ይሖዋን ፍሩ ቅዱስ ስሙንም አክብሩ
“ይሖዋ ሆይ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማነው?”—ራእይ 15:4
1, 2. (ሀ) ይሖዋ በ1991 የሰማይ መስኮቶችን የከፈተው እንዴት ነው? (ለ) አንድ ታማኝ ሚስዮናዊ “ይሖዋን ፍሩ” የሚል ምክር እንዲሰጥ ያነሣሣው ምን ያጋጠመው የሕይወት ተሞክሮ ነው? (የ1991 የዓመት መጽሐፍ ገጽ 187-89ን ተመልከቱ።
ይሖዋ ‘የሰማይን መስኮት ከፍቶ ምንም አይነት ችግር እስከማይኖር ድረስ በረከትን አትረፍርፎ አፈሰሰ።’ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለይሖዋ ምሥክሮች ስለተፈጸሙት ነገሮች ስንናገር እነዚህ ቃላት ተደጋግመው ተፈጽመዋል ለማለት እንችላለን። (ሚልክያስ 3:10) ለምሳሌ ያህል በምድር ዙሪያ በደቡብ አሜሪካ በሳኦ ፓውሎ (ነሐሴ 17-19, 1991)፣ በሩቅ ምሥራቅ በማኒላ፣ በታይፔይና በባንኮክ፣ በምሥራቅ አውሮፓ በቡዳፔስት፣ በፕራግና በዛግሬብ (ነሐሴ 16-18, 1991) በተደረጉት የ“ንፁሕ ልሳን” እና የ“ነፃነት አፍቃሪዎች” ስብሰባዎች ላይ የተገኙ በእንግድነት የመጡ ምሥክሮችና የአካባቢው ተሰብሳቢዎች በልዩ ስብሰባዎቹ ላይ በታየው ክርስቲያናዊ ወዳጅነት ስሜታቸው ተነክቶ ነበር።
2 ከባሕር ማዶ የመጡት ልኡካን በእነዚህ አገሮች ለረዥም ዓመታት በታማኝነት ጸንተው ከቆዩት ምሥክሮች ጋር ለመገናኘት መቻላቸው በጣም አስደስቶአቸው ነበር። ለምሳሌ በባንግኮክ በተደረገው ስብሰባ ላይ በአንድ ወቅት በታይላንድ ብቸኛ የመንግሥት አስፋፊ ሆኖ ያገለግል የነበረው ፍራንክ ዴዋር ስለ 58 ዓመት የሚሲዮናዊነት አገልግሎቱ ተናግሯል። ሥራው ከፓስፊክ ደሴቶች እስከ ደቡባዊ ምሥራቅ እስያና እስከ ቻይና ሳይቀር ተዳርሷል። የመርከብ መስጠም፣ የዱር አራዊት፣ የበረሃ በሽታዎች አደጋና የጃፓን ወታደራዊ ገዥዎች ጭካኔ ደርሶበታል። ለተሰብሳቢዎቹ ምን ምክር እንደሚሰጥ ሲጠየቅ የሰጠው መልስ በጣም አጭር ነበር፦ “ይሖዋን ፍሩ!” አለ።
3. አምላካዊ ፍርሃት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?
