መለኮታዊ ጥበብ በዋጋ ሊተመን የማይችል ጥቅም አለው
1 አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ይበልጥ ትኩረት መስጠት ያለባቸው በዛሬው ጊዜ የሰው ልጆች የሚደርሱባቸውን ችግሮች ለማቃለል መሆን አለበት ብለው ያስባሉ። እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለሰዎች በማስተማር የምናከናውነው ሥራ ከማንኛውም የበጎ አድራጎት ተግባር የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው አይገነዘቡም። ሁኔታው ሐዋርያው ጳውሎስ “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉ ሞኝነት ነው፤ ለእኛ ለምንድነው ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው” በማለት እንደገለጸው ነው። (1 ቆሮ. 1:18) አዎን፣ ክርስቲያናዊው አገልግሎት በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ እየተከናወኑ ካሉት ሥራዎች ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ መሆኑን እናውቃለን።
2 በዛሬው ጊዜ የተሻለ ሕይወት መኖር:- የሰው ልጆችን ችግሮች ለመቅረፍ የሚደረጉ ሰብዓዊ ጥረቶች የሚያስገኙት ውጤት በጣም ውስን ነው። ሕጎችን ማውጣት የወንጀል መስፋፋትን አላስቀረም። የሰላም ስምምነቶች መደረጋቸውና የሰላም አስከባሪ ኃይሎች መኖር ጦርነትን አላስቆመም። ማኅበራዊ ፕሮግራሞች ድህነትን ማጥፋት አልቻሉም። (መዝ. 146:3, 4፤ ኤር. 8:9) በአንጻሩ ግን የመንግሥቱ መልእክት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሚያስገኘውን አዲሱን ሰው እንዲለብሱ በመርዳት ሕይወታቸውን ለውጦታል። (ሮሜ 12:2፤ ቆላ. 3:9, 10) ይህም በአሁኑ ጊዜ የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ አስችሏል።—1 ጢሞ. 4:8
3 ብሩህ የወደፊት ተስፋ:- መለኮታዊ ጥበብ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት ከመርዳቱም በላይ ለወደፊቱ ጊዜ ትክክለኛ እቅድ ለማውጣት ያስችለናል። (መዝ. 119:105) የምንኖርበትን ሥርዓት ለማሻሻል በሚደረጉት ከንቱ ጥረቶች እጃችንን ከማስገባት ይጠብቀናል። (መክ. 1:15፤ ሮሜ 8:20) ከንቱ የሆኑ ግቦችን በማሳደድ ዕድሜያችንን እያባከንን ባለመሆናችን በጣም ደስተኞች ነን! ጥረቶቻችን ያተኮሩት ይሖዋ ጽድቅ የሚሰፍንበትን “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” እንደሚያመጣ በገባልን አስተማማኝ ተስፋ ላይ ነው። የይሖዋ የፍርድ ቀን ሲመጣ ተስፋቸውን በመለኮታዊ ጥበብ ላይ የጣሉ ሁሉ ትክክለኛውን ውሳኔ እንዳደረጉ በማያሻማ ሁኔታ ግልጽ ይሆናል።—2 ጴጥ. 3:10-13፤ መዝ. 37:34
4 መለኮታዊ ጥበብ ‘በዚህ ዓለም ጥበብ’ ለተጠላለፉ ሰዎች ሞኝነት ሊመስል ቢችልም ልንከተለው የሚገባን ብቸኛው መንገድ ግን እርሱ ነው። (1 ቆሮ. 1:21፤ 2:6-8) በመሆኑም “እርሱ ብቻ ጥበበኛ” ከሆነው አምላክ የተቀበልነውን መልእክት በምድር ዙሪያ ማወጃችንን እንቀጥላለን።—ሮሜ 16:27