ክፍል 4—የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እድገት እንዲያደርጉ መርዳት
ጥናቶቻችን እንዴት እንደሚዘጋጁ ማሠልጠን
1 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ትምህርቱን በቅድሚያ የሚያነብብ፣ መልሶቹ ላይ የሚያሰምርና በራሱ አባባል ለመመለስ የሚሞክር ከሆነ በመንፈሳዊ ፈጣን እድገት ማድረግ ይችላል። ስለዚህ ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከጀመራችሁ በኋላ እንዴት መዘጋጀት እንደሚችል ለማሳየት ከተማሪው ጋር አንድ ላይ ተዘጋጁ። ከአብዛኞቹ ጥናቶቻችን ጋር አንድ ሙሉ ምዕራፍ ወይም ትምህርት አብረናቸው መዘጋጀቱ ጠቃሚ ነው።
2 ምልክቶችና ማስታወሻዎች:- ለአንቀጾቹ ለተዘጋጁት ጥያቄዎች እንዴት ቀጥተኛ መልስ ማግኘት እንደሚችል አስረዳው። ቁልፍ ቃላትንና ሐረጎችን ብቻ ለይተህ ያሰመርክበትን የግል ቅጂህን አሳየው። አብራችሁ በምትዘጋጁበት ወቅት የአንተን ምሳሌ በመኮረጅ በግል ቅጂው ላይ መልሱን ለማስታወስ የሚረዳው ነጥብ ላይ ብቻ ማስመር እንደሚያስፈልገው ያስተውል ይሆናል። (ሉቃስ 6:40) ከዚያም በራሱ አባባል መልሱን እንዲነግርህ ጠይቀው፤ ይህም ትምህርቱን ምን ያህል እንደተረዳው ለማወቅ ያስችልሃል።
3 ተማሪው ጥናቱን በሚዘጋጅበት ወቅት ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱትን ጥቅሶች አውጥቶ ማንበቡ አስፈላጊ ነው። (ሥራ 17:11) እያንዳንዱ ጥቅስ በአንቀጹ ውስጥ ያለን አንድ ነጥብ እንደሚደግፍ እንዲያስተውል እርዳው። እንዲሁም በጽሑፉ ሕዳግ ላይ አጠር ያለ ማስታወሻ መያዝ እንደሚችል ልታሳየው ትችላለህ። እያጠና ያለው ትምህርት የተመሠረተው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መሆኑን ማጉላት ያስፈልጋል። በተጨማሪም በጥናቱ ወቅት መልስ ሲሰጥ ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱትን ጥቅሶች በደንብ እንዲጠቀምባቸው አበረታታው።
4 አጠቃላይ ይዘቱን መቃኘት እና መከለስ:- ተማሪው የሚያጠናውን ጽሑፍ በጥልቀት መዘጋጀት ከመጀመሩ በፊት የትምህርቱን ጠቅላላ ይዘት መረዳቱ ይጠቅመዋል። ጥቂት ጊዜ ወስዶ ዋናውን ርዕስ፣ ንዑስ ርዕሶቹንና ሥዕሎቹን በመመልከት የትምህርቱን አጠቃላይ ይዘት መረዳት እንደሚችል ጠቁመው። በተጨማሪም የሚያጠናው መጽሐፍ የክለሳ ጥያቄዎች ካሉት ዝግጅቱን ከመደምደሙ በፊት በእነዚህ ጥያቄዎች በመጠቀም በትምህርቱ ወስጥ ያሉትን ዋና ዋና ነጥቦች መከለሱ ጠቃሚ መሆኑን ልትነግረው ያስፈልጋል። የዚህ ዓይነቱ ክለሳ ትምህርቱን እንዳይረሳው ይረዳዋል።
5 ጥናትህ ጥሩ ዝግጅት እንዲያደርግ ያገኘው ሥልጠና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የታሰበበት መልስ ለመስጠት ያስችለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከአንተ ጋር ማጥናቱን ከጨረሰ በኋላም ቢሆን ጥሩ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልማድ እንዲኖረው ይረዳዋል።