3 አዎ፣ ይሖዋን ፍሩ። ሁላችን ይህን ጤናማ ፍርሃት መኮትኮት በጣም ያስፈልገናል። “የጥበብ መጀመሪያ ይሖዋን መፍራት ነው።” (መዝሙር 111:10) ይህ ፍርሃት የሚያርበተብት ወይም የሚያሸማቅቅ ፍርሐት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአድናቆት ለሚመስጠው ግርማውና ለአምላካዊ ባሕርያቱ ቃሉን በማጥናት በምናገኘው ጥልቅ ማስተዋል ላይ የተመሠረተ ከፍተኛ የሆነ ጥልቅ አክብሮት ማሳየት ነው። በራእይ 15:3, 4 የሙሴና የበጉ መዝሙር ወይም ቅኔ “ሁሉን የምትገዛ ይሖዋ አምላክ ሆይ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው። የዘላለም ንጉሥ ሆይ መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው። ይሖዋ ሆይ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማነው?” ይላል። ይሖዋ ለአምላኪዎቹ ታማኝ በመሆኑ “ይሖዋን ለሚፈሩና ስሙንም ለሚያስቡ የመታሰቢያ መጽሐፍ በፊቱ አስጽፏል።” እነሱም ዘላለማዊ ሕይወት ይሸለማሉ።—ሚልክያስ 3:16፤ ራእይ 20:12, 15
አምላካዊ ፍርሐት ድል ያደርጋል
4. ይሖዋን እንድንፈራ የሚያበረታታን የትኛው የጥንት የማዳን ድርጊት ነው?
4 እሥራኤላውያን ከፈርኦን ግብፅ በሠልፍ በወጡበት ጊዜ ሙሴ ይሖዋን ብቻ ይፈራ እንደነበረ በግልጽ አሳይቷል። ወዲያው እሥራኤላውያን በቀይ ባሕርና በግብጻውያን የጦር ኃይል መሃል ተከበቡ። ምን ያደርጉ ይሆን? “ሙሴ ለሕዝቡ አትፍሩ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብጻውያን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ። ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የይሖዋን ማዳን እዩ፣ ይሖዋ ስለ እናንተ ይዋጋል። እናንተም ዝም ትላላችሁ” አላቸው። ይሖዋ በተዓምር ውኃውን ከፈለ፣ እሥራኤላውያንም በባሕሩ መሃል በደረቅ መሬት ተሻገሩ። ከዚያ በኋላም ውኃው እንደገና መፍሰስ ጀመረ። የፈርዖን ሠራዊት ተደመሰሰ። ይሖዋ፣ አምላክን በምታዋርደው ግብጽ ላይ የጥፋት ፍርዱን ሲያስፈጽም ፈሪሐ አምላክ የነበራቸውን ሕዝብ ግን አዳነ። ዛሬም በተመሳሳይ ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን ምሥክሮቹን ከሰይጣን ዓለም በማዳን ታማኝነቱን ያሳያል።—ዘጸአት 14:13, 14፤ ሮሜ 15:4
5, 6. ከሰው ይልቅ ይሖዋን መፍራት እንዳለብን የሚያሳዩት በኢያሱ ዘመን የነበሩ ምን ሁኔታዎች ናቸው?
5 እሥራኤላውያን ከግብጽ ከወጡ በኋላ ሙሴ 12 ሰላዮች ወደ ተስፋይቱ ምድር ላከ። አሥሩ ሰላዮች የምድሪቱ ነዋሪዎች ግዙፍ መሆናቸውን ሲያዩ ተሸበሩና እሥራኤላውያን ወደዚያች ምድር እንዳይገቡ ለማሳመን ሞከሩ። የተቀሩት ሁለቱ ማለትም ኢያሱና ካሌብ ግን “ዞረን የሰለልናት ምድር እጅግ መልካም ናት። ይሖዋስ ከወደደን ወተትና ማር ወደምታፈሰው ወደዚህ ምድር ያገባናል፣ እርስዋንም ይሰጠናል። ነገር ግን በይሖዋ ላይ አታምጹ እንደ እንጀራ ይሆኑልናልና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ። ጥላቸው ተገፏል። ይሖዋም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሯቸው” ብለው ተናገሯቸው።—ዘኁልቁ 14:7-9
6 ይሁን እንጂ እሥራኤላውያን በሰው ፍርሐት ተሸነፉ። በዚህም ምክንያት ወደ ተስፋይቱ ምድር ሳይደርሱ ቀሩ። ኢያሱና ካሌብ ግን ከአዲሱ የእሥራኤላውያን ትውልድ ጋር ወደዚች ምርጥ ምድር ለመግባትና የወይንና የወይራ ተክሎቿን ለመኮትኮት ታደሉ። ኢያሱ የእሥራኤልን ሕዝብ ሰብስቦ ባደረገው የስንብት ንግግር ላይ ይህን ምክር ሰጠ፦ “አሁንም ይሖዋን ፍሩ፤ በፍጹምም በእውነተኛም ልብ አምልኩት” አለ። ጨምሮም “እኔና ቤቴ ግን ይሖዋን እናመልካለን” አላቸው። (ኢያሱ 24:14, 15) ወደ አምላክ ጻድቅ አዲስ ዓለም ለመሻገር በዝግጅት ላይ በምንገኝበት በአሁን ጊዜ እነዚህ የኢያሱ ቃላት ለቤተሰብ ራሶችና ለሌሎች ክርስቲያኖች በጣም የሚያበረታቱ ናቸው!
