ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ በማጥናት ደስታ ማግኘት
1 ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ ከወጣበት ከ2005 አንስቶ በመስክ አገልግሎት በተለይ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት በሰፊው ስንጠቀምበት ቆይተናል። ይሁን እንጂ ግሩም የሆነውን ይህን ጽሑፍ በሚገባ ማንበባችን አስፈላጊ ነው። ይህ መጽሐፍ ከመስከረም 15, 2008 ጀምሮ በጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ላይ የሚጠና መሆኑ ጽሑፉን በደንብ ለመረዳት የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥርልናል።
2 የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ፣ በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ የሚገኙትን ጥያቄዎች በመጠቀም ትምህርቱ በምን ጉዳይ ላይ እንደሚያተኩር ከገለጸ በኋላ ከሥር ባሉት ጥያቄዎች አማካኝነት ጥናቱን ይመራል። ዋናውን ሐሳብ የሚደግፉ ጥቅሶች ተነበው ውይይት ሊደረግባቸው ይገባል። በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ የሚገኘው “መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ትምህርት” የሚለው ሣጥን፣ በምዕራፉ መጀመሪያ ላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ መልሶችን ስለያዘ ትምህርቱን ለመከለስ ይረዳል። ይህ መጽሐፍ ትምህርቱን ግልጽ፣ ቀላልና ማራኪ በሆነ መንገድ የሚያቀርብ በመሆኑ በጥናቱ ወቅት ተሳትፎ ማድረግ አስደሳች ይሆንልናል።
3 የመጽሐፉ ተጨማሪ ክፍል የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚያብራራ ዝርዝር ሐሳብ ይዟል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን በአንድ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚፈልጉ ከሆነ ይህንን ክፍል ልንጠቀም እንችላለን። በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ወቅት ተጨማሪ ክፍል ውስጥ ባሉት ርዕሶች ላይ ውይይት የሚደረግበት ጊዜ ይኖራል። የመጽሐፍ ጥናት አንባቢው ተጨማሪ ክፍል በሚለው ሥር የሚገኙትን አንቀጾች በሙሉ ማንበብ ይኖርበታል፤ በተጨማሪ ክፍል ውስጥ የሚገኙት አንዳንዶቹ ርዕሶች ብዙ አንቀጾች በሚኖራቸው ጊዜ ደግሞ ከፋፍሎ ማንበብና ውይይት ማድረግ ይቻላል። ተጨማሪ ክፍሉ ለውይይት የሚረዱ ጥያቄዎች ስለሌሉት የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ ዋና ዋና ነጥቦችን የሚያጎሉ ጥያቄዎች በመጠቀም አድማጮች ሐሳብ እንዲሰጡ ማድረግ ይችላል።
4 የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ላይ በምናጠናበት ወቅት በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ አንቀጾችን እንሸፍን ይሆናል። ሆኖም ይህን መጽሐፍ፣ ሌሎችን በተለይ ብዙም የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የሌላቸው ወይም ምንም የማያውቁ ሰዎችን ስናስጠና በአንድ ጊዜ በርካታ አንቀጾችን መሸፈን አይጠበቅብንም። (ሥራ 26:28, 29 የ1980 ትርጉም) የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ በጥቅሶቹ ላይ በደንብ መወያየት፣ ምሳሌዎችን ማብራራትና የመሳሰሉትን ነገሮች ማድረግ ይኖርብናል። ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ በሚጠናበት ጊዜ በየሳምንቱ በስብሰባ ላይ ለመገኘትና ጥሩ ተሳትፎ ለማድረግ ግብ አውጣ።