የአምላክ ቃል እውነት ነው
1. መጽሐፍ ቅዱስ ምን ጠቃሚ መልእክት ይዟል?
1 መዝሙራዊው “የቃልህ መሠረት እውነት ነው” ሲል ጽፏል። (መዝ. 119:160 የ1980 ትርጉም ) ይሖዋ በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ አማካኝነት በሕይወት ውስጥ ለሚነሱ ዓበይት ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጣል። ለተጨነቁ ሰዎች ማጽናኛና ተስፋ ይሰጣቸዋል። ከዚህም በላይ ወደ እርሱ መቅረብ የምንችልበትን መንገድ ያሳየናል። አንዲት ሴት “የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማር ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ደማቅ ብርሃን የመውጣት ያህል ነው” በማለት አድናቆቷን ገልጻለች። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ባገኘኸው አጋጣሚ ሁሉ ለሌሎች ለማካፈል ጥረት ታደርጋለህ?
2. መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ሕይወታቸው እንዲሻሻል የሚረዳው እንዴት ነው?
2 ሕይወትን የሚለውጥና ሁሉንም ሰው የሚነካ እውነት:- የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሰዎችን ልብ የመንካትና ሕይወታቸውን የመለወጥ ኃይል አለው። (ዕብ. 4:12) በሴተኛ አዳሪነት ከመሰማራቷም በላይ የአልኮል መጠጥ ትጠጣና ዕፅ ትወስድ የነበረች ሮዛ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “አንድ ቀን በጣም ተስፋ ቆርጬ እያለሁ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ አንድ ባልና ሚስት መጽሐፍ ቅዱስ ለችግሮቻችን መፍትሔ ለማግኘት እንዴት ሊረዳን እንደሚችል ነገሩኝ። የአምላክን ቃል ማጥናት የጀመርኩ ሲሆን በጥናቱም በጣም ተደሰትኩ። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አኗኗሬን አስተካክዬ አዲስ ሕይወት ለመጀመር የሚያስችል ኃይል አገኘሁ። አሁን የሕይወትን ዓላማ ስለተገነዘብኩ ከአልኮል መጠጥና ከዕፅ ጥገኝነት ተላቅቄያለሁ። የይሖዋ ወዳጅ ለመሆን ስለጓጓሁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹን ለመጠበቅ ቆርጬ ነበር። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ ያዘለ ምክር ባልሰማ ኖሮ ይህን ጊዜ ሕይወቴን አጥፍቼ ነበር።”—መዝ. 119:92
3. የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች ከማካፈል ወደ ኋላ ማለት የሌለብን ለምንድን ነው?
3 ዛሬ ካሉ በርካታ መጻሕፍት በተለየ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋ ለተውጣጡ ሰዎች’ የሚሆን መጽሐፍ ነው። (ራእይ 7:9) አምላክ ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ይፈልጋል። (1 ጢሞ. 2:3, 4) በመሆኑም የአንድን ሰው አኗኗር ወይም አስተዳደግ በመመልከት ብቻ ምሥራቹን አይቀበልም ብለን መደምደም አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ በተቻለ መጠን በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀስን ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን መልእክት ለሁሉም ሰዎች መናገር አለብን።
4. ምሥክርነት በምንሰጥበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
4 ጥቅሶችን ጥቀስ:- በአገልግሎታችን ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ልንጠቀም የምንችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። መጽሔቶች በምታስተዋውቅበት ጊዜ ለመግቢያ በቀረበው ሐሳብ ላይ ያለውን ጥቅስ አውጥተህ ለማንበብ ጥረት አድርግ። አንዳንዶች በወሩ ውስጥ የሚበረከተውን ጽሑፍ በሚያስተዋውቁበት ጊዜ አንድ የታሰበበት ጥቅስ ማንበቡን ውጤታማ ሆኖ አግኝተውታል። ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ የምታነጋግረው ሰው ትክክለኛ የሆነውን እውቀት ደረጃ በደረጃ ማግኘት እንዲችል በየጊዜው ቢያንስ አንድ ወይም ሁለት ጥቅስ አንብብለት። መጽሐፍ ቅዱስ በምታስጠናበት ጊዜ ውይይቱ ቁልፍ በሆኑት ጥቅሶች ዙሪያ እንዲያተኩር አድርግ። አገልግሎት ላይ ባትሆንም አጋጣሚው ሲፈጠር መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመስከር እንድትችል መጽሐፍ ቅዱስ በቅርብ ይኑርህ።—2 ጢሞ. 2:15
5. በአገልግሎታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ለመጠቀም ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
5 በአገልግሎታችን ላይ አመቺ በሆነ በማንኛውም አጋጣሚ በመጽሐፍ ቅዱስ በመጠቀም ሌሎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ለተግባር የሚያነሳሳ እውነት ካለው ኃይል እንዲጠቀሙ እንርዳቸው።—1 ተሰ. 2:13