ይሖዋን እንዲያከብሩት ሌሎችን መርዳት
1 “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት” የሚል እጅግ አስፈላጊ መልእክት በምድር ዙሪያ ላሉ ሰዎች በመታወጅ ላይ ነው። (ራእይ 14:6, 7) ይህን መልእክት በማወጁ ሥራ የመካፈል መብት አግኝተናል። ሰዎች ይሖዋን እንዲፈሩትና እንዲያመልኩት ስለ እርሱ ምን ማወቅ አለባቸው?
2 ስሙን:- ሰዎች እውነተኛውን አንድ አምላክ ዛሬ ከሚመለኩት በርካታ የሐሰት አማልክት በስም ለይተው ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። (ዘዳ. 4:35፤ 1 ቆሮ. 8:5, 6) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የይሖዋን ገናና ስም ከ7, 000 ጊዜ በላይ ተጠቅመዋል። ለሰዎች በምንመሰክርበት ጊዜ ስለ አምላክ ስም መቼ ብንነግራቸው እንደሚሻል ማሰባችን ተገቢ ነው። ይህ ማለት ግን ስሙን እንደብቃቸዋለን ወይም ለመጥራት እናፍራለን ማለት አይደለም። አምላክ መላው የሰው ዘር ስሙን እንዲያውቅ ይፈልጋል።—መዝ. 83:18 NW
3 ባሕርያቱን:- ሰዎች አምላክን ማክበር እንዲችሉ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። ልዩ ስለሆነው ፍቅሩ፣ አቻ ስለሌለው ጥበቡ፣ ስለማይጓደለው ፍትሑ፣ ሁሉን ቻይ ስለሆነው ኃይሉ እንዲሁም ስለ ምሕረቱ፣ ስለ ፍቅራዊ ደግነቱና ስለ ሌሎች ግሩም ባሕርያቱ ልንነግራቸው ይገባል። (ዘጸ. 34:6, 7) በተጨማሪም ሕይወታቸው የተመካው የይሖዋን ሞገስ በማግኘታቸው ላይ እንደሆነ ተገንዝበው ለአምላክ ጤናማ ፍርሃት ማሳደርንና እርሱን ማክበርን መማር አለባቸው።—መዝ. 89:7
4 ወደ አምላክ መቅረብ:- ከሚመጣው የአምላክ ፍርድ በሕይወት ለመትረፍ ሰዎች የይሖዋን ስም በእምነት መጥራት አለባቸው። (ሮሜ 10:13, 14፤ 2 ተሰ. 1:8) ይህ ደግሞ ስሙንና ባሕርያቱን በማወቅ ብቻ ከመወሰን የበለጠ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። ሰዎች በሙሉ ልባቸው በእርሱ በመታመን ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና እንዲመሠርቱ ልንረዳቸው ይገባል። (ምሳሌ 3:5, 6) የተማሩትን በሥራ ላይ ሲያውሉ፣ ወደ አምላክ ልባዊ ጸሎት ሲያቀርቡና እርሱ የሚያደርግላቸውን እርዳታ በሕይወታቸው ውስጥ ሲመለከቱ እምነታቸው የሚጠናከር ሲሆን ይህም ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርቡ ይረዳቸዋል።—መዝ. 34:8
5 የአምላክን ስም በቅንዓት የምናውጅና ሰዎች በእርሱ እንዲታመኑና እንዲፈሩት የምንረዳቸው እንሁን። ሌሎች በርካታ ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁትና ‘የመዳናቸው አምላክ’ አድርገው እንዲያከብሩት መርዳት እንችል ይሆናል።—መዝ. 25:5