“ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው”
1 በአንድ ወቅት ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ትዳርን በሚመለከት ሲነጋገር ነጠላነትን ‘ስጦታ’ እንደሆነ አድርጎ ከገለጸው በኋላ “ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው” አላቸው። (ማቴ. 19:10-12) ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ነጠላነት ስለሚያስገኘው ጥቅም የጻፈ ሲሆን ሌሎች ትዳር ባለመያዝ የእርሱን አርዓያ እንዲከተሉ አበረታቷል። (1 ቆሮ. 7:7, 38) በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የነጠላነትን ስጦታ ‘የተቀበሉ’ ሲሆን ብዙ ጥቅሞችንም አግኝተዋል። እነዚህ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?
2 ‘ሳይባክኑ’ ማገልገል:- ጳውሎስ አለማግባቱ ‘ሳይባክን’ ይሖዋን ማገልገል የሚያስችል አጋጣሚ እንደከፈተለት ተገንዝቦ ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ አንድ ነጠላ ወንድም በአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለመካፈል የሚያስችለውን ብቃት ለማሟላት ጥረት ማድረግ የሚችል ከመሆኑም በላይ ያላገባ ሰው አቅኚ ለመሆን፣ ሌላ ቋንቋ ለመማር፣ እርዳታ በሚያስፈልግበት ቦታ ሄዶ ለማገልገል፣ ቤቴል ለመግባት ወይም ሌሎች ልዩ የአገልግሎት መብቶችን ለመቀበል የተሻለ አጋጣሚ አለው። ጥልቀት ያለው የግል ጥናት ለማድረግና ለማሰላሰል እንዲሁም ለይሖዋ ከልብ የመነጨ ጸሎት ለማቅረብ የሚያስችል ሰፊ ጊዜ ያገኛል። ብዙውን ጊዜ ያላገባ ሰው ሌሎችን ለመርዳት በቂ ጊዜ ይኖረዋል። አንድ ሰው እነዚህን ነገሮች በማድረጉ ‘እርሱ ራሱ መጠቀሙ’ አይቀርም።—1 ቆሮ. 7:32-35፤ ሥራ 20:35
3 ባልተከፈለ ልብ ለአምላክ የሚቀርበው እንዲህ ያለው አገልግሎት ብዙ በረከቶች ያስገኛል። አንዲት ነጠላ እህት በኬንያ ለ27 ዓመታት ካገለገለች በኋላ እንዲህ በማለት ጽፋለች:- “በርካታ ወዳጆች የነበሩኝ ሲሆን ብዙ የሚሠራ ሥራም ነበር! አንድ ላይ ብዙ ነገሮችን እናደርጋለን [እንዲሁም] እርስ በእርስ እንጠያየቃለን። . . . ነጠላ መሆኔ ያስገኘልኝ ነጻነት በአገልግሎት ብዙ እንዳሳልፍ ያስቻለኝ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶልኛል። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና ለመመሥረት ችያለሁ።”
4 የነጠላነትን ስጦታ በአግባቡ ተጠቀሙበት:- አንድ ሰው ነጠላ ለመሆን የሚነሳሳበት ምክንያት ‘ስለ መንግሥተ ሰማያት’ ሲል መሆን እንዳለበት ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴዎስ 19:12) እንደ ማንኛውም ስጦታ ሁሉ ነጠላነት የሚያስገኘውን ደስታና ጥቅሞች ለማግኘት በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል። በርካታ ያላገቡ ሰዎች ነጠላነት የሚያስገኛቸውን አጋጣሚዎች በሚገባ በመጠቀምና ጥበብና ብርታት ለማግኘት በይሖዋ በመታመን ስጦታውን መቀበል ያለውን ጠቀሜታ ተገንዝበዋል።