እርዳታ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው?
1 የይሖዋ ምሥክሮች በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች አደጋ እንደደረሰ ሲሰሙ “እርዳታ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው?” የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ያነሳሉ። በሐዋርያት ሥራ 11:27-30 ላይ የሚገኘው ዘገባ እንደሚያመለክተው የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በወቅቱ ተከስቶ በነበረው ረሃብ ምክንያት በይሁዳ ለሚኖሩ ወንድሞች እርዳታ ልከው ነበር።
2 በዘመናችን የድርጅታችን መተዳደሪያ ደንብ በተፈጥሮ አደጋዎች ወይም ሰው ሰራሽ በሆኑ ምክንያቶች ችግር ለደረሰባቸው እንዲሁም እርዳታ በሚያስፈልግበት ሌላ አጋጣሚ ላይ በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ ለበጎ አድራጎትና ለሰብዓዊ እርዳታ እንድናውል የሚያስችል ነው።
3 ለምሳሌ ያህል ባለፈው ዓመት በደቡብ እስያ ተከስቶ በነበረው የሱናሚ አደጋ ምክንያት ችግር የደረሰባቸውን ለመርዳት ብዙ ወንድሞች የገንዘብ መዋጮ አድርገዋል። ለተቸገሩ ወንድሞች ማኅበሩ የሚያደርገውን እርዳታ በመደገፍ ረገድ ወንድሞች ያሳዩት ይህ ከልብ የመነጨ አሳቢነት በጣም የሚደነቅ ነው። ይሁን እንጂ መዋጮ የላከው ግለሰብ ገንዘቡ ለአንድ ዓይነት የመልሶ ማቋቋም ሥራ እንዲውል የሚፈልግ መሆኑን ከገለጸ፣ አንዳንድ አገሮች ገንዘቡ ለጋሹ የፈለገው ዓላማ ላይ ብቻ እንዲውልና ይህም በተወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ መከናወን እንዳለበት የሚያስገድድ ሕግ አላቸው። ስለዚህ የተቸገሩት ወንድሞች የሚያስፈልጋቸው ነገር ተሟላም አልተሟላ ሕጉን መከተል ግዴታ ይሆናል።
4 በመሆኑም ለሰብዓዊ እርዳታና ለበጎ አድራጎት ሥራ የሚውል ገንዘብ መስጠት ስትፈልጉ ለዓለም አቀፉ ሥራ ብላችሁ መዋጮ ብታደርጉ ጥሩ ይሆናል። ይህ እርዳታ ለመልሶ ማቋቋም ሥራ የሚውል ከመሆኑም በተጨማሪ የወንድሞቻችንን መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ይረዳል። ምናልባት በአንዳንድ ምክንያቶች የተነሳ አንድ ግለሰብ ለዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ ሳይሆን በቀጥታ ለእርዳታ የሚውል ገንዘብ መስጠት ከፈለገ ስጦታው ተቀባይነት ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ የፈለገው ዓላማ ላይ ብቻ ይውላል። ነገር ግን እንዲህ ያሉት ስጦታዎች አንዳንድ ገደቦች ባይደረግባቸው ማለትም ለምን ዓላማና እንዴት ሊሠራባቸው እንደሚገባ የሚያሳስቡ ባይሆኑ ይመረጣል።
5 የገንዘብ መዋጮዎች በዋነኝነት ለዓለም አቀፉ ሥራ ገቢ እንዲሆኑ የምንጠይቅበት ምክንያት ገንዘቡን ለመልሶ ማቋቋም ሥራ ቢያስፈልግ ብሎ ከማስቀመጥ ይልቅ ለመንግሥቱ ሥራ የተለያዩ ዘርፎች ሊውል የሚችል ተጨማሪ ገንዘብ እንዲገኝ ስለሚያስችል ነው። በኤፌሶን 4:16 ላይ ካለው መንፈስ ጋር በመስማማት አስፈላጊውን ነገር ለማሟላት በአንድነት ተባብረን ስንሠራ በአካል የተመሰለው የክርስቲያን ጉባኤ “በፍቅር ያድጋል፤ ራሱንም ያንጻል።”