ለአምላክ ቃል ጥብቅና ትቆማላችሁ?
1 እውነተኛ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን በሚያጣጥለው በዚህ ዓለም ውስጥ የአምላክ ቃል ቀናተኛ ጠበቆች ናቸው። “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ” እንዳለባቸው ስለምናምን ወደ ይሖዋ ሲጸልይ “ቃልህ እውነት ነው” በማለት ከመሠከረው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ተመሳሳይ አቋም አለን። (2 ጢሞ. 3:16፤ ዮሐ. 17:17) ታዲያ ለአምላክ ቃል ውጤታማ በሆነ መንገድ ጥብቅና መቆም የምንችለው እንዴት ነው?
2 ቅዱሳን መጻሕፍትን አጥኑ:- ኢየሱስ የአምላክን ቃል በትጋት እንዳጠና ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲህ ማድረጉ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ዓመታት ቅዱሳን መጻሕፍትን ተጠቅሞ ማስተማር እንዲችል ረድቶታል። (ሉቃስ 4:16-21፤ 24:44-46) ታዲያ ጥቅሶችን በአእምሯችን የመያዝ ችሎታችንን ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? በእያንዳንዱ ቀን መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና በተለይ ደግሞ የሚያበረታታ ወይም ለአገልግሎት የሚጠቅም ሆኖ ባገኘነው አንድ ጥቅስ ላይ በማሰላሰል ነው። ለስብሰባዎች ስንዘጋጅ የተጠቀሱትን ጥቅሶች በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አውጥተን ማንበብ ይኖርብናል፤ ምናልባትም በጥቅሶቹ ላይ ሐሳብ ለመስጠት መዘጋጀት እንችላለን። በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ተናጋሪው ጥቅሶች ሲያነብ በራሳችን መጽሐፍ ቅዱስ አውጥተን መከታተል ይኖርብናል። የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅሶች ማጥናታችን ‘የእውነትን ቃል በትክክል ማስረዳት’ እንድንችል ያደርገናል።—2 ጢሞ. 2:15
3 በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቀሙ:- በአገልግሎት ስንካፈል በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀም ይኖርብናል። ለምሳሌ ሁኔታዎቹ የሚፈቅዱልን ከሆነ ለቤቱ ባለቤት አንድ ጥቅስ ለማንበብና በጥቅሱ ላይ ለመወያየት ጥረት ማድረግ አለብን። የቤቱ ባለቤት ጥያቄ ከጠየቀ ወይም የተቃውሞ ሐሳብ ካነሳ መልስ ለመስጠት መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀማችን የተሻለ ነው። ግለሰቡ ሥራ ላይ በሚሆንበት ጊዜም “ከመሄዴ በፊት አንድ ጥቅስ ብቻ እንዳነብልዎት ቢፈቅዱልኝ ደስ ይለኛል” በማለት አንድን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ ጎላ አድርገን መጥቀስ እንችላለን። በተቻለ መጠን የምታነጋግረው ሰው እንዲከታተልህ በማድረግ በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ጥረት አድርግ።
4 አንድ የቤት ባለቤት የሥላሴን ትምህርት የሚያፈርሱ ጥቅሶችን ሲመለከት “ዕድሜ ልኬን ቤተ ክርስቲያን ሄጃለሁ፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ እንደሚል በጭራሽ አላውቅም!” በማለት በግርምት ተናግሯል። ይህ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና የቀረበለትን ሐሳብ ሳያንገራግር ተቀብሏል። ኢየሱስ በጎቹ ድምፁን እንደሚሰሙ ተናግሯል። (ዮሐ. 10:16, 27) ልበ ቅን ሰዎች ጥቅሶችን በቀጥታ ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ማየታቸው እውነትን ለመቀበል የሚያስችላቸው ግሩም መንገድ ነው። ስለዚህ ሁላችንም እውነት ለሆነው የአምላክ ቃል ጠበቆች እንሁን!