ዓይንህ አጥርቶ የሚያይ ነው?
1. ‘አጥርቶ የሚያይ ዓይን’ አለን ሲባል ምን ማለት ነው?
1 ዓይናችን የሚያተኩርበት ነገር በድርጊታችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ኢየሱስ “ስለሆነም ዓይንህ አጥርቶ የሚያይ ከሆነ መላ ሰውነትህ ብሩህ ይሆናል” ብሎ መናገሩ የተገባ ነው! (ማቴ. 6:22) ዓይናችን በመንፈሳዊ “አጥርቶ” የሚያይ ከሆነ በአንድ ግብ ይኸውም የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ላይ ያተኮረ ይሆናል። የአምላክን መንግሥት እናስቀድማለን እንዲሁም ለአገልግሎት እንቅፋት የሚሆኑ የማያስፈልጉ ቁሳዊ ነገሮች ወይም እንቅስቃሴዎች ትኩረታችንን አይከፋፍሉብንም።
2. አመለካከታችንን ምን ሊያዛባው ይችላል? ይሁን እንጂ ምን ሊረዳን ይችላል?
2 ራስን የመመርመር አስፈላጊነት፦ መገናኛ ብዙኃን ያስፈልጓችኋል እያሉ በማስታወቂያ ላይ የሚነግሩን ወይም ሌሎች ያሏቸው ነገሮች አመለካከታችንን ሊያዛቡብን ይችላሉ። ጊዜያችንን፣ ገንዘባችንን ወይም ጉልበታችንን የሚያሟጥጥብንን አንድ ዓይነት ሥራ ከመጀመራችን ወይም የሆነ ዕቃ ከመግዛታችን በፊት ‘ለይሖዋ የማቀርበውን አገልግሎት ጥራት ያሻሽልልኛል ወይስ እንቅፋት ይሆንብኛል?’ ብለን ራሳችንን በመጠየቅ ‘ወጪያችንን ማስላታችን’ አስፈላጊ ነው። (ሉቃስ 14:28፤ ፊልጵ. 1:9-11) በተጨማሪም በአገልግሎቱ የበለጠ ጊዜ ለማሳለፍ እንድንችል አኗኗራችንን እንዴት ቀላል ማድረግ እንደምንችል በየጊዜው ማሰባችን የጥበብ አካሄድ ነው።—2 ቆሮ. 13:5፤ ኤፌ. 5:10
3. ኑሮዋን ቀላል ለማድረግ ስትል ማስተካከያዎችን ካደረገች አንዲት እህት ምን እንማራለን?
3 አንዲት እህት ዘወትር አቅኚ ሆና ማገልገል በጀመረችበት ወቅት በሳምንት ውስጥ የተወሰነ ሰዓት ብቻ መሥራቷ የሚያስፈልጋትን ነገር ለማሟላት የሚያስችላት በቂ ገንዘብ እንደሚያስገኝላት ብታውቅም የሙሉ ጊዜ ሥራ መሥራቷን ለመቀጠል ወሰነች። ከጊዜ በኋላ ግን እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ማንም ሰው ለሁለት ጌቶች ባሪያ መሆን አይችልም። እምብዛም የማያስፈልጉኝን ነገሮች መሥዋዕት ማድረግና መሠረታዊ በሆኑ ፍላጎቶቼ ብቻ ረክቼ መኖር እንዳለብኝ ተምሬያለሁ። ቁሳዊ ነገሮች ከጊዜ በኋላ እንደሚያረጁ ወይም ለእነሱ ያለን ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ እንዲሁም እነዚህን ነገሮች ለማግኘት መሮጤ ከድካም ሌላ የሚያስገኝልኝ ነገር እንደሌለ ተገነዘብኩ።” ያለችበት ሁኔታ ኑሮዋን ቀላል ለማድረግ የሚያስችሏትን ማስተካከያዎች እንድታደርግና ሥራ እንድትቀይር ያስቻላት ሲሆን ይህም በአቅኚነት አገልግሎቷ እንድትቀጥል ረድቷታል።
4. በአሁኑ ጊዜ አጥርቶ የሚያይ ዓይን ያለን መሆኑ አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?
4 የጊዜያችን አጣዳፊነት ምንጊዜም አጥርቶ የሚያይ ዓይን ለመያዝ የምናደርገውን ጥረት ይበልጥ አስፈላጊ ያደርገዋል። አንድ ቀን ባለፈ ቁጥር ወደዚህ ሥርዓት መደምደሚያ እንዲሁም የአምላክ አዲስ ዓለም ወደሚጀምርበት ጊዜ ይበልጥ እየተቃረብን ነው። (1 ቆሮ. 7:29, 31) ትኩረታችንን በስብከቱ ሥራ ላይ በማድረግ ራሳችንንም ሆነ የሚሰሙንን ማዳን እንችላለን።—1 ጢሞ. 4:16