ከሁሉ ለላቀው የአምላክ ስጦታ አድናቆታችንን መግለጽ
1. ይሖዋን የምናመሰግንበት ምን ልዩ ምክንያት አለን?
1 ይሖዋ በርካታ ‘መልካም ስጦታዎችን’ የሰጠን ሲሆን ከሁሉ የላቀው ግን ውድ ልጁን በመስጠት ያደረገልን የቤዛው ዝግጅት ነው። (ያዕ. 1:17) ቤዛው የኃጢአት ይቅርታን ጨምሮ ብዙ በረከቶችን እንድናገኝ መንገድ ከፍቷል። (ኤፌ. 1:7) ለዚህም ምንጊዜም አመስጋኞች ነን። በተለይ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን በዚህ ውድ ስጦታ ላይ ለማሰላሰል ጊዜ መመደብ ይኖርብናል።
2. ለቤዛው ያለንን አድናቆት በቤተሰብና በግለሰብ ደረጃ ማሳደግ የምንችለው እንዴት ነው?
2 አድናቆታችሁ እንዲጨምር አድርጉ፦ ቤተሰባችሁ ለቤዛው ያለውን አድናቆት እየጨመረ እንዲሄድ ለመርዳት፣ መጋቢት 30 ከሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ቀደም ብሎ ባሉት ሳምንታት ውስጥ ለቤተሰብ አምልኮ በመረጣችሁት ምሽት ላይ ከቤዛው ጋር የተያያዙ ሐሳቦችን አንስታችሁ ለመወያየት ለምን ጊዜ አትመድቡም? በተጨማሪም በቤተሰብ አንድ ላይ ሆናችሁ ለመታሰቢያው በዓል ተብሎ የተዘጋጀውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ በየዕለቱ ማንበብ ትችላላችሁ። ቤዛው ስላስገኘላችሁ ጥቅም እንዲሁም ስለ ይሖዋ፣ ስለ ራሳችሁና ስለ ሌሎች እንዲሁም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያላችሁን አመለካከት የነካው እንዴት እንደሆነ በግለሰብ ደረጃ አሰላስሉ። ከዚህም ባሻገር በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚዘመሩትን ሁለቱን አዳዲስ መዝሙሮች ማለትም መዝሙር ቁጥር 8ን እና 5ን መለማመዱ ጠቃሚ ነው።—መዝ. 77:12
3. ለቤዛው ያለንን አድናቆት መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው?
3 አድናቆታችንን የምንገልጽባቸው መንገዶች፦ ለቤዛው ያለን አድናቆት ስለ ይሖዋ ብሎም ይሖዋ ልጁን በመላክ ስላሳየን ታላቅ ፍቅር ለሌሎች እንድንናገር ይገፋፋናል። (መዝ. 145:2-7) አንዳንድ ቤተሰቦች በመጋቢት፣ በሚያዝያና በግንቦት ወር ቢያንስ ከቤተሰባቸው አባላት አንዱ ረዳት አቅኚ እንዲሆን ዝግጅት በማድረግ ለቤዛው አድናቆታቸውን ይገልጻሉ። ይህን ማድረግ የማይቻል ከሆነ በአገልግሎት የምታደርጉትን ተሳትፎ ለማሳደግ ‘ጊዜ መግዛት’ ትችላላችሁ? (ኤፌ. 5:16) በተጨማሪም ለቤዛው ያለን አድናቆት ሌሎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ከእኛ ጋር እንዲገኙ ለመርዳት ያነሳሳናል። (ራእይ 22:17) በመሆኑም ልትጋብዟቸው ያሰባችኋቸውን ተመላልሶ መጠየቅ የምታደርጉላቸው ሰዎች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች፣ ዘመዶች፣ የሥራ ባልደረቦችና ጎረቤቶች ስም በዝርዝር ጻፉ፤ ከዚያም ሰዎችን በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ የምንጋብዝበት ልዩ ዘመቻ በሚጀምርበት ወቅት ብዙዎቹን ለመጋበዝ የተቻላችሁን ሁሉ ጥረት አድርጉ።
4. በመታሰቢያው በዓል ሰሞን የሚከፈቱልንን አጋጣሚዎች በጥበብ መጠቀም የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
4 ይሖዋ ለሰው ልጆች ለሰጠው ስጦታ ምን ያህል አድናቆት እንዳለን የምናሳይባቸው በርካታ አጋጣሚዎች በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ይከፈቱልናል። እንግዲያው ለቤዛውና ‘ሊደረስበት ለማይችለው የክርስቶስ ብልጽግና’ ያለንን አድናቆት ለማሳደግም ሆነ ለመግለጽ ይህን አጋጣሚ እንጠቀምበት።—ኤፌ. 3:8