ሌሎችን ለመርዳት ዝግጁ ናችሁ?
1 ይሖዋ ምንጊዜም ታማኝ አገልጋዮቹን የሚረዳበትን መንገድ ይፈልጋል። (2 ዜና 16:9፤ ኢሳ. 41:10, 13) ኢሳይያስ ይሖዋን ከአንድ መልካም እረኛ ጋር በማመሳሰል “ጠቦቶቹን በክንዱ ይሰበስባል፤ በዕቅፉም ይይዛቸዋል፤ የሚያጠቡትንም በጥንቃቄ ይመራል” ሲል ጽፏል። (ኢሳ. 40:11) ፍቅራዊ አሳቢነትን በማሳየት ረገድ ይሖዋን መኮረጅ የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመልከት።
2 አዲሶችን ለመርዳት ጥረት አድርጉ፦ አዲሶች ከእኛ ጋር እንዲቀራረቡና በመንፈሳዊ እንዲበረቱ በማድረግ መርዳት እንችላለን። (ምሳሌ 13:20) አንድ ወንድም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት በጀመረበት ወቅት ሌሎች እሱን ለመርዳት ያደረጉትን ጥረት ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “አንድ ቤተሰብ ለበርካታ ጊዜያት በቤተሰብ ጥናታቸው ላይ እንድገኝ ይጋብዙኝ ነበር። እድገት እያደረግሁ ስሄድ ደግሞ አንድ ወጣት ባልና ሚስት አቅኚዎች ሙሉ ቀን አብሬያቸው እንዳገለግል በተደጋጋሚ ይጋብዙኝ ነበር። በየዕለቱም ግሩም መንፈሳዊ ውይይቶች እናደርግ ነበር።” አክሎም “ወደ እውነት ከመምጣቴ በፊት ዓርብና ቅዳሜ ምሽት ሁሌ ለመዝናናት እወጣ ነበር። አሁን ግን ከወንድሞች ጋር ጊዜ ስለማሳልፍ ሌላ ነገር አያምረኝም” ሲል ተናግሯል። ጉባኤው ያሳየው ፍቅራዊ አሳቢነት ይህ ወንድም በእምነት ሥር ሰድዶ እንዲቆም ከማድረጉም ሌላ በአሁኑ ወቅት በቤቴል ውስጥ እንዲያገለግል ረድቶታል።—ቆላ. 2:6, 7
3 እርስ በርሳችሁ ተናነጹ፦ ወንድሞቻችን አንድ ችግር ላይ በሚወድቁበት ጊዜ በችግራቸው ደራሾች መሆናችንን ማሳየት እንችላለን። አቅመ ደካማ የሆነ ወይም እንደ ልብ መንቀሳቀስ የማይችል አስፋፊ ቢኖር አጠገቡ በመሆን በስልክ ለመመስከር ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህን እቤቱ ወስደህ ለማስጠናት ዝግጅት ማድረግ ትችላለህ? ሕፃናት ልጆች ያሏቸውና በአገልግሎት በሚካፈሉበት ጊዜ የአንተን እርዳታ የሚሹ ወላጆች ይኖሩ ይሆን? ወይም ደግሞ ፍርሃት ያለባቸውና ተመላልሶ መጠይቅ ለማድረግ ወይም በሌላ የአገልግሎት መስክ ለመሳተፍ የአንተን እርዳታ የሚፈልጉ አስፋፊዎች ይኖሩ ይሆን? ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅራዊ አሳቢነት እነሱን የምናንጽበትን መንገድ እንድንፈልግ ያነሳሳናል።—ሮሜ 14:19
4 ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ያለውን ፍቅራዊ አሳቢነት የምንኮርጅ ከሆነ እርስ በርስ እንበረታታለን፣ ጉባኤው በፍቅር አንድ እንዲሆንና የሰማዩ አባታችንን እንዲያወድስ እንረዳለን።—ኤፌ. 4:16