7. ዳዊት አምላክን የመፍራትን አስፈላጊነት አጉልቶ የገለጸው እንዴት ነው?
7 የበጎች እረኛ የነበረው ዳዊትም ጐልያድን በአምላክ ስም በገጠመው ጊዜ ይሖዋን በመፍራት ረገድ ጥሩ ምሳሌ አሳይቷል። (1 ሳሙኤል 17:45, 47) ዳዊት ሊሞት በተቃረበበት ጊዜ “የይሖዋ መንፈስ በእኔ ተናገረ። ቃሉም በአንደበቴ ላይ ነበር። የእሥራኤል አምላክ ተናገረኝ። የእሥራኤል ጠባቂ እንዲህ አለ፦ በሰው ላይ በጽድቅ የሚሠለጥን በይሖዋም ፍርሐት የሚነግሥ እርሱ እንደ ማለዳ ብርሃን እንደ ጸሐይ አወጣጥ በጥዋትም ያለደመና እንደሚደምቅ ከዝናብ በኋላ ከምድር እንደሚበቅል ልምላሜ ይሆናል” ብሎ ለመናገር ችሏል። (2 ሳሙኤል 23:2-4) ይህ የአምላክ ፍርሐት ከዚህ ዓለም ገዥዎች መሃል በሚያስደንቅ ሁኔታ ጠፍቷል። ውጤቱስ እንዴት አሳዛኝ ነው! “የዳዊት ልጅ” ኢየሱስ በምድር ላይ በይሖዋ ፍርሐት ሲገዛ ሁኔታው እንዴት የተለየ ይሆናል!—ማቴዎስ 21:9
በይሖዋ ፍርሐት መመራት
8. የይሁዳ ምድር በኢዮሳፍጥ ግዛት ሥር የበለጸገው እንዴት ነው? ይህስ ዛሬ ለእኛ ምን ያመለክታል?
8 ዳዊት ከሞተ መቶ ዓመት ከሚያክል ጊዜ በኋላ ኢዮሳፍጥ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ። እሱም በይሖዋ ፍርሐት የሚገዛ ንጉሥ ሆነ። ለይሁዳ ምድር አምላካዊ ሥርዓትን መለሰ። በምድሪቱም ሁሉ ላይ ፈራጆችን መደበና የሚከተለውን መመሪያ ሰጣቸው፦ “ለይሖዋ እንጅ ለሰው አትፈርዱምና እርሱም በፍርድ ነገር ከእናንተ ጋር ነውና የምታደርጉትን ተመልከቱ። አሁንም ይሖዋን መፍራት በእናንተ ላይ ይሁን። በአምላካችንም በይሖዋ ዘንድ በደልና ለሰው ፊት ማድላት መማለጃም መውሰድ የለምና፣ ሁሉን ተጠንቅቃችሁ አድርጉ . . . እንዲሁ ይሖዋን በመፍራት በቅንነትም በፍጹምም ልብ አድርጉ።” (2 ዜና 19:6-9) በዚህም ምክንያት ዛሬ የአምላክ ሕዝቦች ከርኅሩኅ የበላይ ተመልካቾች አገልግሎት እንደሚጠቀሙ ሁሉ የይሁዳም ምድር በይሖዋ ፍርሐት በለጸገ።
9, 10. ኢዮሳፍጥ በይሖዋ ፍርሐት ድል ያደረገው እንዴት ነው?
