው በመስክ አገልግሎት በድጋሚ መካፈል እንዲጀምሩ ረድተዋቸዋል። ሽማግሌዎች የሚያደርጓቸው እነዚህ ሁሉ ጥረቶች የይሖዋን ፍቅራዊ አሳቢነትና የኢየሱስ ክርስቶስን ንቁ አመራር ያንጸባርቃሉ። ኢየሱስ ከመንጋው መካከል ለባዘነ ወይም ለጠፋ ለእያንዳንዱ በግ እንዲህ ዓይነት አሳቢነት በማሳየት ምሳሌ ትቷል።—ማቴ. 18:12-14፤ ዮሐ. 10:16, 27-29
4 የበታች እረኞች አንዳንዶች በመንፈሳዊ እየተንሸራተቱ እንዳሉ የሚጠቁሙ ምልክቶችን በንቃት ይከታተላሉ። ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ምልክት የታየባቸው፣ በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው የማይገኙ ወይም በመስክ አገልግሎት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የቀነሱ መንፈሳዊ እገዛ የሚያስፈልጋቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ሽማግሌዎች ዓለማዊ መንፈስ የሚያንጸባርቅ አለባበስና አበጣጠር መከተል የጀመሩትን ወይም ጉባኤውን የመተቸት ዝንባሌ ያዳበሩትን ለመርዳት ዝግጁ ናቸው። አሳቢ የሆኑ የበላይ ተመልካቾች ከልብ በመነጨ አሳቢነትና በርኅራኄ ስሜት እነዚህ ሰዎች ለይሖዋ የነበራቸውን ፍቅር እንዲያቀጣጥሉ ለመርዳት ‘የገዛ ነፍሳቸውን ለማካፈል’ ፈቃደኞች ናቸው።—1 ተሰ. 2:8
5 ባለፉት ዓመታት ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ አንዳንድ ክርስቲያኖች በጤና እክል፣ በኢኮኖሚ ችግር ወይም በቤተሰብ ተጽዕኖ ምክንያት በመንፈሳዊ ተዳክመው ከጉባኤው ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አቋርጠዋል። ሽማግሌዎች ነቃፊ ሳይሆኑ ይሖዋ ለበጎቹ ሁሉ እንደሚያስብና በአስቸጋሪ ጊዜያት እንደሚረዳቸው በደግነት ያረጋግጡላቸዋል። (መዝ. 55:22፤ 1 ጴጥ. 5:7) ንቁ የሆኑ የመንጋው እረኞች ‘ወደ እግዚአብሔር ከቀረቡ እሱ ወደ እነሱ እንደሚቀርብና’ ማጽናኛና እረፍት እንደሚሰጣቸው እንዲገነዘቡ ሊረዷቸው ይችላሉ።—ያዕ. 4:8፤ መዝ. 23:3, 4
6 አቅመ ደካማ የሆኑትን ከፍ አድርጎ መመልከት፦ አፍቃሪ የበታች እረኞች በቀላሉ ትኩረት ሊነፈጋቸው ለሚችሉ ሰዎችም ያስባሉ። በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ አቅመ ደካማ የሆኑ፣ የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ወይም የአካል ጉዳተኞች ሊኖሩ ይችላሉ። ያሉባቸው የአቅም ገደቦች የመንግሥቱን መልእክት በማወጁ ሥራ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ውስን እንደሚያደርግባቸው የታወቀ ነው። ምናልባት ምሥክርነቱን መስጠት የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ሊጠይቋቸው ለሚመጡ ሰዎች፣ ለሌሎች ሕመምተኞች ወይም ለአስታማሚዎቻቸው ብቻ ሊሆን ይችላል። የሆነ ሆኖ ማከናወን የሚችሉት ምንም ያህል ይሁን አጠቃላዩን የስብከት ሥራ የሚደግፍ ከፍ ያለ ዋጋ እንዳለው ተደርጎ ይታያል። (ማቴ. 25:15) ምሥክርነቱን በመስጠት ያሳለፉት ሰዓት 15 ደቂቃ ብቻ እንኳ ቢሆን ይህ ሪፖርት ሊደረግ ይገባል፤ እነሱም አዘውታሪ የመንግሥቱ አስፋፊ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠራሉ።
7 ‘ስጦታ የሆኑት ወንዶች’ በተለይ በዚህ የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ሰሞን የወንድሞቻቸውን መንፈሳዊነት በንቃት ይከታተላሉ። የባዘኑ ከጉባኤው ጋር ሞቅ ያለ ቅርርብ መፍጠር የሚያስገኘውን ደስታና የአእምሮ ሰላም በድጋሚ እንዲያገኙ ለመርዳት ልዩ ጥረት ለማድረግ ይህ ወቅት ለሽማግሌዎች ምንኛ ተስማሚ ጊዜ ነው! እንደነዚህ ያሉ ‘በእምነት የሚዛመዱን’ ሰዎች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘትና በመስክ አገልግሎት በመካፈል በቤዛዊው መሥዋዕት ላይ እምነት እንዳላቸው በድጋሚ ሲያረጋግጡ ስንመለከት እንደሰታለን።—ገላ. 6:10 NW፤ ሉቃስ 15:4-7፤ ዮሐ. 10:11, 14