ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ምን ጥቅም እናገኛለን?
1 የይሖዋ ሕዝቦች በቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤት የመካፈል ልዩ መብት አግኝተዋል። (ኢሳ. 54:13፤ ዮሐ. 6:45) እርግጥ ነው፣ ከትምህርት ቤቱ የምናገኘው ጥቅም በአብዛኛው የተመካው በግለሰብ ደረጃ በምናደርገው ጥረት ላይ ነው። ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በመንፈሳዊነትህ ላይ ያመጣውን ለውጥ አስተውለሃል?
2 ገንቢ አስተያየት:- በርካታ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካቾች በንግግር ባሕርያት ላይ እየተሰጠ ያለው ጥልቀት ያለው ትምህርት ጉባኤያቸውን በመስክ አገልግሎት ላይ ውጤታማ እንዲሆን እንደረዳው ተናግረዋል። በተጨማሪም አንድ የበላይ ተመልካች የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጎላ ያሉ ነጥቦች በሚቀርቡበት ጊዜ አድማጮች ተሳታፊ እንዲሆኑ ዝግጅት ከተደረገ በኋላ ብዙ ወንድሞችና እህቶች ለየሳምንቱ የተመደበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም መከተል እንደጀመሩ አስተውሏል። በ2ኛው የተማሪ ክፍል ላይ ተማሪዎቹ መግቢያና መደምደሚያ መዘጋጀት ሳያስፈልጋቸው በሚያነቡት ነገር ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ መደረጉ ያስገኘውን ጥቅም አስመልክተው ብዙ ወንድሞች ገንቢ የሆነ አስተያየት ሰጥተዋል። ይህን ክፍል እንዲያቀርቡ የተመደቡት ተማሪዎች አሁን ይበልጥ ትኩረት የሚሰጡት የንባብ ችሎታቸውን ለማሳደግ ነው።—1 ጢሞ. 4:13
3 ሁሉም ተጠቃሚ መሆን ይችላል:- በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት አስደሳች መብት ነው። (ምሳሌ 15:23) የቃል ክለሳ ጥያቄውን አስቀድመን ማግኘታችን ተዘጋጅተን ለመሄድና ክፍሉ በሚቀርብበት ወቅት የታሰበበት ተሳትፎ ለማድረግ ያስችለናል። ከዚህም በላይ ከጥር 1, 2004 የመጠበቂያ ግንብ እትም አንስቶ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ላይ የምናነባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የያዙትን ጎላ ያሉ ነጥቦች የሚያብራሩ ርዕሰ ትምህርቶች መውጣት ጀምረዋል። ብዙዎች እነዚህን ርዕሰ ትምህርቶች በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጎላ ያሉ ነጥቦች በሚቀርቡበት ጊዜ ገንቢ የሆነ ሐሳብ ለመስጠት ችለዋል።
4 በትምህርት ቤቱ የተመዘገበ እያንዳንዱ ተማሪ ክፍሎችን የመዘጋጀትና የማቅረብ ልዩ መብት አለው። የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ከመድረክ ከሚሰጣቸው ገንቢ ሐሳቦች ሁላችንም የምንጠቀም ሲሆን ተማሪዎቹ ደግሞ ስብሰባው ካበቃ በኋላ በግል ከሚሰጣቸው ምክር ተጨማሪ ጥቅም ያገኛሉ። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም በተባለው መጽሐፍ ውስጥ የንግግር ባሕርይን በሚያብራሩት ምዕራፎች መጨረሻ ላይ ያሉት መልመጃዎች ደግሞ ተጨማሪ እርዳታ ያበረክታሉ።
5 ትምህርት ቤቱ በሚካሄድበት ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ ተግባራዊ ልታደርጋቸው የምትችላቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆኑ ሐሳቦች ስትሰማ በአገልግሎት ትምህርት ቤት መጽሐፍ የግል ቅጂህ ላይ ልትጽፋቸው ትችላለህ። በተማርከው ነገር ላይ አሰላስል፣ እንዲሁም ይህ መለኮታዊ ትምህርት እንዴት መንፈሳዊነትህን ለማሻሻል እንደረዳህ አስብ።