አዲሶች እንዲሰብኩ ማሠልጠን የሚቻልበት መንገድ
1. በአገልግሎት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካፈላችሁበት ወቅት ምን ተሰምቷችሁ ነበር?
1 ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈላችሁበትን ቀን ታስታውሳላችሁ? በወቅቱ በጣም ፈርታችሁ ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው። ያገለገላችሁት መጽሐፍ ቅዱስን ካስጠናችሁ ሰው ወይም ከሌላ አስፋፊ ጋር ከነበረ የእሱን እርዳታ በማግኘታችሁ ተደስታችሁ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። አሁኑ ግን በአገልግሎት ረገድ ጥሩ ልምድ ስላገኛችሁ እናንተም በተራችሁ አዲሶችን በስብከቱ ሥራ ማሠልጠን ትችላላችሁ።
2. አዳዲስ አስፋፊዎች ምን መማር ያስፈልጋቸዋል?
2 አዳዲስ አስፋፊዎች ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ውይይት መጀመር፣ መጽሐፍ ቅዱስ መጠቀም፣ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ብሎም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመርና መምራት እንዴት እንደሚችሉ መማር ያስፈልጋቸዋል። በተጨማሪም በተለያዩ የአገልግሎት መስኮች እንዴት እንደሚካፈሉ ለምሳሌ፣ መንገድ ላይ እንዴት እንደሚመሠክሩና በንግድ አካባቢዎች እንዴት ሰዎችን እንደሚያነጋግሩ ሥልጠና ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። በእነዚህ የአገልግሎት ዘርፎች ጥሩ ምሳሌ በመሆንና ሐሳብ በመስጠት ማሻሻያ ማድረግ እንዲችሉ ልትረዷቸው ትችላላችሁ።
3. ምሳሌ በመሆን ሌሎችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
3 ምሳሌ በመሆን አስተምሩ፦ ኢየሱስ መስበክ የሚቻልበትን መንገድ ለደቀ መዛሙርቱ በተግባር አሳይቷቸዋል። (ሉቃስ 8:1፤ 1 ጴጥ. 2:21) ከአንድ አዲስ አስፋፊ ጋር ለማገልገል ዝግጅት ስታደርጉ አስፋፊው ምሳሌ አድርጎ ሊከተለው የሚችለውን ቀላል አቀራረብ ተዘጋጁ፤ ምናልባትም በጽሑፎቻችን ላይ የተሰጡትን የናሙና አቀራረቦች መጠቀም ትችሉ ይሆናል። ከዚያም አስፋፊው የምትናገሩትን መስማት እንዲችል የመጀመሪያዎቹን አንድ ወይም ሁለት ቤቶች እናንተ አንኳኩ። አንዱን ቤት አንኳክታችሁ ወደ ሌላው ቤት ከመሄዳችሁ በፊት አቀራረባችሁ ውጤታማ ስለመሆኑ አስፋፊውን አስተያየት ልትጠይቁት ትችላላችሁ። እንዲህ ማድረጋችሁ አስፋፊው ከሌሎች ጋር ማገልገል ያለውን ጥቅም እንዲገነዘብ የሚረዳው ከመሆኑም ሌላ አንድ ሰው አነጋግሮ ከጨረሰ በኋላ የምትሰጡትን ማንኛውንም አስተያየት በቀላሉ እንዲቀበል ያስችለዋል።
4. አንድን አዲስ አስፋፊ አቀራረቡን ካዳመጥን በኋላ እንዴት ልንረዳው እንችላለን?
4 ሐሳብ ስጡት፦ በተጨማሪም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንዴት መስበክ እንደሚችሉ መመሪያ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 10:5-14) እናንተም አንድን አዲስ አስፋፊ በተመሳሳይ መንገድ መርዳት ትችላላችሁ። ተራው ደርሶ በሚያነጋግርበት ጊዜ በጥሞና አዳምጡት። ከዚያም ከበሩ ዞር ካላችሁ በኋላ ግልጽ የሆነና ከልብ የመነጨ ምስጋና ከመስጠት ወደኋላ አትበሉ፤ በአቀራረቡ ላይ ማሻሻያ ሊያደርግባቸው የሚገቡ ነገሮች በምትመለከቱበት ጊዜም እንኳ ይህን ማድረጋችሁ ጠቃሚ ነው። አስተያየት ከመስጠታችሁ በፊት የሚቀጥለውን ቤት ሲያንኳኳ አቀራረቡ ይሻሻል እንደሆነ ለማየት ትመርጡ ይሆናል። ምናልባት መጀመሪያ ላይ ፈርቶ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ሁሉም አስፋፊዎች ተመሳሳይ ችሎታ እንደሌላቸው አስታውሱ፤ እንዲሁም አንድን ነገር በትክክል ማከናወን የሚቻልባቸው የተለያዩ መንገዶች እንደሚኖሩ ማስታወስ አስፈላጊ ነው።—1 ቆሮ. 12:4-7
5. በራሳችን ተነሳስተን ሐሳብ በምንሰጥበት ጊዜ ምን ማለት እንችላለን?
5 አንዳንድ ጊዜ አንድ አዲስ አስፋፊ አስተያየት ይጠይቃችሁ ይሆናል። ካልጠየቃችሁ ግን በራሳችሁ ተነሳስታችሁ እርዱት። ይህን በዘዴ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ተሞክሮ ያላቸው አንዳንድ አስፋፊዎች “አንድ ሐሳብ ብሰጥህ ቅር ይልሃል?” ወይም “አቀራረብህ እንዴት ነው? ጥሩ ነው?” ብለው ይጠይቃሉ። በሌላ በኩል ደግሞ እንደሚከተለው ብላችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ፦ “አዲስ አስፋፊ ሳለሁ . . . ማድረግ በጣም አስቸግሮኝ ነበር፤ ይሁንና . . . ማድረጌ ሁኔታውን እንዳሻሽል ረድቶኛል።” አንዳንድ ጊዜ ማመራመር የተባለውን መጽሐፍ አብራችሁ መመልከታችሁ ጠቃሚ ይሆናል። አስፋፊው ተስፋ እንዳይቆርጥ አቀራረቡን በሚመለከት ስለ አንድ ነገር ብቻ አስተያየት ስጡት።
6. ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ ‘ብረት ብረትን የሚስለው’ እንዴት ነው?
6 ብረት ብረትን ይስላል፦ ተሞክሮ የነበረው ወንጌላዊው ጢሞቴዎስ ማስተማሩንና እድገት ማድረጉን ለመቀጠል የተቻለውን ጥረት ሁሉ እንዲያደርግ ከጳውሎስ ማበረታቻ አግኝቶ ነበር። (1 ጢሞ. 4:13, 15) ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት ከወጣችሁ ብዙ ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም ችሎታችሁን ለማሻሻል የምታደርጉትን ጥረት ፈጽሞ ማቋረጥ አይኖርባችሁም። አብረዋችሁ ከሚያገለግሉ አስፋፊዎች ሌላው ቀርቶ በአገልግሎት ከእናንተ ያነሰ ተሞክሮ ካላቸው አስፋፊዎች ጭምር ትምህርት ለመቅሰም ጥረት አድርጉ፤ እንዲሁም ንቁ በመሆን ሌሎች በተለይ ደግሞ አዳዲስ አስፋፊዎች የተዋጣላቸው የምሥራቹ አገልጋዮች እንዲሆኑ በደግነት እርዷቸው።—ምሳሌ 27:17