9 ይሁን እንጂ የይሁዳ ምድር ጠላቶች ነበሯት። እነዚህ ጠላቶቿም የአምላክን ሕዝብ ጠራርገው ለማጥፋት ቆረጡ። የአሞን፣ የሞአብና የሴይር ተራራ ጦር ኃይሎች ወደ ይሁዳ ግዛት ጐረፉና ኢየሩሳሌም በከፍተኛ አደጋ ላይ ወደቀች። ለወረራ የመጣው ሠራዊት እጅግ ታላቅ ሠራዊት ነበር። ስለዚህ ኢዮሣፍጥ “የይሁዳ ሰዎች ሁሉ ከሕፃኖቻቸውና ከሚስቶቻቸው ከልጆቻቸውም ጋር በይሖዋ ፊት ቆመው ሳሉ” በጸሎት ይሖዋን ተማጠነ። ከዚያም ይሖዋ ላቀረቡት ጸሎት መልስ ሰጠ። የይሖዋ መንፈስ በሌዋዊው በየሕዚኤል ላይ መጣና “ይሖዋ እንዲህ ይላችኋል፦ ሰልፉ የይሖዋ ነው እንጂ የእናንተ አይደለምና ከዚህ ታላቅ ወገን የተነሣ አትፍሩ። አትደንግጡም። ነገ በእነርሱ ላይ ውረዱ። . . . እናንተ በዚህ ሰልፍ የምትዋጉ አይደላችሁምና ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ ተሰለፉ። ዝም ብላችሁ ቁሙ። የሚሆነውንም የይሖዋን መድኃኒት እዩ። ይሖዋም ከእናንተ ጋር ነውና አትፍሩ፤ አትደንግጡም። ነገም ውጡባቸው” ብሎ ተናገረ።—2 ዜና 20:5-17
10 በማግስቱ ጧት የይሁዳ ሰዎች ማልደው ተነሱ። በታዛዥነት ጠላቶቻቸውን ለመግጠም ሲወጡ ኢዮሳፍጥ ቆሞ “ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ ስሙኝ። በአምላካችሁ በይሖዋ እመኑ። ትጸኑማላችሁ። በነቢያቱም እመኑ። ነገሩም ይሳካላችኋል” አለ። ለይሖዋ የሚዘምሩ ዘማሪዎች ከታጠቁት ሰዎች ፊት እየሄዱ “ምሕረቱ ለዘላለም ነውና ይሖዋን አመስግኑ” እያሉ በኅብረት ይዘምሩ ነበር። ይሖዋም የጠላት ሠራዊት እንዲወናበድና እርስ በርስ እንዲጠፋፋ በማድረግ ከፍተኛ ፍቅራዊ ደግነት አሳይቷል። የይሁዳም ሰዎች ወደ ምድረ በዳው መጠበቂያ ግንብ በመጡ ጊዜ ያገኙት የጠላቶቻቸውን ሬሳ ብቻ ነበር።—2 ዜና 20:20-24
11. ፍርሐትን በተመለከተ አሕዛብ ከአምላክ ሕዝቦች የሚለዩት እንዴት ነው?
