የጥያቄ ሣጥን
◼ ሙሽሮች የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ መፈጸም የሚፈልጉ ከሆነ ከሽማግሌዎች ጋር ሊነጋገሩባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ የሚከናወኑ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶች ለይሖዋ ክብር ያመጣሉ። በተለይ ማኅበረሰቡ በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ የሚከናወኑ ፕሮግራሞችን የድርጅታችን ነጸብራቅ አድርጎ ስለሚመለከታቸው በአዳራሹ ውስጥ የሚፈጸሙ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች ለይሖዋ ክብር የሚያመጡ መሆን አለባቸው። ሙሽሮች በመንግሥት አዳራሹ የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን ለመፈጸም ጥያቄ በሚያቀርቡብት ጊዜ “ሁሉም በአግባብና በሥርዐት” እንዲከናወን የጉባኤው ሽማግሌዎች ከሙሽሮቹ ጋር አንዳንድ ጉዳዮችን አንስተው መነጋገራቸው አስፈላጊ ነው።—1 ቆሮ. 14:40
የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን በመንግሥት አዳራሹ ለመፈጸም የሚፈልጉ ሙሽሮች ጥያቄያቸውን በዚያ አዳራሽ ለሚሰበሰበው ጉባኤ የአገልግሎት ኮሚቴ በጽሑፍ ማቅረብ ይኖርባቸዋል። ደብዳቤውን አስቀድመው ለኮሚቴው መስጠት ያለባቸው ከመሆኑም በላይ የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን በአዳራሹ ውስጥ የሚፈጽሙበትን ቀንና ሰዓት በደብዳቤው ላይ መግለጽ ይኖርባቸዋል። ሽማግሌዎቹ ለጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ሲሉ የጉባኤ ስብሰባ የሚደረግበትን ቀንና ሰዓት እንደማይለውጡ ሙሽሮቹ መገንዘብ ይገባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሙሽራዋም ሆነች ሙሽራው ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ያላቸው እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው የሚኖሩ መሆን አለባቸው።
የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ለአምላክ ክብር የሚያመጣ እንዲሆን ሙሽሮቹ ሊደረጉ የታሰቡትን ዝግጅቶች በተመለከተ ውሳኔ ከማድረጋቸው በፊት ከአገልግሎት ኮሚቴው ጋር መወያየት ይኖርባቸዋል። ሽማግሌዎቹ፣ ሙሽሮቹ የእነሱን የግል ምርጫ እንዲከተሉ ለመጫን መሞከር የሌለባቸው ቢሆንም በዝግጅቱ ውስጥ ሊካተቱ የታሰቡ ተገቢ ያልሆኑ ነገሮች ካሉ ማስተካከያ ሊደረግባቸው ይገባል። በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ መከፈት የሚኖርበት በመንግሥቱ ጣዕመ ዜማዎች ወይም በመዝሙር መጽሐፋችን ውስጥ ያለ ሙዚቃ ብቻ ነው። በተጨማሪም የመንግሥት አዳራሹን ለማስጌጥም ሆነ የወንበሮቹን አቀማመጥ ለማስተካከል የሚደረገው ማንኛውም ዝግጅት አስቀድሞ የኮሚቴውን ፈቃድ ማግኘት ይኖርበታል። ፎቶግራፍ ለማንሳትና ቪዲዮ ለመቅረጽ የታሰበ ዝግጅት ካለ ይህም የሥነ ሥርዓቱን ክብር ዝቅ በሚያደርግ መንገድ መከናወን የለበትም። ሙሽሮቹ አስቀድመው በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ልምምድ ማድረግ የሚፈልጉ ከሆነ ሽማግሌዎቹ ሌሎች የጉባኤ ፕሮግራሞችን እስካልነካ ድረስ ሊፈቅዱላቸው ይችላሉ። በማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ ምንም ዓይነት የጥሪ ወረቀት መለጠፍ የለበትም። ይሁን እንጂ ሽማግሌዎቹ በመንግሥት አዳራሹ የሚከናወነውን የጋብቻ ሥነ ሥርዓት አስመልክቶ በአገልግሎት ስብሰባ ላይ አጠር ያለ ማስታወቂያ እንዲነገር ሊያደርጉ ይችላሉ።
የሙሽሮቹ ሚዜዎችና ፕሮቶኮሎች በሙሉ የግድ የተጠመቁ መሆን ባይኖርባቸውም ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጨርሶ የወጣ አኗኗር ወይም በሥነ ሥርዓቱ ላይ በሚገኙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ ጥያቄ የሚፈጥር ዓይነት ምግባር ያላቸውን ግለሰቦች ለዚህ ዓላማ መጠቀም ተገቢ አይደለም። የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱን የሚያስፈጽመው ሰው በተቻለ መጠን ሽማግሌ መሆን አለበት። ሽማግሌዎች ብቃት ያላቸው የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ናቸው፤ ስለሆነም ትልቅ ግምት ለሚሰጠው ለዚህ ሥነ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን በጥሩ ሁኔታ ለማብራራት ይበልጥ ብቃት የሚኖራቸው እነሱ ናቸው።—1 ጢሞ. 3:2
የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱን የሚያስፈጽመው ሽማግሌም ትልቅ ኃላፊነት ስላለበት ከጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ጋር በተያያዘ ስለሚደረጉት ነገሮች በዝርዝር ሊነገረው ይገባል። ሽማግሌው ሙሽሮቹን በመጠናናት ላይ በነበሩበት ጊዜ ስለነበራቸው የሥነ ምግባር ሁኔታ ያነጋግራቸዋል፤ በዚህ ጊዜ ሙሽሮቹ ግልጽና ሐቀኛ መሆን ይኖርባቸዋል። ሙሽራዋም ሆነች ሙሽራው ቀደም ሲል ትዳር ከነበራቸው ከቅዱስ ጽሑፉና ከሕግ አንጻር እንደገና ለማግባት የሚያስችል ነፃነት ያላቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ አለባቸው። (ማቴ. 19:9) ይህም ሕጋዊ የሆነውን የፍቺ ሰነድ ቅጂ ለሽማግሌው ማሳየትን ይጨምራል።
ሙሽሮቹ ከሽማግሌዎቹ ጋር በግልጽ የሚወያዩና ሙሉ በሙሉ የሚተባበሩ ከሆነ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ሁሉንም የሚያስደስት ይሆናል።—ምሳሌ 15:22፤ ዕብ. 13:17