የጥያቄ ሣጥን
◼ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንደ መስክ አገልግሎት ተቆጥሮ ለጉባኤ ሪፖርት መደረግ ይኖርበታል?
አንድ ክርስቲያን ወላጅ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚመራና በጥናቱ ላይ ያልተጠመቁ ልጆች የሚገኙ ከሆነ በሳምንት አንድ ሰዓትና አንድ ተመላልሶ መጠየቅ እንዲሁም በወር አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሪፖርት ማድረግ ይችላል። ጥናቱ ከአንድ ሰዓት በላይ ቢቆይም፣ በሳምንት ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ የተመራ ቢሆንም ወይም እያንዳንዱ ልጅ የሚያጠናው ለብቻው ቢሆንም እንኳ ከዚህ በላይ ሪፖርት አይደረግም።—አገልግሎታችን መጽሐፍ ገጽ 104ን ተመልከት።
በቤተሰቡ ውስጥ ያሉት ሁሉ የተጠመቁ ምሥክሮች ከሆኑ (ቢጠመቅም ሁለተኛውን የጥናት መጽሐፍ አጥንቶ ያልጨረሰ ልጅ እስከሌለ ድረስ) በጥናቱ ላይ ያለፈው ሰዓትም ሆነ ጥናቱ ራሱ እንደ መስክ አገልግሎት ተቆጥሮ ሪፖርት አይደረግም። ይህ የሆነበት ምክንያት የጉባኤው የመስክ አገልግሎት ሪፖርት በዋነኝነት የሚያሳየው ራሳቸውን ወስነው የተጠመቁ የይሖዋ አገልጋዮች ላልሆኑ ሰዎች ምሥራቹን በመስበክና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማስተማር እየተከናወነ ያለውን እንቅስቃሴ በመሆኑ ነው። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) ይሁን እንጂ ይህ ቋሚ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማድረጉን አስፈላጊነት በምንም መንገድ አይቀንሰውም።
ክርስቲያን ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የማጥናት ኃላፊነት አለባቸው። የቤተሰብ ጥናት ለመጀመር ወይም የጥናቱን ይዘት ለማሻሻል እገዛ የሚያስፈልጋቸው ቤተሰቦች ሽማግሌዎች እንዲረዷቸው መጠየቅ ይችላሉ። የጉባኤው አባል የሆነ ክርስቲያን ቤተሰብ ያልተጠመቀ ወንድ ወይም ሴት ልጅ ቢኖረውና ሌላ አስፋፊ ቢያስጠናው የተሻለ እንደሚሆን ከታመነበት ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹን ወይም የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹን ማማከር ያስፈልጋል። ሽማግሌው በጉዳዩ ከተስማማ ጥናቱን የሚመራው አስፋፊ እንደማንኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሁሉ ይህንንም ሪፖርት ማድረግ ይችላል።
ልጆችን በይሖዋ መንገድ ማሳደግ በመስክ አገልግሎት ሪፖርቱ ላይ ከሚገለጸው እጅግ የበለጠ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። (ዘዳ. 6:6-9፤ ምሳሌ 22:6) ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” ለማሳደግ የተጣለባቸውን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት ለሚያደርጉት ጥረት ሊመሰገኑ ይገባል።—ኤፌ. 6:4