11 የጐረቤት መንግሥታት ይህን ተዓምራዊ ማዳን ሲሰሙ “የእግዚአብሔር ፍርሐት” ወደቀባቸው። ይሖዋን በመፍራት የታዘዘው ሕዝብም “በዙሪያው ካሉት ሁሉ አረፈ።” (2 ዜና 20:29, 30) በተመሳሳይም ይሖዋ በአርማጌዶን ፍርዱን ሲያስፈጽም አሕዛብ በአምላክና ፍርድ አስፈጻሚው በሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍርሐት ይርዳሉ። መለኮታዊው ቁጣ በሚገለጥበት ታላቅ ቀን ጸንተው መቆም አይችሉም።—ራእይ 6:15-17
12. ይሖዋን መፍራት በቀድሞ ዘመን ሽልማት ያስገኘው እንዴት ነበር?
12 ይሖዋን ጤናማ በሆነ መንገድ መፍራት ብዙ ሽልማቶችን ያስገኛል። ኖህ “እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተሰቦቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ።” (ዕብራውያን 11:7) የአንደኛው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችንም በተመለከተ ከስደቱ ጊዜ በኋላ ጉባኤዎች “በሰላም ኖሩ፤ ታነጹም። በይሖዋም ፍርሐትና በመንፈስ ቅዱስ መጽናናት እየሄዱ ይበዙ ነበር” የሚል ቃል ተጽፎአል። በአሁኑ ጊዜ በምሥራቅ አውሮፓ ከሚገኘው ሁኔታ ጋር በጣም በሚመሳሰል ሁኔታ ሥር ነበሩ ማለት ነው።—ሥራ 9:31
መልካሙን ውደዱ፤ ክፉውን ጥሉ
13. የይሖዋን በረከት ልንቀምስ የምንችለው እንዴት ብቻ ነው?
13 ይሖዋ ሁለመናው ጥሩ ነው። ስለዚህ “ይሖዋን መፍራት ማለት ክፉውን መጥላት ማለት ነው” (ምሳሌ 8:13) ስለ ኢየሱስ “ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመጻን ጠላህ። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ በደስታ ዘይት ቀባህ” ተብሎ ተጽፏል። (ዕብራውያን 1:9) እኛም እንደ ኢየሱስ የይሖዋን በረከት የምንሻ ከሆነ ክፋትን፣ ብልግናን፣ ዐመጽንና የሰይጣንን ትዕቢተኛ ዓለም ስግብግብነት መጸየፍ አለብን። (ከምሳሌ 6:16-19 ጋር አወዳድሩ) ይሖዋ የሚወደውን መውደድና እሱ የሚጠላውንም መጥላት አለብን። እሱን የሚያስከፋ ምንም ነገር ለማድረግ መፍራት ይገባናል። “ይሖዋንም በመፍራት ሰው ከክፋት ይመለሳል።”—ምሳሌ 16:6
14. ኢየሱስ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?
14 ኢየሱስ ፈለጉን በጥብቅ እንድንከታተል ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም። መከራንም ሲቀበል አልዛተም። ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።” (1 ጴጥሮስ 2:21-23) እኛም ይሖዋን ከፈራን የሰይጣን ዓለም በላያችን የሚያወርደውን ነቀፌታ፣ ውርደትና ስደት ለመቋቋም እንችላለን።
15. ሥጋን ሊገድሉ ከሚችሉት ይልቅ ይሖዋን መፍራት የሚኖርብን ለምንድን ነው?
15 ኢየሱስ በማቴዎስ 10:28 ላይ “ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ። ይልቅ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚችለውን ፍሩ” በማለት መክሮናል። አንድ ይሖዋን የሚፈራ ሰው በጠላቶቹ ቢገደልም እንኳን የሞት ጣር ያለው ኃይል ጊዜያዊ ብቻ ነው። (ሆሴዕ 13:14) የሞተው ሰው በትንሣኤ በሚነሣበት ጊዜ “ሞት ሆይ ድል ማድረግህ ወዴት አለ? ሲኦል ሆይ መውጊያህ የት አለ?” ለማለት ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 15:55
16. ኢየሱስ ይሖዋን መፍራቱን ያሳየውና ይሖዋን ያከበረው እንዴት ነበር?
