የቤተሰብ ፕሮግራም ይኑራችሁ—ለጉባኤ ስብሰባዎች
1 ክርስቲያን ወላጅ ከሆናችሁ ልጆቻችሁ ይሖዋን የሚወዱና የሚያገለግሉ እንዲሆኑ ብሎም አምላክ ቃል በገባልን አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ትፈልጋላችሁ። በሕይወታቸው ውስጥ ለይሖዋ አምልኮ የመጀመሪያውን ቦታ እንዲሰጡ እንዴት ልትረዷቸው ትችላላችሁ? ዋነኛው መንገድ የእናንተ ምሳሌነት ነው። (ምሳሌ 20:7) አንዲት እህት፣ የይሖዋ ምሥክር የሆነችውን የእናቷን ምሳሌ በማስታወስ እንዲህ ብላለች:- “ስብሰባ መሄድ አለመሄዳችን በጭራሽ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አልነበረም።” ይህ ደግሞ ፈጽሞ የማይረሳ ትምህርት ሆኗታል።
2 የቤተሰባችሁ አባላት የጉባኤ ስብሰባዎችን ዓላማ ይገነዘባሉ? በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የምናገኛቸው መመሪያዎች የአምላክን ፈቃድ በማድረግ እንድንቀጥል የሚረዱን ናቸው። በተጨማሪም ከወንድሞቻችን ጋር የምናሳልፈው ጊዜ በዋጋ ልንተምነው ከምንችለው በላይ የብርታት ምንጭ ይሆነናል። (ኢሳ. 54:13፤ ሮሜ 1:11, 12) ይሁን እንጂ የእነዚህ ስብሰባዎች ተቀዳሚ ዓላማ “በታላቅ ጉባኤ መካከል” ይሖዋን ማወደስ ነው። (መዝ. 26:12) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ለማሳየትና እርሱን ለማምለክ አጋጣሚዎች ይከፍቱልናል።
3 “እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ”:- የተቀደሰ ዓላማ ላላቸው ስብሰባዎቻችን ያለን አድናቆት ‘ተጠንቅቀን እንድንኖር’ በማድረግ እምብዛም አስፈላጊ ላልሆኑ ነገሮች ትኩረት በመስጠት ቀስ በቀስ ከስብሰባዎች የመቅረት ልማድ እንዳናዳብር ይረዳናል። (ኤፌ. 5:15, 16፤ ዕብ. 10:24, 25) የቤተሰባችሁን ፕሮግራም ስታወጡ በጉባኤ ስብሰባዎች መጀመር ትችላላችሁ። የምታከናውኗቸው ሌሎች ነገሮች ይህን ፕሮግራም እንዳያስተጓጉሉባችሁ ጥንቃቄ አድርጉ። ቤተሰባችሁ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር መሆን አለበት።
4 ወንድሞቻችን በጉባኤም ሆነ በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ሲሉ ስለሚወጡት መሰናክል ስናነብ ስሜታችን አይነካም? ምንም እንኳ ያንተ ሁኔታ ያን ያህል የከፋ ላይሆን ቢችልም አንተም ችግሮች ሳይኖሩብህ አይቀርም። ሰይጣን የአምላክ ሕዝቦች ይሖዋን ማምለክ ይበልጥ ከባድ እንዲሆንባቸው ያደርጋል። ይሁንና በጉባኤ ስብሰባዎች ለመገኘት እያደረጋችሁት ያለው ጥረት ከልጆቻችሁ እይታ የተሰወረ እንደማይሆን እርግጠኛ ሁኑ። በእርግጥም እንዲህ በማድረግ ለልጆቻችሁ መቼም የማይረሱት መንፈሳዊ ስጦታ ልትሰጧቸው ትችላላችሁ።