16 ኢየሱስ ራሱ የይሖዋን ጽድቅ ለሚወዱና ክፋትን ለሚጠሉ ሁሉ ግሩም ምሳሌ ትቶአል። ኢየሱስ ይሖዋን ይፈራ እንደነበረ በዮሐንስ 16:33 ላይ እንደሚገኘው ለደቀመዛሙርቱ በተናገራቸው የመጨረሻ ቃላት ተገልጾአል። “በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬያችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ። ነገር ግን አይዟችሁ፣ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” የዮሐንስ ትረካ በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ አይኖቹን አነሳና እንዲህ አለ፦ አባት ሆይ ሰዓቱ ደርሷል ልጅህ ያከብርህ ዘንድ በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደሰጠኸው፣ ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው። . . . ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው።”—ዮሐንስ 17:1-6
ይሖዋን ፍሩ፤ አወድሱትም
17. የኢየሱስን ምሳሌ ልንቀዳ የምንችለው በምን መንገዶች ነው?
17 ዛሬስ እኛ የኢየሱስን የድፍረት ምሳሌ ልንከተል እንችላለንን? ይሖዋን ከፈራን በእርግጥ ልንመስለው እንችላለን! ኢየሱስ የይሖዋን ገናና ስምና ባሕርያት አሳውቆናል። ይሖዋን እንደ ልዑል ጌታችን አድርገን በመፍራት ከሌሎች ስም የለሽ አማልክት ሁሉ በላይ፣ ምሥጢራዊ ከሆነው ከሕዝበ ክርስትና ሥላሴ በላይ ከፍ ከፍ እናደርገዋለን። ኢየሱስ ሟች የሆነውን የሰው ልጅ በመፍራት ለመሸነፍ እምቢተኛ ሆኖ ይሖዋን በጤናማ ፍርሃት አገልግሎታል። “(ኢየሱስ) በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ። ይሖዋንም ስለመፍራቱ ተሰማለት።” እኛም እንደ ኢየሱስ ከምንቀበለው መከራ ታዛዥነትን መማራችንን በመቀጠልና ሁልጊዜ የዘላለም መዳንን ግባችን በማድረግ ይሖዋን እንፍራ።—ዕብራውያን 5:7-9
18. ለይሖዋ በአምላካዊ ፍርሃት ተነሳስተን ቅዱስ አገልግሎት ልናቀርብ የምንችለው እንዴት ነው?
18 ጳውሎስ በዚህ ለዕብራውያን በጻፈላቸው ደብዳቤ ላይ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን “የማይናወጥን መንግሥት ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ” በማለት በጥብቅ አሳስቧቸዋል። በአሁኑ ጊዜ “እጅግ ብዙ ሰዎችም” በዚህ ቅዱስ አገልግሎት እየተካፈሉ ነው። ይህ ቅዱስ አገልግሎት ምን ነገሮችን ያካትታል? ጳውሎስ ይሖዋ የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን መሥዋዕት በማዘጋጀት ያሳየውን የማይገባ ደግነት ከገለጸ በኋላ “እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምሥጋናን መሥዋዕት ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ በእርሱ (በኢየሱስ) እናቅርብለት” ይላል። (ዕብራውያን 12:28፤ 13:12, 15) እኛም ይሖዋ ያሳየንን የማይገባ ደግነት በማድነቅ የምንችለውን ያህል ያለንን ጊዜ በሙሉ ለቅዱሱ አገልግሎት ለማዋል መፈለግ ይኖርብናል። በአሁኑ ጊዜ እጅግ ብዙ ሰዎች የቀሪዎቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ታማኝ ባልንጀሮች በመሆን አብዛኛውን የዚህ አገልግሎት ክፍል እያከናወኑ ነው። እነሱም በምሳሌያዊ አባባል በአምላክ ዙፋን ፊት በመቆም “ሌሊትና ቀን ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ” መዳን የአምላክና የክርስቶስ መሆኑን ይናገራሉ።—ራእይ 7:9, 10, 15
ይሖዋን ለዘላለም ዓለም አክብሩት
19, 20. “በይሖዋ ቀን” ምን ሁለት ዓይነት ፍርሃቶች ይታያሉ?
19 የይሖዋ ልዕልና የሚረጋገጥበት ክብራማ ቀን በፍጥነት እየቀረበ ነው! “እነሆ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ቀን ይመጣል። ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ። የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፤ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።” ይህ የእልቂት ጊዜ “የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን” ነው። (ሚልክያስ 4:1, 5) ይህ ቀን በክፉዎች ልብ ውስጥ ሽብር ይለቃል። እነሱም “ከቶ አያመልጡም።”—ኤርምያስ 8:15፤ 1 ተሰሎንቄ 5:3
20 የይሖዋን ሕዝቦች ለሥራ የሚያነሳሳቸው ፍርሐት ግን ከዚህ ዓይነቱ ፍርሐት የተለየ ነው። “የዘላለም ወንጌል” አደራ የተቀበለው መልአክ በታላቅ ድምጽ “የፍርዱ ሰዓት ደርሷልና እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርንም ስጡት” በማለት ጥሪ አስተላልፎላቸዋል። (ራእይ 14:6, 7) የአርማጌዶን የሚያቃጥል ትኩሳት የሰይጣንን ዓለም በሚፈጅበት ጊዜ ይህን ፍርድ በማድነቅ ተመስጠን እንቆማለን። ሊፋቅ የማይችልና ጤናማ የሆነ የይሖዋ ፍርሃት በልባችን ውስጥ ይቀረጻል። በዚያን ጊዜ “የይሖዋን ስም ከጠሩትና ከሚድኑት” መሃል ለመገኘት የታደልን ያድርገን!—ኢዩኤል 2:31, 32፤ ሮሜ 10:13
21. የይሖዋ ፍርሃት ምን አይነት በረከቶችን ያስገኛል?
21 ከዚያ በኋላ አስደናቂ በረከቶችን እናገኛለን። የሕይወታችን ዘመንም ከዘላለም እስከ ዘላለም የሚቆይ ይሆናል። (ምሳሌ 9:11፤ መዝሙር 37:9-11, 29) ስለዚህ ተስፋችን መንግሥቱን መውረስም ይሁን ወይም በመንግሥቲቱ ምድራዊ ግዛት ማገልገል በአምላካዊ ፍርሃትና በአክብሮት ተነሳስተን ቅዱስ አገልግሎት ማቅረባችንን እንቀጥል። ይህስ እንዴት ያለ የተባረከ ውጤት ያስገኝልናል? ይሖዋን ፍራ የሚለውን ጥበባዊ ምክር ልብ በማለታችን ለዘላለም ዓለም የሚቆይ የአመስጋኝነት መንፈስ ያድርብናል።
ምን ብላችሁ ትመልሳላችሁ?
◻ “የይሖዋ ፍርሐት” ወይም “ይሖዋን መፍራት” ማለት ምን ማለት ነው?
◻ አምላክን መፍራት የጥንት ሕዝቦቹን የጠቀማቸው እንዴት ነበር?
◻ ኢየሱስ ምን የአምላካዊ ፍርሃት ምሳሌ ትቶልናል?
◻ ይሖዋን በመፍራት ፍጹም አቋማችንን ልንጠብቅ የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የኢየሱስ ወንድሞች ይሖዋን የሚያወድስ መዝሙር፣ ማለትም “የሙሴን ቅኔ” ሲዘምሩ ታይተዋል
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢዮሳፍጥ ሠራዊት በይሖዋ ፍርሃት ድል አድርጎአል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋን የሚፈሩ ሰዎች ከዘላለም እስከ ዘላለም የሚቆይ የሕይወት ዘመን ይወርሳሉ